Saturday, 09 August 2014 11:50

የድረገጽ ሌቦች 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ፓስ ዎርዶችን ሰረቁ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የሩስያ ዜግነት ያላቸው አባላትን የያዘ አለማቀፍ የድረገጽ ሌቦች ቡድን የአሜሪካን ግዙፍ ኩባንያዎች ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ታላላቅ ድርጅቶችን፣ የንግድ ኩባንያዎችንና የግለሰቦችን የድረገጽ መረጃዎችና ፓስ ዎርዶችን (የሚስጥር ቁልፎች) መዝረፉን ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
ሆልድ ሴኪዩሪቲ የተባለውን ተቋም ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ቡድኑ ከ420 ሺህ በላይ በሚሆኑ የኩባንያና የግለሰብ ድረገጾች ላይ የፈጸመው ይህ የስርቆት ተግባር፣ በዘርፉ በአለም ዙሪያ የተፈጸመ ትልቁ የመረጃ ዘረፋ ነው፡፡ ዘራፊዎቹ 500 ሚሊዮን የሚሆኑ የኢሜይል አድራሻዎችን የሚስጥር ቁልፍ በርብረው እንዳገኙ የጠቆመው ዘገባው፣ መሰል ተግባር ከተፈጸመባቸው መካከልም በዓለማችን ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም ያላቸው ኩባንያዎች እንደሚገኙበት የሆልድ ሴኪዩሪቲን መስራች አሌክስ ሆልደን መናገራቸውን አስረድቷል፡፡
አስር ያህል አባላትን የያዘው ይህ የዘራፊዎች ቡድን ተቀማጭነቱን ያደረገው፣ ከካዛኪስታንና ከሞንጎሊያ ጋር በሚዋሰነው የሩስያ ደቡብ ማዕከላዊ አካባቢ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ አባላቱ በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
የቡድኑ አባላት የራሳቸውን የኮምፒውተር ፕሮግራም በመፍጠርና የድረገጾችን መረጃ በመስረቅ በሚያገኙዋቸው የሚስጥር ቁልፎች አማካይነት የኩባንያዎችንና የግለሰቦችን የመረጃ ልውውጥና ሚስጥር በእጃቸው እንደሚያስገቡ ተገልጿል፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ በበኩሉ፣ቡድኑ የዝርፊያ ስራውን በረቀቀ መንገድ ማከናወን ከጀመረ ጥቂት አመታት እንደሆነው ገልጾ፣ የሚስጥር ቁልፎችን በመዝረፍ የሚያገኛቸውን የኩባንያዎችና የግለሰቦች ሚስጥሮች መደራደሪያ በማድረግ የገንዘብ ምንጭ አድርጎ እንደሚጠቀም ተነግሯል፡፡

Read 2424 times