Saturday, 09 August 2014 11:35

የአዳማ ከተማ የ193 ሚ. ብር የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት ይፈራረማል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

            በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን የምትገኘውን የባኮ ከተማ በ9 ወር ጊዜ ውስጥ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ያደረገው “ሚና ወተርስ”፤ በውሃ እጥረት የምትታማውን የአዳማ ከተማን የውሃ ችግር ለመፍታት ከኦሮሚያ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ጋር በዛሬው እለት የ193 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፈራረማል፡፡
ከ30 ሺህ በላይ ህዝብ እንደሚኖርባት በሚነገርላት በባኮ ከተማ የ27 ሚሊዮን ብር የውሃ ማጣራት ፕሮጀክት ከ4 ወር በፊት ተጠናቆ የንፁህ ውሃ አቅርቦት ማግኘት ተጠቃሚ መሆን የጀመረች ቢሆንም በሃገራችን የመጀመሪያው ነው የተባለው ይህ አዲስ የውሃ ማጣራት ቴክኖሎጂ በይፋ የተመረቀው ባለፈው ማክሰኞ  ነበር፡፡
ፕሮጀክቱ በአይነቱ የተለየ “ኮንቴነራይዝድ ትሪትመንት ፕላንት” ግንባታ ሲሆን ሁሉም የውሃ ማጣራት ሂደቶች ተጀምረው የሚጠናቀቁት በአንድ ኮንቴነር ውስጥ በተገጠሙ ማሽኖች ነው፡፡ ይሄም የግንባታ ወጪንም ሆነ ጊዜ እንደሚቆጥብ የ “ሚና ወተርስ” የምስራቅ አፍሪካ  ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ ጌታነህ ተናግረዋል፡፡
የባኮ ፕሮጀክትን በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ቢታቀድም እቃዎችን ወደ ሃገር ውስጥ ከማስገባት ጋር በተያያዘ መጓተት 9 ወር ሊፈጅ መቻሉን የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ፤ በሌላው ዓለም በስፋት የሚሰራበት ይሄ ቴክኖሎጂ በአጭር ጊዜና በቀላል ወጪ 50 ሺህ የሚደርስ ህዝብን የውሃ ተጠቃሚ የሚደርግ ነው ብለዋል፡፡ በሃገራችን የወንዝ ውሃን ለንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ለማዋል የሚገነቡት የውሃ ማጣሪያ ጣቢያዎች ከ3-6 ዓመት እንደሚወስዱ አቶ መንግስቱ አስታውሰዋል፡፡
ኩባንያው አዲሱን የውሃ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ ከ3 ዓመት በፊት የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥቶ በውሃ ማጣራት ስራ ፕሮጀክት ላይ መሰማራቱን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፤ የመጀመሪያ ማሳያ የሆነው የባኮ ፕሮጀክት በየቀኑ 2400 ሜትሪክ ኪዩብ የተጣራ ውሃ እያመነጨ ለመጠጥ ያቀርባል ብለዋል። ኩባንያው በተጓዳኝ የበጎ አድራጎት ስራዎችን እንደሚሰራ ገልፀው፤ በወንጂ ከተማ በየቀኑ 500 ሜትር ኪዩብ ውሃ እያጣራ ለከተማው የሚያቀርብ የማጣሪያ ጣቢያ የበጎ አድራጎት ሥራው አካል ሆኖ በነፃ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡ የባኮው ፕሮጀክት ግን ከኦሮሚያ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በተፈፀመ የ27 ሚሊዮን ብር ስምምነት መከናወኑን ገልፀዋል። ሥራ አስኪያጁ አክለውም፤ ፕሮጀክቱ እስከ 50 ዓመት እንዲያገለግል ታስቦ የተከወነ ነው ብለዋል፡፡  “ሚና ወተርስ” በዛሬው ዕለት የአዳማ ከተማ የውሃ አቅርቦትን በእጥፍ ለማሳደግ የሚያስችል ፕሮጀክት በ18 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ከኦሮሚያ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ጋር የ193ሚ. ብር ስምምነት የሚፈራረም ሲሆን ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በቀን 22ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ የሆነውን የከተማዋን የውሃ አቅርቦት ወደ 44 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ያደርሰዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 1736 times