Saturday, 09 August 2014 11:53

የቻይናው ዚያኦሚ “አዲሱ ‘የስማርት ፎኖች’ ንጉስ ነኝ!” እያለ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የቻይናው የሞባይል ቀፎ አምራች የግል ኩባንያ ዚያኦሚ፣ የእነጋላክሲና አይፎን ዘመን አክትሟል፣ ከአሁን በኋላ ከማንም በላይ ከፍ ብዬ የምታየው የአገሬ ‘የስማርት ፎኖች’ ንጉስ እኔ ነኝ እያለ ነው፡፡
በአገረ ቻይና የስማርት ፎን ገበያ ዋነኛ ተፎካካሪው የነበረውን የደቡብ ኮሪያው ሳምሰንግ በዘንድሮው ሁለተኛ ሩብ አመት ለመጀመሪያ ጊዜ በሽያጭ ያስከነዳውና ተወዳጅነቱ እየጨመረ የመጣው ዚያኦሚ፣ ይህ ስኬቱ በአገሩ ምድር የስማርት ፎን ገበያ መሪነቱን እንዳስጨበጠው ሲኤንኤን ሰሞኑን ከሆንግ ኮንግ ዘግቧል፡፡
ከአራት አመታት በፊት የተመሰረተው የቻይናው ስማርት ፎን አምራች ዚያኦሚ፣ በአገሪቱ ገበያ ያለውን ድርሻ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፍጥነት በማሳደግና ባለፈው አመት ተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው የገበያ ድርሻ 240 በመቶ ጭማሪ በማድረግ በአሁኑ ወቅት 14 በመቶ ማድረሱ የተነገረ ሲሆን፣ በሩብ አመቱ ለገበያ ያቀረባቸው ስማርት ፎኖች ቁጥርም 15 ሚሊዮን መሆኑ ተዘግቧል፡፡
ዚያኦሚ በተጠቀሰው ጊዜ 97 በመቶ የሚሆነውን ምርቱን ለቻይና ገበያ ያቀረበ ሲሆን፣ የካፒታል አቅሙም ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱ ተነግሯል፡፡  
ሳምሰንግን ጨምሮ ዋነኛ ተፎካካሪዎች የነበሩት ሁዋዌ፣ ሌኖቮና ዩሎንግ በሩብ አመቱ በአማካይ 10 በመቶ የገበያ ድርሻ መያዛቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ዚያኦሚ በቻይና ቀዳሚውን የገበያ ድርሻ ቢይዝም ከአገር ውጭ እምብዛም እንደማይታወቅ አስታውሷል፡፡
ኩባንያው በአገር ውስጥ እያስመዘገበ ያለውን ስኬት በማስፋፋት በአለም አቀፉ የስማርት ፎን ገበያ ተወዳዳሪና መሪ የመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሰራ እንደሚገኝ የተገለፀ  ሲሆን፣ ይህን እቅዱን ለማሳካት በሚችልበት መንገድ ዙሪያ ባለፈው አመት ከጎግል ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋር የጋራ እንቅስቃሴ መጀመሩም ተዘግቧል፡፡
ዚያኦሚ ወደ አለማቀፉ የስማርት ፎን ገበያ ዘልቆ ለመግባትና ንግስናውን ድንበር ለማሻገር የጀመረውን ጉዞ፣ ምርቶቹን ወደ ሩስያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሜክሲኮ፣ ታይላንድና ቱርክ በመላክ ለመጀመር እንደተዘጋጀ ታውቋል፡፡
የኩባንያው ስማርት ፎኖች በአሁኑ የቻይና ገበያ በ130 ዶላር እየተሸጡ ሲሆን፣ ዋጋቸው ከአፕል ምርቶች ጋር ሲነጻጸር በአንድ ሶስተኛ ያነሰ እንደሆነ ተነግሯል፡፡


Read 1958 times