Saturday, 09 August 2014 11:29

ከዕለታት አንድ ቀን…

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(2 votes)

“ዕውቅ ባለሙያዎች ያላት አገር ድሃ አይደለችም”

(ከወዳጄ ከፕሮፌሰር ሽፈራው ብርሃኑ (“ሽፌ ወይም “ሺፍ”) ጋር ያደረኩት ቆይታ)
ከዕለታት አንድ ቀን…አንድ ልዑል በዕደማርያም ላቦራቶሪ ት/ቤት (Prince Bede Mariam Laboratory School) የሚባል ት/ቤት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ቅፅር ግቢ ውስጥ ይኖር ነበረ፡፡ እዚህ ት/ቤት የሚገቡ ከየጠቅላይ ግዛቱ ከ11ኛ ወደ 12ኛ ያለፉ ምርጥ ምርጥ ተማሪዎች ናቸው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን…እንደሌላው ዓመት ሁሉ ብዙ ጐበዝ ተማሪዎች ወደ ልዑል በዕደማርያም ላቦራቶሪ ት/ቤት ገቡ፡፡
ከብዙዎቹ ተማሪዎች ውስጥ ዛሬ አንቱ የተባሉ የሀገሪቱ ታላላቅ ሰዎች፤ ሚኒስትር የሆኑ፣ የአገር መሪ የሆኑ፣ የፖለቲካ ሰዎች የሆኑ፣ የተማሩ የተመራመሩ…ይገኙባቸዋል፡፡ እነ በየነ ጴጥሮስ፣ እነ ዓለም ሰገድ ገ/አምላክ…እነ ገብሩ አሥራት፣ እነ ስዬ አብርሃ፣ እነ አርከበ ዕቁባይ እነጌታቸው ማሩ፣ እነ አበበ ገ/ዮሐንስ፣ እነ ፃድቃን ገ/ትንሣዔ ምኑ ቅጡ… ይሄ ት/ቤት የአገር ፖለቲካና ፖለቲከኛ መፈልፈያ ኢንኩቤተር ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ እንደ ጄኔራል ዊንጌት ት/ቤት መሆኑ ነው፡፡ ጄኔራል ዊንጌት ት/ቤት እነ መለስ (ለገሠ) ዜናዊን፣ እነ ኃይሌ አሰግዴን…ከዕለታት አንድ ቀን እንዳፈራው ማለት ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን እኔም ልዑል በዕደማርያም ላቦራቶሪ ት/ቤት (በአጭሩ “ላብ - ስኩል”) ገባሁ፡፡ ከአፄ ገላውዴዎስ ት/ቤት ከናዝሬት ነው የመጣሁት።
በዚያው ከዕለታት አንድ ቀን ሽፈራው ብርሃኑም (የዛሬው ፕሮፌሰር - የሂሳብ ሊቅ) ልዑል በዕደማርያም ላቦራቶሪ ት/ቤት ገባ፡፡ እሱ የመጣው ከጄኔራል ዊንጌት ት/ቤት ነው፡፡ መለስ እና እሱ አንድ ጠረጴዛ (ዴስክ) ላይ ይቀመጡ የነበሩ ናቸው። ዕጣ - ፈንታ፣ ትግል ወይም ትምህርት ወዴት እንደሚወስዳቸው ሳያውቁ አንጐላቸውን ብቻ ተማምነው የነበሩ ተማሪዎች የነበሩ ይመስለኛል፡፡ ዘመኑ እንደዚያ ያሉ ተማሪዎችን ይወልድ ነበረና፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን… ዊንጌት ት/ቤት እና በዕደማርያም ት/ቤት በእንግሊዞች የሚመሩ ነበሩ፡፡ በዚህ ምክንያት ሽፈራው ከእንግሊዝ ወደ እንግሊዝ ነው የመጣው ማለት ነው፡፡ መለስም እንደዚያው ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን…የእኔ የናዝሬቱ (የአዳማ) አፄ ገላውዴዎስ ት/ቤት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያስተምር (Anglophone ነበር) እንጂ በአበሻ የሚመራ ት/ቤት ነበር፡፡ ስለዚህ እኔ ከአበሻ ወደ እንግሊዝ ነው የመጣሁት ማለት ነው፡፡ እኔና ሽፈራውን (“ሽፌ” ነው የምንለው ጓደኞቹ) የሚያመሳስለን እንግዲህ አንግሎፎንነታችን ነው ማለት ነው (የኦክስፎርድ ዲክሽነሪ አንግሎፊል (anglophile) እንግሊዝ - ወዳድ፣  Anglophobe (እንግሊዝ - ጠማጅ ) Anglophone (እንግሊዝ - አፍ ተናጋሪ) እያለ ይተነትናል)
በዚያን ዘመን የነበርን (በ1960ዎቹ) ተማሪዎች እንግሊዞችን ካሁን የበለጠ ለማወቅ ዕድል ነበረን ማለት ነው፡፡
አሰፋ ጫቦ የተባለ ወዳጄ ከዕለታት አንድ ቀን ሲፅፍ “አበሻ ምንም ጽሑፍ ሲጽፍ ከአዳምና ሄዋን ቢጀምር ደስ ይለዋል” ብሎ ነበር፡፡ እኔም አሁን ያደረግሁት ያንኑ ይመስለኛል፡፡ እና ከዕለታት አንድ ቀን ከሽፌ ጋር ላብ - ስኩል ተገናኘን፡፡
ሽፌ ዛሬ የሂሳብ ሊቅ ቢሆን አይገርመኝም። የሚወጣ እንጀራ ገና ከምጣዱ ያስታውቃልና። ሽፌና ሂሳብ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽ ናቸው። ከዕለታት አንድ ቀን እንደዚያ ነበሩ፡፡ ዛሬም ያው ናቸው። እንዲያውም አሁን የአንድ ሣንቲም አንድ ገጽ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ሽፌ በዩኒቨርሲቲ (በላብ ስኩል) ቋንቋ ሰቃይ ነበር፡፡ ከትምህርት ድርና ማግ የተሠራ የቀለም ሸማ ነው፡፡
የከዕለታት አንድ ቀኑ ሽፌ ዛሬ አንቱ የተባለ የሂሳብ ፕሮፌሰር ነው፡፡ ፔንሲልቫኒያ ቴምፕል ዩኒቨርሲቲ! ብዙዎች የትናንት የቀለም ክሂሉን የሚያውቁ “መጠርጠሩስ!”  የሚሉ ይመስለኛል፡፡
ዩኒቨርሲቲ ከገባን በኋላ፤ እኛ ፈተና ሲደርስ ስንራወጥ፣ ስንንደፋደፍ፣ ከዶርም ላይብረሪ፣ ከክፍል - ላብራቶሪ ስንሮጥ፤ ሽፌ ሁለት እጁን እኪሱ ከቶ፣ ወደመዝናኛ ሰፈር ነው የሚሄደው፡፡ እሱ አጥንቶ ጨርሶ የቀለም ሸማውን አጥቦ ተኩሶ ይዘንጣል፡፡ አዳሜ ገና ለጥናት፤ “የስድስቱ ቀን ጦርነት” እያለ ይራኮታል፡፡ ይሄን ያየና ያወቀ የሽፌ መድረሻ አይጠፋውም፡፡ ሽፌን “ይሄን አሳየኝ” “እስቲ እቺን ጥያቄ ሥራልኝ!” የሚለው ተማሪ ስፍር ቁጥር የለውም፡፡ ስለዚህ ሽፌ ከዕለታት አንድ ቀን እንደተማሪ ሳይሆን እንደአስተማሪ የተማረ ነው፡፡
ዛሬማ አንደኛውን ለይቶለት ፕሮፌሰር ሆኗል!! አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በየጊዜው ይመጣል፡፡ ይመላለሳል፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (በዱሮ ት/ቤቱ) በሂሳብ የፒኤችዲ ፕሮግራም ጀምሯል፡፡ እንዴት? ለምን? ከማ ጋር? ወዘተ ዛሬ በቆታይችን ወዳጄ እንዲህ ብሎኛል፡፡ ለምን መጣህ ዩኒቨርሲቲ? ምን ጐሎት ልትሞላ መጣህ?
ሽፈራው ብርሃኑ ነህ ብዬ እገምታለሁ? አልኩት በፌዝ፡፡
አይ ስሜ አልተለወጠም፡፡… ዛሬ የመጣሁበት ምክንያት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማቴማቲክስ ዲፓርትመንትን ለመርዳት ነው፡፡ በየክረምቱ ወራት የምመጣው ይሄንኑ ዲፓርትመንት እንዳቅሜ ለማገዝ ነው፡፡
በምን በኩል ነው የምትረዳው?
በአገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ተከፍተዋል፡፡ አንድ አሥር በሚሆኑ ቦታዎች በማቴማቲክስ የማስተርስ ዲግሪ ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን በማስተርስ ደረጃ ለማስተማር በቂ ዕውቀትና ብቃት ያላቸው ሰዎች በጣም በጣም ጥቂቶች ናቸው። ማለትም በፒኤችዲ ደረጃ ያሉ፣ የሰለጠኑ የሂሳብ ባለሙያዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም እነዚህን ሰዎች የሚያሰለጥኑ ፒኤችዲ ያላቸው ሰዎችን ለማፍራት ነው፡፡
ፒኤችዲ ብቻ ነው የሚበቃው ሰዎቹን ለማፍራት?
ፒኤችዲ ያላቸውም ሰዎች ብቻ በቂ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ በሠለጠነው ዓለም ከዚያም በላይ እንደሚያስፈልግ ነው የሚታመነው፡፡ እንደ መጀመሪያ ነው የሚታየው ፒኤችዲ፡፡ ከዚያ በኋላ ምርምር ያደረጉ፣ አዲስ ነገር ሠርተው ያሳተሙ፣ በታወቁ ጆርናሎች ያወጡ፣ እንደዛ ያሉ ሥራዎች የሠሩና በየጊዜው ምርምር የሚያደርጉና ለአዳዲስ ችግሮች መፍትሔ ያገኙ ሰዎች ናቸው የሚያስፈልጉህ፡፡ እዚያ ለመድረስ በሀገራችን ደረጃ ጊዜ ይወስዳል፤ ግን በዛም በኩል አስተዋጽኦ ለማድረግ እንዲረዳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ፕሮግራም መነሻ ይሆን ዘንድ ጀመርን፡፡
ነብሱን ይማረውና፣ ከድሮ አስተማሪያችን ከዶክተር ደምሱ ገመዳ ጋር ነው ይህን ያደረግነው፡፡
መቼ ነው ይሄ?
በፈረንጆች 2007 ዓ.ም፡፡ እዚህ ስመጣ ከሱ ጋር ተነጋግረን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ብቃት ያላቸውንና ሥልጠና ያገኙ የሂሳብ ባለሙያዎችን (ማቴማቲሻኖችን) ለማፍራት ተስማማን፡፡ እጥረቱን ለመቋቋም ምናልባት መፍትሔ ሊሆን የሚችለው እዚሁ የፒኤችዲ ፕሮግራም መጀመር ነው ተባባልን።
እንደግለሰብ (Individual) ነው ከሱ ጋር ያወራችሁት ወይስ እንደ ተቋም ነው፡፡ ደሞስ ለምን ዶክተር ደምሱን መረጥክ? የዱሮ አስተማሪያችን ስለነበረ ነው?
አየህ እሱ የዩኒቨርሲቲው ፖስት ግራጁኤት ፕሮግራም ዳይሬክተር ሆኖ አገልግሏል፤ በማቴማቴክስ ዲፓርትመንት ለብዙ ጊዜ ሊቀመንበር ሆኖ ሰርቷል፤ መጨረሻው ላይ የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንትም ነበረ… ለዲፓርትመንቱ ብዙ ያዋጣ ሰው ነው፤ ብዙ ይጨነቅ የነበረ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ በኃላፊነት ይመለከተዋል፡፡
አንተስ በምን ደረጃ ቦታ ነው የቀረብከው?
እኔ ደግሞ ለብዙ ዓመታት ከዚህ ማስተርሳቸውን ያገኙ ሰዎች አሜሪካ እየመጡ ለፒኤችዲ አቸው እንዲማሩ፤ አድርጌያለሁ፡፡ እስከዛሬ ወደ 17 የሚሆኑ ፒኤችዲ አግኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያን በዚህ በኩል መርዳት እንደሚፈልግ ያውቃል፤ ስለዚህ የጋራ የሆነ ጉዳይ ላይ ያገባናል ባይ ሆነን ነው የተነሳነው። ሆኖም የፒኤችዲውን ፕሮግራም ለመጀመር ሌላ ችግር መጣ፡፡ ይኸውም ፕሮግራሙ ይኑር ያልነው የማስተርስ ፕሮግራምን በየቦታው የሚስተምሩ በቂ ስልጠና ያላቸው ሰዎች የሉም ብለን ነው፡፡ ከዚያ በቂ ስልጠና ያላቸው ሰዎች ከሌሉ “የፒኤችዲ ፕሮግራሙን ራሱንስ ማን ሊያስተምር ነው?” የሚል ጥያቄ መጣ፡፡ (ሳቅ) ስለዚህ እኔና ከዚህ በፊት ከእኔ ጋር ቴምፕል ዩኒቨርሲቲ ተምረው ፒኤችዲ የያዙ ኢትዮጵያዊያን እና ሌሎች የማውቃቸው ፈረንጆች እየመጡ፣ እዚህ ክረምት ክረምት ቢያስተምሩና ካሉበት ፕሮግራሙን ቢሰጡ ይቻላል ብለን ጀምረን፤ በዚያ መሰረት ነው እንግዲህ እኔም ለሶስተኛ ጊዜ ለማስተማር የመጣሁት፡፡
ብቻህን ነው?
አራት ተማሪዎች አሉ፡፡ ከዚህ በፊት ቴምፕል ዩኒቨርሲቲ የጨረሱ፡፡ አሁን እኔ አስተምሬ ጨርሻለሁ.. ልመለስ ነው፡፡ እነሱ እያስተማሩ ናቸው። በቀን ለሶስት ሰዓት ያህል ጊዜ ነው የምናስተምረው። እኔ ለአራት ሳምንት ያህል አስተምሬያለሁ፡፡ ሲደመር አንድ ሴሚስተር ተኩል ያህል ይሆናል፡፡ ባጭሩ ይህን የፒኤችዲ ፕሮግራም ለመርዳት፣ ተማሪዎች ለማሰልጠን ነው የምመላለሰው፡፡
ይሄ በዓይነቱ ልዩ አሰራር ነው ወይስ ዩኒቨርሲው ውስጥ የተለመደ ነው ብለህ ታስባለህ?
የመጀመሪያው አሰራር ይመስለኛል… አሁን ባዮሎጂም፣ ኬሚስትሪም እዚሁ ነው የሚያሰለጥኑት። በቂ ሰዎች አፍርተዋል፡፡ ብዙ ሪሰርችም ይሰራሉ፡፡ ሂሳብ ውስጥ ያለው ችግር አየህ በቂ ሰዎች የሉንም! ስለዚህ ነው ይሄንን ዘዴ የፈጠርነው፡፡ ሰዎቹ እዚህ ከሌሉ ውጪ ያሉት እዚህ መጥተው የሚቆዩ ካልሆኑ… ሌላ ቢቀር ለተወሰነ ጊዜ እንኳ እዚህ ቢመጡና ቢያገለግሉ በሚል ነበር የጀመርነው፡፡ አንድ ልጅ ከሁለት ወር በፊት ፈፅሟል፡፡ አንዲት ደግሞ ከጥቂት ወራት በኋላ ዶክትሬቱን ትፈፅማለች፡፡ በትምህርታቸው ደህና ደረጃ ሲደርሱ፤ እኛ ያለንበት ት/ቤት መጥተውም እንዲቀጥሉ እናደርጋለን፡፡ ሶስት ወር አራት ወር እየቆዩ ያጠናሉ፡፡ እኛን የማግኘት፣ ከእኛ ጋር የመስራት ዕድሉ ይኖራቸዋል፡፡ ቆይተው እዚህ ይመለሳሉ፡፡ አንድ ሰባት የሚሆኑ አሜሪካ፣ ጀርመን መጥተው የተመለሱ አሉ፡፡
በምን ገንዘብ ወደዚያ ይመጣሉ?
የስዊድን መንግስት ለዲፓርትመንቱ የሰጠው እርዳታ አለ፡፡ ያንን እርዳታ ይጠቀማሉ፡፡
አንተስ ራስህ እንዴት ነው ፈንድ የምትደረገው?
በስዊድን መንግስት እርዳታ በተገኘው ገንዘብ ነው፡፡ እስካሁንም … አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፡፡ ዘንድሮ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው የተገኘው…የምንሰራውን ስራ!  ጥቅሙን ስለተገነዘበ ለእኔና አብረውኝ ለመጡት ፕሮፌሰሮች! .. አሁን ስዊድን ከሩዋንዳ ጋር ፕሮግራም አለው፡፡ በማትስ ተማሪዎች እየወሰደ ለፔኤችዲ ያሰለጥናል፡፡ ግን የእኛን ፕሮግራም ሲሰሙ፣ የእኛ ፕሮግራም የበለጠ ለተማሪዎች ሊያመች ይችላል የሚለውን አዩ፡፡ በተለያዩ ዘርፎች የሚሰራበት ስለሆነ ከእነሱ እንማር ብለው ልምድና ትምህርት እንዲያገኙ እዚህ ሰዎች ላኩ፡፡ ባለፈው ሳምንት ተመልሰው ሄዱ፡፡ በዛውም አዲስ ዓይነት ትብብር ለመፍጠር ነው፡፡ ምናልባት እርዳታም ይገኝ ይመስለኛል፡፡
ለመሆኑ ልጆቹን እንዴት ነው የምትመርጧቸው? አድልዎ አለ እንዳይባል ብዬ ነው?
አመራረጥ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተርስ ያላቸው ናቸው፤ የሚመረጡት፡፡ በዩኒቨርሲቲው አስተማሪዎች ናቸው፡፡ የሚመርጣቸው ትምህርት ሚኒስቴር ነው! እኔ እስከገባኝ  እኛ ብዙ  say የለንም (እጃችን የለበትም)፡፡ ዲፓርትመንቱ ቅድመ - ሁኔታ ማሟላታቸውን ያያል፡፡ ያን ያረጋግጣል፡፡ ከዛ በስተቀር እኛ ምርጫው ውስጥ ብዙ አንገባም። አንዱ ችግር ባለፈው ሳምንት ስብሰባ አድርገን ነበር - ፕሮግራሙ የት ነው ያለው፣ ወዴት ነው የሚሄደው? ምን ምን ችግር አለበት በሚል፡፡
በምን መንገድ ይመረጣሉ?
ከተገነዘብናቸው ችግሮች አንዱ አመራረጡ ነው። በኋላ ተማሪዎቹን የምንረከብ፣ የምናስተምራቸው ሰዎች፤ ነን መምረጥ ያለብን ወደሚል መጥተናል። እኛ ውጤታቸውን አይተን፣ ምን እንደተማሩ… አስፈላጊም ከሆነ ኢንተርቪው አድርገን እኛ መምረጥ አለብን፡፡ ለምሳሌ የሚመረጡት ሥራ ልምድ ላይ የተመሠረተ ከሆነ፣ ለውጥ ያመጣል፡፡ ከሁሉም በላይ መመረጥ ያለባቸው ችሎታ ያላቸው ብቻ መሆን አለባቸው፡፡ ያ ብቻ መሆን አለበት መስፈርቱ፡፡
ማገልገል አይደለም ዋናው፤ ነው የምትለኝ?
አዎ፡፡ በደንብ ቀርበህ ብታየው፤ ብዙ ዓመት ያገለገለ ሰው ከሂሳቡ ትምህርትም ርቋል ማለት ነው። ጥሩ ተማሪ ይሆናል ማለት ያስቸግራል… በጣም፡፡ (ሳቅ)
ከሁሉም ትምህርት ሂሳብ በወጣትነት ማወቅና መከታተል ያለብህ መስክ ነው! ሂሳብ ውስጥ ኖቤል ፕራይዝ የለም፡፡ ግን እንደኖቤል ፕራይዝ የሚቆጠር ፊልድስ ሜዳል የሚባል አለ፡፡ ያን ለማግኘት አንዱ ህግ፣ ዕድሜህ ከአርባ በታች መሆን አለበት! (ሳቅ) ከ40 በላይ ከሆነ የሠራኸውን ብትሠራ አይሰጥህም! (ሳቅ)
እና ሂሳብ በልጅነት ነው፤ ነው የምትለኝ?
ነው! ሂሳብ በልጅነት ነው!
በሀገራችን የፒኤችዲ ትምህርቱ ምን ያህል ለውጥ ያመጣል? ተማሪው ብዙ፣ አስተማሪው እጅግ ውሱን በሆነበት አገር ማለቴ ነው…እንዴት ታየዋለህ?
ከተገነዘብናቸው ችግሮች አንዱ አመራረጡ ነው፡፡ ይሄን ችግር ለመፍታት ግዜ ይወስዳል - ግልፅ ነው! ቢያንስ ማስተርስ ከተያዘ በኋላ 4 ዓመት ያስፈልጋል፡፡ የተለመደው ወደ 5 ዓመት ገደማ ነው። ከ5 ዓመት በኋላ ፒኤችዲ የያዙት ሰዎች በየቦታው እየሄዱ ያለውን የአስተማሪ እጥረት ችግር በመጠኑም ቢሆን ያቃልላሉ፡፡ ዋናው ተስፋችን በረዥም ጊዜም ቢሆን ይፈታል፡፡ በእኔ ግምት ጉዳዩ የሚያበረታታ ነው!
ይሄ ነገር ባጠቃላይ በተለይ በት/ሚኒስቴር አኳያ ለውጥ ያመጣል ብለህ ታምናለህ? ከት/ሚኒስቴር ጋር ግንኙነት የለኝም፡፡ ምናልባት ዲፓርትመንቱ ይኖረው ይሆናል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በኩል አንዳንድ ባለሥልጣኖች ለምሳሌ የሪሰርች ፕሬዚዳንት የነበረው አሁን ኢትዮፒያን አካዳሚ ኦፍ ሳይንስ ዳይሬክተር የሆነው፤ ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ፤ በጣም ረድቶናል፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ የዛሬ 2 ዓመት ኮንፈረንስ አድርጌ ነበረ፡፡ በኮንፈረንሱ ብዙ አስተማሪ ተጋባዦችን ለመጠቀም ጥረናል፡፡ ያኔ ዶ/ር መላኩም ረድቶናል፡፡ አየህ በት/ሚ በኩል እማይሆኑ ተማሪዎች ላይ ኢንቨስት ብታደርግ ዋጋ የለውም!
ዋናው ነገር በተማሪዎቹ አመራረጥ ላይ ት/ሚኒስቴር እጁን ቢያነሳ ጥሩ ነው! ለዲፓርትመንቱ ቢተወው! ከማቴማቲሻኖቹ የበለጠ የሚማረውን ሰው ሊያውቅ አይችልም! ት/ሚ የራሱ ሊቆች ሊኖሩት ይችላል፡፡ ግን እነዚህን ሰዎች እዚህ ካሉት ባለሙያዎች የተሻለ የሚያውቅ አለ ብዬ አላምንም! ባለንበት ሁኔታ በሂሳብ አንፃር፤ ይሄን አርግልኝ ከማለት፤ ይሄን ባታረግ ማለት እመርጣለሁ!
ብዙ ሰዎች ስናነጋግር ዩኒቨርሲቲው በማቴሪያል፣ በሰው ኃይልና በዩኒቨርሲቲው ኢንቫይሮንሜንት ዝቅ ብሏል፤ ይሉናል፡፡ ይሄ ዕውነት ከሆነ የናንተን ሥራ ድርብ ያደርገዋል! የኔም አብሮ አደግ ነህና ከእኛ ዘመን ስታወዳድረው እንዴት ታየዋለህ? በአጠቃላይ?
የቢኤስሲ ደረጃ ትምህርት ዝቅ ብሏል! አንድ መታየት ያለበት ነገር በኛ ጊዜ ዩኒቨርሲቲው ጥቂት ተማሪዎች ነበር የሚቀበለው! ዛሬ ግን ብዙ ነው ተማሪው፡፡ ያ ልዩነት አለው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ ጨምረው የዚያኑ ያህል የአስተማሪው ቁጥር አልጨመረም፡፡ ማቴሪያሎቹ፣ ላይብረሪዎቹ፣ ላቦራቶሪዎቹ በዚያው ልክ አልጨመሩም!
ያ ችግር አለ! በሂሳብ በኩል አዲስ የምለው ተማሪዎቹ የሚመጡት በፍላጐታቸው አይደለም። ኢንጂነሪንግ መሄድ ስላቃታቸው ወደሂሳብ ይመደባሉ፡፡ Undergraduate level ችግር አለ፡፡ የትምህርቱ ደረጃ ዝቅ ብሏል!
ዝቅ ብሏል ስንል የመምህራኑም ደረጃ ነው ሊባል ይችላል?
ተማሪው በዝቷል፡፡ ኮሌጆቹ በጣም በዝተዋል፡፡ የመምህራኑ ቁጥር ግን በዚያ መጠን አልጨመረም። የዩኒቨርሲቲዎቹ ሪሶርስስ፣ የላይብረሪዎቹ፣ የላቦራቶሪዎቹ ቁጥርም አልጨመረም፡፡ ፕሮፖርሽናሊ አብረው አላደጉም፡፡ ዱሮ ያልነበሩ አሁን ያሉ ሪሶርስስ አሉ፡፡ በጣም ሊረዱ የሚችሉ ለምሳሌ ኢንተርኔት፣ ላይብረሪ ባይኖርም ልትጠቀም ትችላለህ፡፡ ብዙ ኮርስስ (Lecture notes) ማግኘት ትችላለህ…ግን ማንም አይጠቀምባቸውም!
የመምህራኑስ ኢንተግሪቲ (ህብርነት) መተጋገዝ፣ መተባበር፣ አብሮ የማደግ? እንዴት ታየዋለህ?
ግራጁዌት ፕሮግራሙን በሚመለከት፤ ሂሳብ ውስጥ ሲተባበሩ አያለሁ! ራሳቸውን ለማሻሻል ይጥራሉ፡፡ ግን መጠቀስ ያለበት ሁኔታ ኑሮ እየተወደደ ይሄዳል፤ ደሞዛቸው አያድግም፡፡ ስለዚህ አንዳንዶቹ በደሞዛቸው ብቻ ለመኖር ያስቸግራቸዋል፡፡ ሌላ ሌላ ኮሌጅ እየሄዱ ያስተምራሉ፡፡
ያ ማለት ለምርምር ጊዜ ያጥርሃል ማለት ነው! ለሥራ የምታጠፋውንም አቅም ይሸራርፈዋል፡፡ ዞሮ ዞሮ dedicated ሆነው በቁርጠኝነት የሚሠሩ ናቸው በእኔ ዕይታ!
ይሄን ፕሮግራም እንዴት ለኢትዮጵያ ህዝብ እናሳውቃለን? እኔ አንተን ባላውቅህና ባልጠይቅህ ማለቴ ነው? ዩኒቨርሲቲው ምን ዘዴ ያስባል? ትልቅ ነገር ተሠርቶ ካልታወቀ ምን ዋጋ አለው?
ስለወደፊቱ አላውቅም፡፡ ባለፈው ኮንፈረንስ ስናካሂድ ተፈራ ገዳሙ (Meet ETV) አቅርቦት ነበር። እግረ መንገድ ስለ ፒኤችዲ ፕሮግራም አውርተናል። ማስተርስ ፕሮግራም ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ያውቃሉ!! ከዛ ሌላ እንግዲህ ሚዲያዎችን መጠቀም ዋናው መንገድ ነው! እንዳልከው ወጣቱ መንፈሰ - ዕርገት (inspiration) ያስፈልገዋል፡፡ ቢያውቅ ትልቅ ነገር ነው! ዋናው ጉዳይም እሱ ነው!
ወዳጄ ፕሮፌሰር ሽፈራው ብርሃኑ (ሽፌ) በሚቀጥለው ስትመጣ የተለወጠ ነገር ካለ እንወያያለን!! መልካም መንገድ!!
እንደ ፕሮፌሰር ሽፈራው ያሉ ዕውቅ ባለሙያዎች ያሏት አገር ደሀ አደለችም ብዬ አስባለሁ!!
(ይቀጥላል)

Read 4361 times