Saturday, 24 December 2011 11:57

ደበበ እሸቱ የምስክርነት ቃሉን ሰጠ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

“ፀጉሬ እየተነጨ ተደብድቤአለሁ” - አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር የኢ.ብ.አ.ፓ ሊቀመንበር

- “በቁጥጥር ሥር ከዋልኩ 10 ቀናት በኋላ የኢሜል መልዕክት

መለዋወጤን የሚገልፅ ማስረጃ ቀርቦብኛል” - ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ

- “የሽብር ተግባር እንደተሰጠሽ ከተናገርሽ እንፈታሻለን ብለውኛል” -ጋዜጠኛ ርዕዮተ ዓለሙ

- የእነ ዶ/ር መራራ ጉዲና የሙያ ምስክርነት ሳይሰማ ቀርቷል

ህገ መንግስቱንና ህገመንግስታዊ ሥርዓቱን በሃይልና በሽብር ድርጊት ለማናጋትና ለማፍረስ ተንቀሳቅሰዋል በሚልና በሌሎች አራት ወንጀሎች በእነ ኤልያስ ክፍሌ መዝገብ ክስ ቀርቦባቸው በእስር ላይ ከሚገኙት ተከሳሾች መካከል ለጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ የመከላከያ ምስክር በመሆን አርቲስት ደበበ እሸቱ ፍ/ቤት ቀርቦ የምስክርነት ቃሉን ሰጠ፡፡ ከጋዜጠኛዋ ጋር የረዥም ጊዜ ትውውቅ እንዳለውና በሥራዎቿ እንደሚያደንቃት፤ “ኢትዮጵያን ሪቪው” ለተባለ ድረገፅ እንድትሠራ ከድረገፁ ባለቤት ጋር እንዳገናኛትም ተናግሯል፡፡  የ69 ዓመት ዕድሜ እንዳለውና የኪነጥበብ አማካሪ መሆኑን የተናገረው ደበበ እሸቱ፤  የጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ሥራዎችን እንደሚያደንቅ፤ “እንደኖህ መርከብ” የተባለ አንድ  ሥራዋን ለእሷ ሣይነግራት በውጪ አገር ለውድድር እንዳቀረበው፣ በዚህ መሠረትም በርካታ የድረገፅ ባለቤቶች ከእሷ ጋር አብረው ለመሥራት ፍላጐት ማሣደራቸውን ከእነዚህም አንዱ “ኢትዮጵያን ሪቪው” የተባለው ድረገፅ መሆኑን ገልጿል፡፡ የድረገፁን ባለቤት ኤልያስ ክፍሌን ከጋዜጠኛዋ ጋር የማገናኘቱን ተግባር መፈፀሙንና ከዚያ በኋላ ስላለው ነገር የሚያውቀው ጉዳይ እንደሌለም ተናግሯል፡ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ቃላቸውን እንዲሰጡ በሰጣቸው እድል ተጠቅመው ሁሉም ተከሳሾች ሃሣባቸውን ለችሎቱ የገለፁ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀመበር አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር በሰጠው ቃል፤ ፓርቲያቸው የተቋቋመው ገዢው ፓርቲን ለመቃወም እንጂ ለመደገፍ አለመሆኑን ገልፆ “መለስ በቃ” የሚለው ፅሁፍ በፓርቲው ለተቃውሞ ሰልፍ ማድመቂያ መፃፉን አመልክቷል፡ “በኢብአፓ አመራርነቴ የተቀበልኩት የሽብር ተግበር የለም” ያለው አቶ ዘሪሁን፤ “ከጋዜጠኛ ኤልያስ ክፍሌ ጋር ያለኝ ግኙኝነት የጋዜጠኛና የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ግንኙነት ብቻ ነው፡፡ የቀረበብኝ ክስ ገዥው ፓርቲ ሆን ብሎ ሰላማዊ ትግሉን ለማፈን የሚያደርገው እንቅስቃሴ አካል ነው” ብሏል፡፡ በእስር ላይ በነበረበት ወቅት ፀጉሩን እየተነጨ ይደበደብ እንደነበርና ይህንንም ለፍ/ቤቱ ለማሣየት እንደሚችል ተናግሯል፡፡    ዐቃቤ ህግ በ3ተኛ ተከሳሽነት ክስ ያቀረበበት የቀድሞ የ”አውራምባ ታይምስ” ጋዜጣ ዋና  አዘጋጅ ውብሸት ታዬ በበኩሉ፤ ሰኔ 12 ቀን 2003 ዓ.ም በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውዬ ቃሌን ለፖሊስ መስጠቴን የሚያመለክት ማስረጃ ከመዝገቡ ጋር ተያይዞ እያለ ሰኔ 23/2003 ዓ.ም የኢሜል መልዕክቶችን መለዋወጤን የሚያስረዳ መረጃ ቀርቦብኛል፡፡ ዐቃቤ ህግ በማስረጃነት ካቀረባቸው የኢሜል መልዕክቶች መካከል እኔ የማላውቃቸውና ያልነበሩ መልዕክቶች ተጨምረውባቸዋል፡፡ አባቴ አይናቸዉን በመታመማቸው ምክንያት በሐኪም ኦፕራሲዮን መደረጋቸውን ገልጬ የፃፍኩት ኢሜል “ኦፕሬሽኑ ተሣክቷል”  የሚል ሌላ መልዕክት እንዲይዝ ተደርጐ መቅረቡ አላግባብ ነው” ሲል ተቃውሞውን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

“ሥራዬ መምህርትነትና ጋዜጠኝነት ነው” በማለት ቃሏን ለፍ/ቤት መስጠት የጀመረችው 5ኛዋ ተከሳሽ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ፤ በጋዜጠኝነት ሙያ በተለያዩ የግል የህትመት ሚዲያዎች ውስጥ መሥራቷን “Ethiopian Review” ለተባለ ድረገፅ  በሪፖርተርነት እንድትሠራ በአርቲስት ደበበ እሸቱ አገናኝነት ሥራ መጀመሯንና ከኤልያስ ክፍሌ ጋር የነበራትም ግንኙነት የሪፖርተርነት ብቻ መሆኑን፤ ለምትሠራበትም ደመወዝ እንደሚከፈላት ተናግራለች፡፡ ኤልያስ ክፍሌ የሽብር ተግባር እንድፈፅምለት አሰማርቶኛል ብዬ ከተናገርኩ ከእስር እንደምፈታ፣ ያንን ሣላደርግ ብቀር ግን ከ20-25 ዓመት ሊደርስ የሚችል እስር እንደሚጠብቀኝ እየነገሩ አስፈራርተውኛል፡፡ ይህንን ሃሣብ ባለመቀበሌም ለ13 ቀናት ለብቻዬ በባዶ ክፍል ውስጥ እንድታሰር አድርገውኛል ስትልም ተከሳሿ ተናግራለች፡፡ ተከሳሿ በመከላከያ ማስረጃነት ያቀረበቻቸው የሰው ምስክሮች ችሎት ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ የ5ኛ ተከሳሽ ጠበቃ የሙያ ምስክርነታቸውን እንዲሰጡላቸው ያቀረቧቸውን ዶ/ር መራራ ጉዲና እና ዶ/ር ያዕቆብ ወ/ማርያም ፍ/ቤቱ ምን ዓይነት የሙያ ምስክርነት እንደሚሰጡላቸው ሲጠይቋቸው፤ ሁለቱ ምሁራን የፖለቲካና የህግ ምሁራን በመሆናቸው የቀረበውን ክስ በዚህ መልኩ አይተውት ሙያዊ አስተያየታቸውን ይሰጡልኛል ብለዋል፡ ይህንን ሃሣብም ዐቃቤ ህግ በፅኑ ተቃውሞታል፡፡ ፍ/ቤቱም ችሎቱ የተቋቋመው  በህግ ጉዳዮች ላይ ማብሪሪያ ለመስጠትና ህጉን ለመተርጐም ሆኖ ሣለ ሌላ ህግ ተርጓሚ አካል እንደማያስፈልገው፤ ከዚህ በተጨማሪም ፍ/ቤቱ የተቀመጠው ተከሳሾቹ ፈፀሙ በተባለው ወንጀል ላይ የቀረቡ ማስረጃዎችን አጣርቶ ውሣኔ ለመስጠት እንጂ በፀረሽብርተኝነቱ አዋጅም ሆነ በሌሎች አዋጆች ላይ ምሁራንን አሰባስቦ ለማወያየት አይደለም በማለቱ ጠበቃው የሁለቱን የሙያ ምስክሮች ምስክርነት ትቼዋለሁ ብለው  ምስክሮቹ እንዲሰናበቱ አድርገዋል፡፡ የተከሳሽ ጠበቆች ምስክሮቻቸውን ማጠናቀቃቸውን ለፍ/ቤቱ ገልፀዋል፡፡ የአቃቤ ህግንና የተከሳሾችን የማጠቃለያ ሃሳብ ለመቀበልም ፍ/ቤቱ ቀጣይ ቀጠሮ ይዟል፡፡

 

 

Read 17770 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 15:26