Saturday, 09 August 2014 11:26

“…ወስዶ ይቀላቅላል ከማያውቁት ጋራ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ቦብ ሆፕ የሚባል ‘ፈረንጅ’ ቀልደኛ ምን ብሎ ነበር መሰላችሁ… “ልደትህን በምታከብርበት ጊዜ ከኬኩ ዋጋ ይልቅ የሻማዎቹ ዋጋ ሲበልጥ ያኔ እያረጀህ መሆኑን እወቅ፡፡” ወዳጆቼ ይሄ የሻማ ቁጥር ነገር እንወያይበት እንዴ! (በሁለቱም ጫፍ ‘የሚለኮሱትን’ ሳይጨምር ማለት ነው። ቂ…ቂ…ቂ… ልጄ በሻማው ጊዜ ችላ ያሉት ቁጥር ለአቅመ ‘አዲንግ ማሺን’ እንዳይደርስ!) ዓመቱ እኮ ሽው እያለ ግራ ገባን!
ደግ ያሰማን፣ ደግ ያሳየን፣ ደግ ያሳስበንማ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…‘ሲቪል ሰርቫንቶች’ ወዳጆቼ …ቃል ከሚጠፋ ምናምን ይጥፋ የሚሉት ነገር አለ አይደል! መቼም ቃል የገባችሁልኝን ነገር አትረሱትም አይደል! (ምን ላድርግ… በዚህ የክህደት ዘመን ልጠይቅ እንጂ!) አሀ…ምንስ ህልምና እውነት አልገጥም ቢል ታዲያ እኔ ነኝ እንዴ ከመቶ ምናምን ሠላሳና አርባ ምናምን ያወረድኩት!
ይቺን ስሙኝማ…የሆነ መዝናኛ ቦታ ነው፡፡ እናላችሁ…በአንድ ብሄረሰብ ባህል “…የቡና ጀበናው ሁለት አፍ አለው፡፡ በአንዱ ቡና በቅቤ ሲወጣ በሌላው ቡና እንደወረደ ይቀዳል…” የሚል ነገር ይነሳል፡፡ ይሄኔ የጦፈ ክርክር ይጀመራል፡፡ ገሚሱ “እንዲህ አይነት ጀበና የለም…” ሲል ገሚሱ ደግሞ “ባታይ ነው እንጂ ሞልቶ…” ምናምን እየተባለ ክርክሩ ጦፈ፡፡ መዝናኛ ቤቱ ውስጥ ያለው የሚተዋወቀውም፣ የማይተዋወቀውም ሁሉ ክርክሩ ውስጥ ገባበት፡፡ እናላችሁ… አንዱ የሰዉን ሁሉ በነገሩ መግባት ያየ ምን አለ አሉ መሰላችሁ፣
“ጌሾ ዝሩ ጌሾ ነው አዝመራ፣
ወስዶ ይቀላቅላል ከማያውቁት ጋራ፡፡”
አሪፍ አይደል! (የካዛንቺስ ተባባሪዎቼ ለምታደርሱኝ ሁሉ ይመቻችሁማ! ለእናንተም መዝናኛ ለእኔም ርዕስ ማግኛ ካዛንቺስን ከመፍረስ ያድናትማ!)
እናላችሁ…ዘንድሮ ከማናውቀው ጋራ ሄዶ ለመቀላቀል ‘ጌሾ’ የምር እኮ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡ በደህናችን እንኳን ልንቀላቀል የተቀላቀለውንም ብተና ላይ ነን፡፡ እናማ…ከምንተዋወቃቸው ጋር እንኳን የቅልቅላችን አይነት ተለውጧል፡፡ ታዲያላችሁ…እንደ ድሮው…“ስማ እንገናኝና ሻይ ቡና እንበል…” የሚባለው ከንጹህ ወዳጅነት መሆኑ እየቀረ ነው፡
“እሺ…” ብላችሁ ለሻይ ቡና ያገኛችሁት ሰው… “ስማ እንትን መሥሪያ ቤት ከባድ ጉዳይ አለኝ፤ አንተ መቼም ሰው አታጣም…” ብሎ ይጀምርላችኋል። ነገርዬውማ…ሰውየው መጀመሪያም የፈለጋችሁ የናፍቆት ምናምን ጉዳይ ሆኖበት ሳይሆን “እንትን መሥሪያ ቤት ሰው ስላማታጡ…” ነው፡፡ “በየቦታው ሰው የማያጡ ሰዎች ብጹአን ናቸው…” ምናምን የሚል ጥቅስ በ‘አሜንድመንት’ ተገቢው መጽሐፍ ውስጥ ይካተተልንማ!
ቀለምና ቀለም ተጣልተው በቦታ
ጊዜ ተሰጥቷቸው የቀጠሮ ተርታ
ነገሩን ብንጠይቅ አግድሞ ካለፈ
ብለው ገለጹልን ወገን አሸነፈ፡፡
የሚሏት ግሩም ሰምና ወርቅ አለች፡፡ አዎ ዘንድሮ እንደሁ… ‘ወገን’ እንደ ኦክሲጅን የሚያስፈልግበት ዘመን ላይ እየደረስን ነው፡፡ እናማ…“አንተ መቼም ሰው አታጣም…”የምንል ሰዎች ብንበዛም አይገርምም፡፡
በደግና በመልካሙ ሁሉ የሚያቀራርቡንና ልብ ለልብ የሚያገናኙን…“ወስዶ ይቀላቅላል ከማያውቁት ጋራ” የሚያሰኙ ነገሮችን ያብዛልንማ!
እናላችሁ…ግንኙነታችን ሁሉ ከጀርባ የጥቅማ ጥቅም ነገር አዝሎ የሚመጣ ሲሆን አስቸጋሪ ነው። በንጹህ የምንቀርባቸው ወዳጆቻችንን ሁሉ… አለ አይደል… “ምን ቢፈልግ ነው ልጋብዝህ፣ ልጋብዝህ ያበዛው!” ማለት እንጀምራለን፡፡
ደግሞላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የሆነ ወዳጃችሁን መጠራጠር ስትጀምሩ አባባሹ መአት ነው፡፡ “አንተ፣ ይሄ ጓደኛህ አሁን፣ አሁን የሆነ ደስ የማይል ነገር አይበታለሁ…” ምናምን ካለ በኋላ ምን ይል መሰላችሁ… “ብቻ ለክፉም ለደጉም ከእሱ ጋር ስትሆን ጠንቀቅ በል…” የሚል መርዝ ጣል ያደርግባችኋል፡፡ እናማ… አይደለም ከማታውቁት ጋራ ሄዶ መቀላቀል የዘንድሮው ነገር የምታውቁትን፣ አብራችሁ አፈር እየፈጫችሁ ያደጋችሁትን  ሁሉ መጠራጠርና መሸሽ ሆኗል፡፡
ስሙኝማ…ለረጅም ጊዜ ሳትተያዩ ከኖራችሁ በኋላ ድንገት የምታገኟቸውን ሰዎች አስቧቸው። ብዙዎቹ አሳሳቃቸው፣ ትከሻ አገጨጫታቸው ምናምኑ ሁሉ የሆነ ቅዝቃዜ ነገር ታዩበታላችሁ፡፡ ዘመኑ ነዋ!  አጠገባችሁ ያለውን ያላመናችሁ የሩቁን እንዴት አድርጋችሁ ትቀበሉት!
በደግና በመልካሙ ሁሉ የሚያቀራርቡና ልብ ለልብ የሚያገናኙ…“ወስዶ ይቀላቅላል ከማያውቁት ጋራ” የሚያሰኙ ነገሮችን ያብዛልንማ!
ግንኙነት ሲበላሽ ነገር ይበዛል፡፡ ዘንድሮ በትንሹም በትልቁም አምባጓሮ ማየት እየተለመደ ነው፡፡ ስሙኝማ…አንዳንድ ቦታ
“ጌሾ ዝሩ ጌሾ ነው አዝመራ፣
ወስዶ ይቀላቅላል ከማያውቁት ጋራ፣”
እየተባለ ሰላማዊ ጨዋታ ሲኖር ሌላው ዘንድ ደግሞ በይዋጣልን የሸሚዝ እጀታውን የሚጠቀልል ሞልቶላችኋል፡፡
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የሆነ መዝናኛ ስፍራ ነው፡፡ ሰውዬው ቀጫጫ ነው፡፡ እናማ… ከሆነ ግዙፍ ሰው ጋር በሆነ ነገር ይጋጫል። ታዲያላችሁ… ቀጫጫው ሰውዬ ግዙፉን ሰው ከፍ ዝቅ አድርጎ ይሰድበዋል፡፡ ግዙፉ ሰውዬም ይናደዳል፡፡
እናማ… ግዙፉ ሰውዬ የቀጫጫውን አሥራ ሦስት ብልት ሊያወጣለት ከተቀመጠበት ብድግ ብሎ ወደ እሱ አቅጣጫ መሄድ ይጀምራል፡፡ ግን ከመድረሱ በፊት ቆም ይላል፣ ከዚያ ምን አለ መሰላችሁ…“ለዶሮ አጥንት መጥረቢያ አያስፈልገውም…” ብሎ ወደ ቦታው ተመለሰ አሉ፡፡ እንኳንም ተመለሰ። ጉልበታችን ምላሳችን ላይ ለሆነችው “ለዶሮ አጥንት መጥረቢያ አያስፈልገውም…”  የሚሉ ሰዎች ያብዛልንማ!
በደግና በመልካሙ ሁሉ የሚያቀራርቡና ልብ ለልብ የሚያገናኙ  “ወስዶ ይቀላቅላል ከማያውቁት ጋራ” የሚያሰኙ ነገሮችን ያብዛልንማ!
የቅርቦቻችንን ሰዎች ባህሪይ የማወቅ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ጎረቤቱ ያሉትን አዛውንት ምን ይላቸዋል… “ትናንት ማታ አንድ ወጣት ልጅዎን ሊስማት ሲታገል አየሁት፣” ይላቸዋል፡፡ እሳቸውም “ታዲያ ተሳክቶለት ሳማት?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡ እሱም ነገር አሳመርኩ ብሎ፣  “ኸረ በጭራሽ! ቀንድ ቀንዱን ብላ ነው ያባረረችው…” ሲላቸው ምን አሉ መሰላችሁ… “እንግዲያውስ ያየሀት የእኔ ልጅ አይደለችም፡፡”
አሪፍ አይደል! በዚህ ዘመን እንዲህ ‘ልጁን የሚያውቅ’ አባት ሲገኝ አሪፍ ነው፡፡
በደግና በመልካሙ ሁሉ የሚያቀራርቡና ልብ ለልብ የሚያገናኙ… “ወስዶ ይቀላቅላል ከማያውቁት ጋራ…” የሚያሰኙ ነገሮችን ያብዛልንማ!
እኔስ መስሎኝ ነበር ድኻ ነው ደካሚ
ለካስ ሁሉም ኖሯል አፈር ተሸካሚ
የሚሏት የጥንት ስንኝ አለች፡፡ የዚህ አገርና የዚህ ዓለም ዋናው ቸግር…አለ አይደል…“ሁሉም አፈር ተሸካሚ…” መሆኑን መርሳቱ ነው፡፡ “ሁሉም ዘላለም ኗሪ አለመሆኑን መርሳቱ…” ነው፡፡ መርሳት የሌሉብንን ነገሮች እንዳንረሳ ልቦናውን ይስጠን፡፡
በደግ በደጉ፣ በመልካም በመልካሙ፣ በጽድቅ በጽድቁ…“ወስዶ ይቀላቅላል ከማያውቁት ጋራ…” የሚያሰኙ ነገሮችን ያብዛልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4259 times