Saturday, 16 August 2014 10:40

ሞዴል ሜሮን ውድነህ ‘ሚስ አፍሪካ አሜሪካ 2014’ን አሸነፈች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሞዴል ሜሮን ውድነህ ባለፈው ቅዳሜ በአሜሪካ ሜሪላንድ ቤተሳይዳ ውስጥ በተከናወነው የ‘ሚስ አፍሪካ አሜሪካ 2014’ የቁንጅና ውድድር አሸናፊ በመሆን ዘውድ መድፋቷን ታዲያስ መጽሄት ከዋሽንግተን ዘገበ፡፡
በሚስ አፍሪካ አሜሪካ የቁንጅና ውድድር አሸናፊ በመሆን የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት የሆነችው ሞዴል ሜሮን፣ ዘንድሮ ለ9ኛ ጊዜ በተዘጋጀው በዚህ ውድድር ከተሳተፉና ለመጨረሻው ዙር ከደረሱ 20 ያህል ተወዳዳሪዎች መካከል የበለጠ ነጥብ በማግኘት ለሽልማት መብቃቷን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ሞዴል ሜሮን ማሸነፏን ተከትሎ በግሏ ድረ-ገጽ ላይ ባስተላለፈችው መልዕክት፣ “የሚደንቅ ብዝሃ ህይወት ባለቤት፣ ብዝሃነት ባላቸው ባህሎቻቸው የሚኮሩ ጀግና ህዝቦች መገኛ፣ የታላላቅ ነገስታት አገር የሆነችውን ጥንታዊቷን አፍሪካዊት አገር ኢትዮጵያን ወክዬ በቁንጅና ውድድሩ ላይ በመሳተፌና በማሸነፌ ትልቅ ኩራትና ደስታ ይሰማኛል” ብላለች፡፡ ባህላዊ ውዝዋዜ እንደምትወድ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን እንደምታዘወትርና በፋሽን አማካይነት የአገሯን ባህል ማስተዋወቅ እንደሚያስደስታትም ተናግራለች፡፡
ያለፈው አመት የ‘ሚስ አፍሪካ አሜሪካ 2014’ የቁንጅና ውድድር አሸናፊ ናይጀሪያዊቷ ካቲ ኦንሙ እንደነበረች ያስታወሰው ዘገባው፤ የዘንድሮዋ አሸናፊ ሞዴል ሜሮን ውድነህ ነዋሪነቷ በአሜሪካ ሞንትጎመሪ ካውንቲ መሆኑንና ከቦዊ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በጤና ሳይንስ መመረቋንም ጨምሮ ገልጿል፡፡

Read 2072 times