Saturday, 09 August 2014 11:37

ማራኪ አንቀጽ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

“..ምን ልርዳችሁ? ምን ፈልጋችሁ ነው?” አሉ ግራ ተጋብተው፡፡
ተዘጋጅተንበት ስለነበር ሁላችንም በአንድ ድምፅ
“ዜግነት!!! ዜግነት!!!...ነፃነት!!...አባት ሀገር!!...አባት ሀገር!!! Our father land!!...Father land!!!” እያልን መጮህ ጀመርን፡፡
ወንበር ላይ ወጥቼ እያጨበጨብኩ፤
“ነፃነት!! ዜግነት!! ነፃነት!! ዜግነት!!...” በማለት መዝፈን ስጀምር ሁሉም እኔን እየተከተሉ መዝፈንና ግድግዳ እየደበደቡ ሲረብሹ፣ አቶ ተስፋዬ የሚሰማቸው ስላጡ ቢሮውን ለቀው ወጡ፡፡ የኤምባሲው ሰራተኞች በሙሉ ደንግጠው ሲመለከቱን ጭራሽ ባሰብን፡፡ ከአስር ደቂቃ በኋላ አቶ ተስፋዬ አምባሳደሩን፣ ቆንስሉንና ሌሎች ነጭ ሆላንዳዊያንን አስከትለው መጡ፡፡
“እባካችሁ ተረጋጉና የምትፈልጉትን ንገሩን፡፡” ቢሉንም እኛ ግን መጮሃችንን ቀጠልን፡፡
“እንዲህ መሆናችሁ ጥቅም የለውም፡፡ ይልቁንስ አምባሳደሩ አጠገባችሁ ስለሚገኝ ይህን ዕድል ተጠቅማችሁ ጥያቄያችሁን ብታቀርቡ ይሻላል” አሉ አቶ ተስፋዬ፡፡
ይህን ስንሰማ ቀስ በቀስ ተረጋጋን፡፡ ወዲያውኑ አምባሳደሩ ንግግር ጀመረ፡፡ አቶ ተስፋዬ የአምባሳደሩን ንግግር ማስተርጐም ሲጀምሩ ከቆምኩበት ወንበር ላይ ዘልዬ ወረድኩ፡፡
“አቶ ተስፋዬ እንዲያስተረጉምልን አንፈልግም። እንግሊዘኛ ቋንቋ የሚችል ሰው አለን፡፡ አንተ እኛን ለማስፈራራት ብቻ ነው የምትፈልገው፡፡” ብዬ ጮህኩኝ።
ኢዩኤል በእንግሊዝኛ መናገር ሲጀምር ፀጥታ ሠፈነ፡፡
“እኛ የተረሳን የሆላንድ ተወላጆች ነን። አባቶቻችን ጥለውን ጠፍተዋል፡፡ ስለዚህ ወደ ሀገራችን መሄድ እንፈልጋለን! ጥያቄያችን ይህ ነው፡፡” አለና በእንግሊዝኛ የተናገረውን ወዲያው በአማርኛ ለእኛ ተረጐመልን፡፡ አምባሳደሩ የተናደደ መሰለ፡፡
“የሆላንድን ዜግነት በጉልበት ማግኘት ትችላላችሁ?! ሁላችሁም ከዚህ ቢሮ አሁኑኑ ለቃችሁ ውጡ! በፖሊስ ሃይል ተገዳችሁ ከመውጣታችሁ በፊት አሁኑኑ በሰላም ውጡ!” ብሎ ድምፁን ከፍ አድርጐ ተናገረ፡፡
በመቀጠል ቆንስሉ ወደ እኛ ተጠግቶ “በሉ ውጡ!” እያለ ሲንጐራደድ፣ ሁሉም ልጆች “ምን እናድርግ?” በሚል ስሜት ተመለከቱኝ፡፡
“በለው! በለው!” አልኩና ከባድ ግርግር አስነሳሁ። ሰለሞን ታይሰን አይኑን አፍጥጦ ቆንስሉን ሲጠጋው ቆንስሉ ወደ ውጪ ሮጠ፡፡
“ነፃነት! ዜግነት! ነፃነት! ዜግነት! ዜግነት!” የሚል ጩኸት ተጀመረ፡፡
ሁሉም ሸሽተውን በርቀት ይመለከቱናል። ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ አምስት የታጠቁ የኢትዮጵያ ፖሊሶች የእንጨት ዱላና ካቴና ይዘው መጡ፡፡ አምስቱም ፖሊሶች ተከታትለው ገብተው፤
“ፀጥ በል! ፀጥ በል! ለምንድነው የምትረብሹት?! ተነስ ውጣ! ውጣ!” እያሉ ያመናጭቁን ጀመር፡፡
ሳያስቡት ዘልዬ መጀመሪያ ወደኛ የተጠጋውን ፖሊስ ሁለቴ በቦክስ ስመታው፣ ተንገዳግዶ ጥግ ያዘ። ሰለሞን ሮጠና ጥግ የያዘውን ፖሊስ እግሩን ዘርጥጦ ጣለውና፣ በጉልበቱ ግንባሩን መቶት ራሱን አሳተው። የቀሩት ፖሊሶች ራሳቸውን ለመከላከል በያዙት ዱላ ሰለሞንን ፈነከቱት፡፡ በግብግቡ ውስጥ እንደምንም ብለው የተመታውን ፖሊስ ከቢሮ ጐትተው አወጡት። በመስታወት ውስጥ ቆመው ጠቡን የሚያዩት አምባሳደሩ፤ ቆንስሉና ሌሎችም ነጭ ሆላንዳዊያን በኛ ቁርጠኛነት ደንግጠዋል፡፡
በቢሮው ውስጥ የነበረውን አግዳሚ ወንበር አንስተን ለስድስት ተሸከምነውና ፊት ለፊት የሚያዩበትን መስታወት ለመስበር በወንበሩ መምታትና መደብደብ ጀመርን፡፡ በአምስተኛው ምት መስታወቱ ፈረሰ፡፡ ቢሮው ውስጥ የነበሩት አምባሳደሩ እና ሌሎች የኤምባሲው ሰራተኞች ቢሮውን ጥለው ከፖሊሶች ጋር ተቀላቀሉ። እንደማይቋቋሙን ሲረዱ ከሃያ በላይ የሚሆኑ ፖሊሶች አስጨምረው ከብዙ ትግልና መስዋዕትነት በኋላ ስለተዳከምን፣ ሁላችንንም በካቴና አስረው እየጐተቱ እና በዱላ እየቀጠቀጡ፣ በፖሊስ መኪና ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ስንደርስ ካቴናችንን እየፈቱ፣ አንድ ቤት ውስጥ አስገብተው ቆለፉብን፡፡ ሁላችንም በጣም ደክሞን ስለነበር ወለሉ ላይ በጀርባችን ተዘርረን ተኛን፡፡ ማታ ራት አቀረቡልን፡፡ በነጋታው ሁላችንም ሻወር ወስደን እስር ቤት ውስጥ መጫወትና ያደረግነውን ትግል ጀብዱ፣ ድፍረት፣ ቆራጥነት ስናወራ፣ የፖሊስ ጣቢያው መርማሪዎችና መቶ አለቃው በሩን ከፍተው መሃላችን ቆሙ፡፡ ለሁለት ደቂቃ አዩንና
“አመፀኛው ክልስ የታል? የዚህ አመጽ መሪ አንተ ነህ?” ብሎ አፈጠጠብኝ፡፡ የቀሩት መርማሪ ፖሊሶች “አመፀኛው ክልስ ተነስ!! አመፀኛ!!” እያሉ በጥፊ እየመቱኝ፣ ለምርመራና ጥየቃ የመቶ አለቃው ቢሮ አስገቡኝ፡፡
“አመፀኛው ክልስ ስምህ ማነው” አለ መቶ አለቃ፡፡
“ዳንኤል ሁክ” አልኩት…
(ከዳንኤል ሁክ “አመፀኛው ክልስ”
እውነተኛ ታሪክ መፅሃፍ የተቀነጨበ -2005 ዓ.ም)

Read 6498 times