Saturday, 09 August 2014 11:58

በመጨረሻም ዋልያዎቹ ብራዚል መሄዳቸው አልቀረም

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋልያዎቹ የብራዚል ጉዞ  በ20ኛው ዓለም ዋንጫ  ተሳትፎ  ባይሳካም፤ ለሁለት ሳምንት ዝግጅት መሄዳቸው አልቀረም፡፡
በአሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ጥረት በብራዚል በካምፕ በአይነቱ የተለየ ዝግጅት የሚያደርጉት ዋልያዎቹ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ  ተሳታፊነት ብራዚልን በመርገጥ አስደናቂ ብቃት ያሳየችውን አልጄርያ ከመግጠማቸው በፊት ጥሩ ብቃት ላይ እንደሚደርሱ እየተነገረ  ነው፡፡ ከብራዚል ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ የሚያደርገው ብሄራዊ ቡድኑ  በቆይታው የሚያገኘው ጥቅም ያመዝናል። አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ቋሚ ተሰላፊ ቡድናቸውን ለመለየት ያሰቡ ይመስላል፡፡ ባሬቶ በሃላፊነቱ በቆዩባቸው ጊዜያት ቋሚ አምበል አለመሾማቸው ሙሉ ቋሚ ተሰላፊዎች አለመለየታቸውን ያመለክታል፡፡ ፍቅሩ ተፈራ፤ አበባው ቡጣቆ እና ፍፁም ገብረማርያም አምበሎች እንደሚሆኑ እየተገመተ ነው፡፡ አዳነ ግርማ፤ ሳላዲን ሰኢድና መስኡድ መሃመድም ለሃላፊነቱ ብቁ መሆናቸውም ይገለፃል፡፡ 19 አባላትን ያካተተው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  የመጀመርያው ልዑክ ረቡዕ ወደ ብራዚል ተጉዟል፡፡ ቀሪዎቹ ዛሬ ይበራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በብራዚል በሚኖረው የ14 ቀናት ቆይታ 33 አባላት ያሉት ልዑክ ይኖረዋል። በብራዚሊያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነገው ዕለት ከሰሜን ብራዚል ከመጣው ሬምዋ ከተባለ ክለብ ይጫወታል፡፡ የዛሬ ሳምንት ደግሞ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ጨዋታ አስተናግዶ በነበረው የማኔ ጋሪንቻ ስታድዬም ሁለተኛውን ጨዋታ ያደርጋል፡፡  ከ2 ሳምንት በኋላ  ደግሞ ሬዮ ግሬምዬ ከተባለ ክለብ ጋር ሶስተኛውን የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል፡፡ ሦስቱም የብራዚል ክለቦች በአገሪቱ የክለብ ውድድር በ4ኛ ዲቪዚዮን የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ጨዋታዎቹ አቋምን ከመፈተሽ ባሻገር ተጫዋቾቹን ለማስተዋወቅ ጥሩ እድል እንደሚፈጥር አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ተናግረዋል፡፡
በ2015 እኤአ ላይ ሞሮኮ ለምታስተናግደው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚካሄድ  የምድብ ማጣርያ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከአልጄርያ ጋር  ከመጫወቱ በፊት ቢያንስ ስምንት የወዳጅነት ጨዋታዎች ሊያደርግ ይችላል፡፡ ዋልያዎቹ ባለፈው ሰሞን  በሉዋንዳ ላፓላንካ ኔግራስ ከተባለው የአንጎላ ብሄራዊ ቡድን ጋር በመጀመርያ የወዳጅነት ጨዋታቸው ተገናኝተው 1ለ0 ተሸንፈዋል፡፡
በሉዋንዳ 11 ዲ ኔቨምብሮ ስታድዬም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አንጎላ ያሸነፈችው ፍሬዲ የተባለ ተጨዋች በ16ኛው ደቂቃ ላይ ባገባት ብቸኛ ግብ። የአንጎላው ፕሬዝዳንት ጆሴ ኤድዋርዶ ዶሳንቶስ የክብር እንግዳ ነበሩ፡፡
ከብራዚል መልስም  በነሀሴ ወር ሁለት የደርሶ መልስ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ፈርኦኖቹ ከተባለው የግብፅ ብሄራዊ ቡድን ጋር ለማድረግ ቀጠሮ መያዙም አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 2 የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታው ጳጉሜ 2 ላይ በአዲስ አበባ ስታድዬም ከአልጄርያ  ይገናኛል፡፡ አልጄርያና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ እና ዋና ውድድሮች 6 ጊዜ ተገናኝተዋል። እኩል አንዴ ተሸናንፈው በ4 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል፡፡ በምድብ 2 ከአልጄርያ፤ ከማሊ እና ከኢትዮጵያ ጋር ማጣርያ የምትገባው አራተኛ ቡድን ማላዊ ሆናለች፡፡ ማላዊ ምድቡን የተቀላቀለችው በሁለተኛ ዙር ቅድመ ማጣርያ ቤኒን ጥላ በማለፍ ነው፡፡
በተያያዘ ዜና የሴካፋ ዋና ፀሃፊ ኒኮላስ ሙንሶኜ በሞሮኮው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመካከለኛው እና የምስራቅ ዞን አንድ ተወካይ መኖሩ አይቀርም ብለዋል። ከዞኑ አራት ቡድኖች በምድብ ማጣርያው የሚካፈሉ ሲሆን ኢትዮጵያ እና ሱዳን በቀጥታ ወደ ምድብ ሲገቡ በቅድመ ማጣርያ ያለፉት ደግሞ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በማጣርያ  በሜዳዋ በምታደርጋቸው ጨዋታዎች ባለፈው ሁለት ዓመት ያሳየችው ብቃት ለጥንካሬዋ ምክንያት እንደሚሆን ኒኮላስ ሙንሶኜ ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከወራት በኋላ የመካከከለኛው እና ምሰራቅአፍሪካ ሻምፒዮና አዘጋጅ እንደሆነች ይታወቃል።

Read 1622 times