Saturday, 16 August 2014 10:43

ቡሄን ከእነትውፊቱ ለትውልዱ ማስተዋወቅ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(3 votes)

     የቡሄ በዓል ጥንታዊ ታሪኩንና ትውፊታዊ ሥርዓቱን ሳይለቅ ለትውልድ ማስተዋወቅን ዓላማ ያደረገ ዝግጅት ባለፈው ማክሰኞ ምሽት በሀርመኒ ሆቴል ተካሂዷል፡፡ “እዮሃ ኢንተርቴይመንትና ኢቨንት” ከ“አርሂቡ የኪነጥበብ ባለሙያዎች” ጋር በመተባበር ባቀረቡት ዝግጅት ላይ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን “ቡሄ የልጆች በዓል በመሆኑ ነው እዚህ የተገኘሁት” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አዳራሹ መግቢያ ላይ በባህላዊ አልባሳት የተዋቡ ወጣቶች እንግዶችን እየተቀበሉ ሲያስተናግዱ ነበር። መድረኩን በባህላዊ የቡና አፈላል ሥርዓት ያጀቡት ሲሆን፣ መሶብ ከእነወስከንባው፣ የድፎ ማቅረቢያ እንቅብ፣ ግድግዳ ላይ የሚሰቀሉ አነስተኛ እርቦዎች… በመጠቀም ለዝግጅቱ ባህላዊ ድባብ ለመፍጠር ተሞክሯል፡፡
በታዋቂው መሲንቆ ተጫዋች ይስሐቅ ዜማ የተጀመረው የምሽቱ ዝግጅት፤ በእጅጉ አዝናኝ ነበር፡፡ የቡሄ ዳቦ ለመጋገር ምን እንደሚያስፈልግና አዘገጃጀቱም ምን እንደሚመስል እንዲገልፁ የተጋበዙ ሁለት እናቶች፤ ሙልሙል ዳቦዎቻቸውን ይዘው በመቅረብ ለታዳሚው ማብራሪያ ሰጥተዋል። በኮባ ቅጠል ተጠቅልሎ የሚጋገረው የቡሄ ዳቦ፤ ለአበልጅ፣ ለጐረቤትና በዋነኛነት ለቡሄ ጨፋሪ ልጆች እንደሚሰጥ እናቶቹ ተናግረዋል፡፡
የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ባደረጉት ንግግር፤ “ጠቃሚ ባህሎችን እየመረጡ እንደዚህ ባለ መድረክ ለሕዝብ ማስተዋወቅ ተገቢ ነው፡፡ በተለይ ልጆችን ማዕከል ያደረጉ ባህሎች እንዳይጠፉ አስባችሁ ይህን መድረክ በማሰናዳታችሁ ልትመሰገኑ ይገባል፡፡ እኔም ቡሄ የልጆች በዓል በመሆኑ ነው እዚህ የተገኘሁት” ብለዋል፡፡
በምሽቱ ዝግጅት ከሦስት የተለያዩ አካባቢዎች የተጋበዙ ሕፃናትና ወጣቶች ሦስት የተለያየ ዓይነት የቡሄ አጨፋፈርን አሳይተዋል፡፡ ከቀጨኔ አካባቢ የመጡት ሕፃናት በረኪናን ከመኪና፣ መኮረኒን ከሮኒ፣ ጀሪካንን ከአሜሪካን ጋር ቤት እንዲመታ እያደረጉ በመግጠም የአሁኑን ዘመን ቡሄ አጨዋወት ያሳዩ ሲሆን ከምኒልክ ሆስፒታል አካባቢ የመጡ ወጣቶች ደግሞ ወደ ጥንቱ ባህል የቀረበ የቡሄ አጨዋወት ለታዳሚው ለማስታወስ ሞክረዋል፡፡
የቡሄን አደራ አንች አሞራ (ሁለት ጊዜ)
አንቺ አሞራ ሆይ ቡሄ በይ (ሁለት ጊዜ)
ቡሄ ቡሄ በሉ ልጆች ሁሉ (ሁለት ጊዜ)
ሦስተኛውን የቡሄ ጨዋታ ያቀረቡት ከግቢ ገብርኤል አካባቢ የመጡ ሕፃናት ነበሩ፡፡ እነሱ ደግሞ በሁለቱ ዘመን መካከል ያለውን የቡሄ አጨፋፈር አሳይተዋል፡፡
መጣና ባመቱ እንደምን ሰነበቱ (ሁለት ጊዜ)
ክፈት በለው በሩን የጌታዬን (ሁለት ጊዜ)
ሆያ ሆዬ ጉዴ ጨዋታ ነው ልማዴ (ሁለት ጊዜ)…እያሉ ተጫውተው ሙልሙል ዳቦ ሲሰጣቸው “ዓመት አውደ ዓመት” በማለት መርቀዋል፡፡
ቡሄ መነሻው ሃይማኖታዊ እንደነበር የጠቆሙት ከጠቅላይ ቤተክህነት የተጋበዙት ደራሲና መምህር ካህሳይ ገብረእግዚአብሔር፤ ቀስ በቀስ ግን ባህል እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡
በቡሄ ጨዋታ ዙሪያ ጥናት ማድረጋቸውን የተናገሩት ተጋባዡ፤ የደብረታቦር ዕለት ለልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጥበት ታሪክ መነሻው ከመለኮታዊ አሰራር ምስጢር ጋር የተያያዘ ነው በማለት በቡሄ ዕለት ችቦ የሚበራበት ምክንያት ፀሐይ በምሽት ያልጠለቀችበትን ዕለት ለማስታወስ ሲሆን ጅራፍ የማስጮህ ልማዱም በሰማይ የታየ ነጐድጓድን ለማስታወስ እንደሆነ ሃይማኖታዊ ታሪክን እያጣቀሱ አብራርተዋል፡፡
ፀሐይ 24 ሰዓት ሳትጠልቅ በዋለችበት ዕለት ከብት ጥበቃ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ልጆች በሚያዩት ነገር ተደንቀው ፍንጠዛ ላይ ስለነበሩ ቤት መሄዱን ዘንግተውት ነበር፡፡ ልጆቻቸው የዘገዩባቸው ወላጆችም እረኞቹ ወደሚገኙበት መስክ ሙልሙል ዳቦ ይዘውላቸው ሄዱ፡፡ በዚህ መንፈሳዊ ታሪክ መነሻ ነው የቡሄ በዓል በጨዋታ፣ በሙልሙል ዳቦ ስጦታና ጅራፍ በማስጮህ የሚከበረው ብለዋል - ደራሲና መምህር ካህሳይ፡፡
ቡሄ በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች የየራሱ የአከባበር ስርዓት እንዳለው የጠቆሙት አጥኚው፤ ከቤት ቤት እየዞሩ ቡሄ የሚጨፍሩ እንዳሉ ሁሉ፤ ልጆቹ ሳይሆኑ ቤተሰቦቻቸው ቡሄ ጨፋሪዎቹ ያሉበት ድረስ ሄደው ሙልሙል የሚሰጡበት ባህል መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢ ልጆች ቡሄ ጨፍረው ሙልሙል ሲሰጣቸው በምትኩ አበባ እንደሚያበረክቱ፣ የቡሄ ዕለት ከየቤቱ የታለበ ወተት ተሰብስቦ ለቡሄ ጨፋሪዎች እንደሚሰጥ፣ በቡሄ የልጆችን ጭንቅላት በወተት የማጠብ ባህል ያለበት ማህበረሰብ እንዳለም ገልፀዋል፡፡
የቡሄ በዓል ልጆች ከሕብረተሰቡ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ያደርጋል ያሉት  ደራሲና መምህሩ፤ የቡሄ ዕለት ልጆች አዳዲስ አባባሎችን ይዘው ስለሚመጡ ለሥነ ቃል ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት በዓል ነው ብለዋል፡፡ አሁን አሁን የቡሄ በዓል አጨዋወት በከተማ ብቻ ሳይሆን በገጠርም እየጠፋ በመምጣት ላይ መሆኑን የጠቆሙት መምህር ካህሳይ፤ በተለይ በገጠሩ አካባቢ ከግጦሽ ሳር መቀነስ ጋር ተያይዞ ከብቶች በየደጁ ስለሚታሰሩ እረኝነት እየተረሳ መምጣቱንና በዚህም ምክንያት የቡሄ ጨዋታ እየጠፋ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ይህ ባህላዊ በዓል ከእነአካቴው ጠፍቶ ተረት እንዳይሆን ለመታደግ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴርና የመገናኛ ብዙኃን ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ያሉት አጥኚው፤ በዓሉ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የሚካተትበት መንገድ እንዲታሰብበት፣ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ በሚቀርቡ የልጆች ፕሮግራም ላይ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራበትም አሳስበዋል፡፡ የቡሄ በዓል ትውፊታዊ ሥርዓቱን ሳይለቅ ለትውልድ ለማስተዋወቅ ታልሞ በተካሄደው ዝግጅት፤ ስነቃል፣ እንቆቅልሽ፣ የቡሄ ገጠመኝ፣ ድራማና ወግ የቀረበበት ሲሆን በምሽቱ የተገኙ ታዳሚዎች ዝግጅቱ አዝናኝና አስተማሪ እንደነበር መስክረውለታል፡፡  

Read 5172 times