Saturday, 16 August 2014 10:13

ማይክሮሶፍት ለ200 ሺ ኢትዮጵያውያን ስራ ፈጣሪዎች ድጋፍ ሊያደርግ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

     ታዋቂው ማይክሮሶፍት ኩባንያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር ለ200 ሺ ኢትዮጵያውያን ስራ ፈጣሪዎች ድጋፍ የሚያደርግ ፕሮጀክት ሊጀምር እንደሆነ ተገለፀ፡፡
ኦል አፍሪካ ዶት ኮም እንደዘገበው፤ የኩባንያው የምስራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ በስራ ፈጠራ ዘርፍ የሚካሄደውን ልማት ለማሳደግ ከልማት ፕሮግራሙ ጋር በተፈራረመው የትብብር ስምምነት፣ የተመድ የልማት ፕሮግራም በአገሪቱ ድጋፍ ለሚያደርግላቸው 200 ሺ ስራ ፈጣሪዎች ስልጠናና ክትትልን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ እገዛዎችን ያደርጋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት፤ የኩባንያው በጎ ፈቃደኛ ስራ አስፈጻሚዎች ለኢትዮጵያውያኑ ስራ ፈጣሪዎች በስትራቴጂና በማርኬቲንግ ላይ

ያተኮረ ሙያዊ ስልጠናና ድጋፍ የሚያደርጉ ሲሆን፤ ምርጥ ስራ ፈጣሪዎችን የመደገፍ፣ ለ “ፎርአፍሪካ ኢንሺየቲቭ” የፈጠራ ሽልማት እንዲታጩ የማገዝና የኩባንያውን አጋዥ ሶፍትዌር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማስቻል ስራ ያከናውናሉ ተብሏል።
ባለሙያዎቹ ከዚህ በተጨማሪም ስራ ፈጣሪዎቹ ለወደፊት በማይክሮሶፍት የአነስተኛና መካከለኛ ተቋማት ማዕከል በኩል ምርቶችንና አገልግሎቶችን እንዲለዋወጡና አለማቀፍ እውቅና እንዲያገኙ እገዛ እንደሚያደርጉ ዘገባው አስረድቷል፡፡
አዲሱ የትብብር ስምምነት፣ ማይክሮሶፍት ኩባንያ የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማፋጠንና የአገር በቀል ስራ ፈጣሪዎችን አቅም በመገንባት አህጉሪቱ በአለማቀፍ ደረጃ ያላትን ተወዳዳሪነት የማጎልበት ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀሰው “ፎርአፍሪካ ኢኒሺየቲቭ” የተሰኘ ፕሮግራም አካል እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

Read 1571 times