Saturday, 09 August 2014 11:55

አሜሪካ የደህንነት መረጃዎቼን የሚያወጣ ሌላ መንታፊ መጥቶብኛል አለች

Written by 
Rate this item
(4 votes)

         ቁልፍ መረጃዎችን እያወጣ በዓለማቀፍ ደረጃ ክፉኛ ሲያሳጣት የከረመውን ኤድዋርድ ስኖውደን የተባለ ግለሰብ አሳድዳ ለመያዝና ለመፋረድ ደፋ ቀና ማለቷን የቀጠለችው አሜሪካ፣ አሁን ደግሞ ከእሱ የባሰ የብሄራዊ ደህንነት መረጃዎቼን እየዘረፈ በማውጣት ጉድ የሚሰራኝ ሌላ ሚስጥር መንታፊ ግለሰብ መጥቶብኛል ስትል ባለፈው ረቡዕ በይፋ መናገሯን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
ስኖውደን የሚያወጣቸውን መረጃዎች እያተመ ለንባብ በማብቃት የሚታወቀው ዘ ኢንተርሴፕት የተባለ የአገሪቱ ጋዜጣ፣ ባለፈው ማክሰኞም ከዚህ ማንነቱ ያልተገለጸ ግለሰብ ያገኘውን የአገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት መረጃ ለንባብ ማብቃቱን ተከትሎ ነው የአሜሪካ መንግስት አሁንም ሌላ አዲስ መረጃ ዘራፊ እንደመጣበት ያመነው፡፡
ዘ ኢንተርሴፕት ለንባብ ያበቃው ጽሁፍ፣ በኦባማ የስልጣን ዘመን አሜሪካ በሽብርተኝነት ጠርጥራ የምትመዘግባቸው ግለሰቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱንና  የግለሰቦችን መረጃ በሚስጥር እያፈላለገች የመያዝና የመሰለል ስራዋን የበለጠ አጠናክራ መግፋቷን የሚያትት ነው ተብሏል፡፡
ጋዜጣው ግለሰቡ ያወጣቸው መረጃዎች አገሪቱ በሽብርተኝነት ጠርጥራ ከመዘገበቻቸው ዜጎች ውስጥ 40 በመቶ ያህሉ ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላቸው የሚያረጋግጡ ናቸው ማለቱን የጠቆመው ዘገባው፣ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ግን ጋዜጣው ወጡ የተባሉትን የሚስጥር መረጃዎች በአግባቡ ካለመረዳት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ መድረሱን  መናገራቸውን  አስረድቷል፡፡
ማንነቱ ባልተገለጸው ግለሰብ አማካይነት ወጡ ያላቸውን መረጃዎች ጠቅሶ ጋዜጣው እንዳስነበበው፣ አሜሪካ እስከ 2013 ነሃሴ ወር ድረስ 5ሺህ ያህል ዜጎቿን በከፍተኛ፣ 18 ሺህ ያህሉን ደግሞ በመለስተኛ ደረጃ በሽብርተኝነት ጠርጥራ የመዘገበች ሲሆን፣ 1ሺህ 200 የራሷን ዜጎች ጨምሮ ሌሎች ተጨማሪ 16 ሺህ የተለያዩ አገራት ዜጎችንም ‘በአየር መንገዶችና በድንበር አካባቢዎች ጥብቅ ፍተሻ ሊደረግባቸው የሚገቡ’ በማለት ስማቸውን መዝግባ ይዛለች፡፡
ግለሰቡ ያወጣቸው እነዚህ አዳዲስ መረጃዎች፣ ስኖውደን መረጃ በማውጣቱ ሰበብ ለእስር እንዳይዳረግ በመስጋት ከአሜሪካ አምልጦ ወደ ሩስያ ከኮበለለ በኋላ በነበረው ጊዜ በአገሪቱ ብሄራዊ የጸረ ሽብርተኝነት ማዕከል  የተዘጋጁ እንደነበሩ መረጋገጡን ጠቁሞ፣ ይህም መረጃዎቹን ያወጣው ሌላ ግለሰብ መሆኑን  የሚያሳይ ነው መባሉን ገልጿል፡፡ የአገሪቱ ባለስልጣናት የአዲሱን መረጃ መንታፊ ማንነት ለማወቅ ጥረት እያደረጉ ሲሆን፣ ግለሰቡ ምናልባትም በሚመለከታቸው የአገሪቱ የደህንነት መረጃ ተቋማት ውስጥ የሚሰራ ሊሆን እንደሚችል መገመቱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ግለሰቡ ምን ያህል የሚስጥር መረጃዎችን እንዳወጣም ሆነ መረጃዎቹ አፈትልከው መውጣታቸው በአገሪቱ መንግስት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በተመለከተ የአገሪቱ መንግስት ያለው ነገር ባይኖርም፣ መረጃዎቹ ‘ሚስጥራዊና ለውጭ አገራት መንግስታት ተላልፈው የማይሰጡ መረጃዎች’ በሚል  መለያ በአገሪቱ የደህንነት መረጃ ተመዝግበው እንደነበር ዘገባው ጨምሮ ጠቁሟል፡፡
አዲሱ መንታፊ ያወጣቸው መረጃዎች ስኖውደን ከዚህ በፊት ካወጣቸው የደህንነት መረጃዎች ጋር ሲነጻጸሩ በሚስጥራዊነታቸው አነስተኛ እንደሆኑ ዘገባው ጠቁሞ፣ ስኖውደን ካወጣቸው 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአገሪቱ የደህንነት መረጃዎች አብዛኞቹ ‘ጥብቅ ሚስጥሮች’ እንደነበሩ አስታውሷል፡፡

Read 5903 times