Saturday, 16 August 2014 10:37

“ወዝ አደር” እና “ሆድ አደር!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…የነሀሴ ዝናብ ሲያሰኘው እየራራልን፣ ሲያሰኘው ደግሞ ‘እየወቀጠን’ ይኸው መስከረምም እየመጣ ነው፡፡ ዝናቡን ወደሚፈለግባቸው ስፍራዎች ያሰራጭልንማ!
ስሙኝማ…ህጻናት ቤት ውስጥ አንድ ነገር ሲደረግ አይተው ዝም ይላሉ፡፡ ይሄኔ እናት ወይም አባት ነገሩን ለማውጣጣት የሚያባብሉበት ዘዴ አለ፡፡ እንበል የሆነ ብር ቤት ውስጥ ከተቀመጠበት ጠረጴዛ ላይ ይጠፋል፡፡ ይሄኔ አባት ህጻን ልጁን…አለ አይደል… “ቤቢ እዚህ ላይ የነበረውን ብር ማን ወሰደው?” ሲል ይጠይቃል፡፡ ልጁም እንደማያውቅ ይመልሳል፡፡ ይሄኔ አባት ምን ይላል መሰላችሁ… “ከነገርከኝ የምሰጥህን አታውቅም!” ‘ስስ ብልት’ መምታት ይሏችኋል እንዲህ ነው!
ልጅ አሁን ‘ለድርድር’ ፈቃደኛ ይሆናል፡፡ “ምን ትሰጠኛለህ?” ይላል፡፡ አባትም “ኬክ እሰጥሀለሁ…” ይላል፡፡ ልጅ ሳያመነታ “እማዬ ነች የወሰደችው…”
እናላችሁ…አባት ለብዙ መቶ ዓመታት ተሞክሮ ውጤታማ የሆነውን ማባባያ ተጠቀመ…‘ሆድን!’ ልጅም ለብዙ መቶ ዓመታት ተሞክሮ ውጤታማ የሆነውን ሀሳብ ማስለወጫ ተቀበለ…‘ሆድን!’ ዘንድሮም በሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሆድ ዋናው ማባበያና ‘ክር መበጠሻ’ እንደሆነ ነው፡፡ እንደውም ብሶበታል፡፡
ታዲያላችሁ…ነገሬ ብላችሁ ስታዩት ዘንድሮ ከአብዛኞቹ የግል ውሳኔዎቻችን ጀርባ አንድና አንድ (‘ቦተሊከኞች’ እንደሚሉት) ነገር ብቻ ነው ያለው…‘ሆድ!’
ለእናንተ ትከሻውን አስፍቶ ‘ቲፕ’ ሞቅ አድርጎ ለሚሰጠው ሰው እንደ ድመት የሚቅለሰለሰው አሳላፊ ‘የማሰቢያ’ ህዋሳቶቹ ያሉት ቀበቶው ላይ ነው፡፡ ቀድማችሁ የመጣችሁትን ውጪ ገትሮ በኋላ የመጣውን ሌሎችን ‘መንገድ እያስለቀቀ’ የሚያስገባ የጥበቃ ሠራተኛ ‘የማሰቢያ’ ህዋሳቶቹ ያሉት ቀበቶው ላይ ነው፡፡
ምንም እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ሠርቶ የማያውቀውን ድርጅት…አለ አይደል… “ሠራተኞቹ በሚያደርጉት ከፍተኛ የሥራ እንቅስቃሴ…” ምናምን እያለ የሚያንቆለዻዽሰው የእኔ ቢጤ ‘ወሬ ለቃሚ’… ‘የማሰቢያ’ ህዋሳቶቹ ያሉት ቀበቶው ላይ ነው፡፡
እናንተ ላይ ተለጥፋ ከርማ ድንገት ‘ብር አለው ተብሎ የሚታሰብ’ ሲመጣ የሞባይል ቁጥሯን የምትለውጥ እንትናዬ ‘የማሰቢያ’ ህዋሳቶቿ ያሉት ቀበቶዋ ላይ ነው፡፡
በችግሩ ጊዜ አብራው የቆየችውን የመዝገብ ቤት ሠራተኛ እንትናዬ ‘ዳምፕ’ አድርጎ… አለ አይደል… “እሷ እኮ ኢ.ሲ.ኤ. በወር ሀያ ሺህ ብር ነው የምትዝቀው…” ወደምትባለዋው የሚሄደው ሰው ‘የማሰቢያ’ ህዋሳቶቹ ያሉት ቀበቶው ላይ ነው፡፡
እናላችሁ…ልጄ “መደብ”፣ “ተጨቋኝ”፣ “መሀል ሰፋሪ” ምናምን ብሎ ነገር ቀርቷል፡፡ ዘንድሮ ያሉትውን ዜጎች አንዱ በሁለት መደብ ከፍሎናል… “ወዝ አደር” እና “ሆድ አደር!” አሪፍ አይደል! (እኔ የምለው…ዘንድሮ ‘መሀል ሰፋሪ’ የሚባል አለ አንዴ! አሀ…ሲባል አንሰማማ! ነገርዬው… “ከእኛ ጋር ካልሆናችሁ ከእነሱ ጋር ናችሁ…” አይነት ከሆነ እኮ ከራረመ!”) ታዲያማ…“ወዝ አደር” እና “ሆድ አደር!” ማለቱ በወዙ የሚያድርና በሆዱ የሚያድር ማለት ነው፡፡ በሆድ የምናድር እየበዛን ስንሄድ ነገሮች የመበላሸታቸው ዋናው ምልክት ነው፡፡
በየድርጅቱ፣ በየአክስዮኑ፣ በየማህበሩ የምናየው ንትርክ ከፊሎቹ አባሎች የማሰቢያ ህዋሳቶቻቸው ወደ ቀበቷቸው ዝቅ ሲሉ የሚፈጠሩ አይመስላችሁም! አለበለዛ… ተማምሎና ተገዝቶ የተቋቋመ ስብስብ ሦስት ወሩ ሊደፍን አምስት ቀን ሲቀረው ቅልጥ ያለ ‘ሱናሚ’ ውስጥ ሲገባ ምን ይባላል!
እናማ…ሀሳብ አለን፣ ‘አርቲስት እከሌ’ እንደሚባለው ሁሉ ከስሞቻችን በፊት ‘ሆድ አደር’ የሚለውም ‘ማዕረግ’ (ቂ...ቂ…ቂ…) ይካተትልንማ! ልክ ነዋ…ብዙዎቻችን እንደ ‘ሙያ’ ከያዝነው አይቀር ‘ኦፊሴላዊ’ ይሁንልና!
ለምሳሌ ለቃለ መጠይቅ ስንቀርብ ምን ሊባል ይችል መሰላችሁ…“ክቡራንና ክቡራት የዛሬው እንግዳችን ሆድ አደር ሰብስበው ዳር ከዳር ይባላሉ፡፡ ሆድ አደረ ሰብስበው በተለያዩ ስርአቶች ውስጥ በታማኝነት ያገለገሉና የሆድ አደርነትን ሙያ በአገሪቱ እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ…” ምናምን ይባላል፡፡ አሪፍ አይደል!
ታዲያላችሁ…በየጓዳ አቤት ሆዱን ሲወድ! ምናምን መባባል ቀርቶ ‘ሆድ አደርነት’ ‘የሚያኮራ ሙያ’ ይሆናል፡፡ (ማሳሰቢያ “‘ከርሳም!’ ብሎ መሳደብ የተከበረን ሙያ ማንቋሸሽና መስደብ ስለሆነ ሊያስጠይቅ እንሚችል እናሳስባለን፡፡”)
የምር ግን…አለ አይደል…‘ማሰቢያችንን’ ሆዳችን ላይ የሆንን እየበዛን ነው፡፡ ባለገንዘብ ወይም ባለስልጣን ፊት በአፍ ጢማችን ለመደፋት የሚዳዳን በሱፍ ‘ቂቅ’ ያልን ‘ዝርያችን’ እየበዛ ነው፡፡
ስሙኝማ…የምር ብታሰቡት እኮ ‘ሆድ አደር’ የሚለው መደለያ ከስም በፊት መግባት የጀመረ ዕለት ጥያቄው ምን ይሆናል መሰላችሁ… “ከአቶና ከሆድ አደር በብዛት ጥቅም ላይ የዋለው የትኛው ነው?” ምናምን የሚል ይሆናል፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የሥራን ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…አንዱ ፖሊስ ተፈላጊ ወንጀለኛ ፊት ለፊቱ ገጥሞት ሳይዘው ወንጀለኛው ያመልጣል፡፡ እናላችሁ…ጉዳዩ የቀረበላቸው ዳኛ ፖሊሱን… “ለምንድነው ወንጀለኛውን እንዳገኘኸው ያልያዝከው?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡ እሱዬውም… “ጌታዬ እንዴት ብዬ ልያዘው?” ይላል፡፡
“ሥራህ አይደለም እንዴ! እንዴት ብዬ ልያዘው ብሎ ነገር ምንድነው!” ይሉታል ቆጣ ብለው፡፡
ፖሊሱ ምን አለ መሰላችሁ…“በአንድ እጄ ዱላ፣ በሌላ እጄ ሽጉጥ ይዣላሁ፡፡ ጌታዬ እንዴት ልያዘው… ሦስተኛ እጅ የለኝ!” ብሎ አረፈው፡፡ ‘ተፖለሰና’ አረፈው!
ስሙኝማ… እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… ዘንድሮ የህዝብ ግንኙነት ሠራተኞች አያሳዝኑም! ልክ ነዋ…ዋናው ሥራቸው እኮ መረጃ ከመስጠት ይልቅ…አለ አይደል… ፈረንጆች ‘ዳሜጅ ኮንትሮል’ እንደሚሉት አይነት እየሆነ ነው፡፡ መሥሪያ ቤታቸው በሆነ ነገር ከተወቀሰ…“አገልግሎት አጓድሏል” ከተባለ “አጥፍተናል፣ እናስተካክላለን…” ከማለት ይልቅ “አገራችን በተያያዘችው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ጎዳና…” ምናምን አይነት ቃላት በበዙበት መግለጫ ነገርዬውን ሙያዊ ሳይሆን ካድሬያዊ ያደርጉታል፡፡
የምር ግን ይሄ ‘የአገልግሎት መጓደል’ የሚሉት ነገር…እንደው መቼ ነው እንደ ሌላው ህዝብ “እሰይ ስለቴ ሰመረ…” እያልን ስቀን ቤታችን የምንገባበት እያሰኘን ነው፡፡ በዛ ሰሞን ቴሌ የኢንተርኔቱ መቆራራጥ ችግር ከምናምን ቀን ጀምሮ “ሙሉ ለሙሉ ተፈቷል” እንዳለው ሁሉ…መብራትና ውሀንም ለዚህ ያብቃቸውማ!
ሆድ አደርነት እኮ ‘ጣጣ ፈንጣጣ’ የለውም… ልክ ነዋ…“ለክሬ ስል…” “ለማተቤ ብዬ…” ብሎ ነገር የለም።
እኔ የምለው…እንኳን ለቡሄ አደረሳችሁማ! የበፊቱ የቡሄ ግጥም…
“…ያቺን ድግስ ውጬ ውጬ
በድንክ አልጋ ተገልብጬ…”
ምናምን የሚል ስንኝ ነበረው፡፡ እሺ ያኔስ ለጭፈራ ነው… ዘንድሮ ማሰቢያችንን ቀበቷችን ላይ አድርገን “ያቺን ድግስ ውጬ ውጬ…” ሳንል…አለ አይደል…እንደ ሆዳችን በሰፋ አልጋ ላይ ‘የምንገለበጥ’ መአት ሆነናል፡፡ የ‘ሆድ አደርነት’ ትልቁ ችግር ምን መሰላችሁ…‘በሆድ አደሩ’ ድርጊት ምክንያት በዚያኛው ወገን… አለ አይደል… የሚገባውን ጥቅሙን የሚነጠቅ፣ መብቱን የሚገፈፍ፣ የእሱ የሆነውን “ሲያምርህ ይቅር…” የሚባል መአት መሆኑ ነው፡፡
ማሰቢያችንን ከቀበቷችን አላቆ ወደ ‘ትውልድ ስፍራው’ ይመልስልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3096 times