Saturday, 16 August 2014 10:22

አድማስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ወደ ዩኒቨርሲቲ አደገ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

      አድማስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ ወደ ዩኒቨርሲቲነት ማደጉን አስታወቀ፡፡ በጥቅምት ወር 1991 ዓ.ም በቢዝነስ ማሰልጠኛ ማዕከልነት ስራ የጀመረው ተቋሙ፤ በተመሰረተበት ዓመት አጋማሽ ላይ ወደ ኮሌጅነት ማደጉን የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ጠቁመው ከስምንት ዓመት በኋላም ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ማደጉን አስታውሰዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው አቅሙንና ብቃቱን በማሳደግ በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ መሰረት የሚጠበቅበትና መስፈርት በማሟላት ካለፈው ሀምሌ ወር ጀምሮ ወደ ዩኒቨርሲቲነት አድጓል ተብሏል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርሲቲውን የስያሜ ጥያቄ በመቀበል ተቋሙን ከገመገመና መስፈርቶቹን ማሟላቱን ካረጋገጠ በኋላ ተቋሙ ያቀረበውን የደረጃ ለውጥ ማፅደቁን ዩኒቨርሲቲው የላከው መግለጫ ይጠቁማል፡፡
“አንድ ተቋም ወደ ዩኒቨርሲቲነት ለማደግ  ከሶስት ፋኩልቲ በላይ እንዲኖረው ይጠበቃል” ያሉት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ኃላፊ፤ አድማስ ዩኒቨርስቲ ግን አራት ፋኩልቲዎችና ስምንት ካምፓሶች ያሉት በመሆኑ እውቅናውን ሊያገኝ ችሏል ብለዋል፡፡
በቅርቡም መገናኛ አካባቢ “መገናኛ አደባባይ” ካምፓስ በሚል አዲስ ካምፓስ መክፈቱን የገለፁት ኃላፊው፤ ተቋሙ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰባት፣ በሱማሌ ላንድ ዋና ከተማ ሃርጌሳ ውስጥ አንድ ካምፓስ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ አራት አዳዲስ የድህረ ምረቃ ትምህርት ዘርፎችን ለማስተማር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን በመጠቆም፤ በአካውንቲንግ ኤንድ ፋይናንስ፣ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን፣ በሂውማን ሪሶርስ ማኔጅመንትና ኮምፒዩተር ሳይንስ ዘርፎች እንደሚያስተምር አብራርተዋል፡፡ ከቢዝነስ ማሰልጠኛ ማዕከልነት እስከ ዩኒቨርስቲነት ለማደግ ተቋሙ የ16 ዓመታት ትግልን እንደጠየቀ የገለፁት ኃላፊው፤ ከ200ሺ ብር ካፒታል ተነስቶ የመቶ ሚሊዮን ብር ካፒታል ባለቤት ለመሆን እንደቻለ አስታውቀዋል፡፡ ተቋሙ እስካሁን ከ35 ሺህ በላይ ተማሪዎች ማስመረቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 7639 times