Saturday, 09 August 2014 11:21

ዐይነ ስውር ድንጋይ ወርውሮ፣ ጠላቱን ስቶ ወዳጁን መታ!

Written by 
Rate this item
(6 votes)

“ምነው ወዳጅህ እኮ ነኝ፤ ቢለው”
“ዝም በል! ዋናው አለመሳታችን ነው!” አለው

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ጓደኛሞች ጫካ ሄደው እንጨት ቆርጠው ለመምጣት ይፈልጋሉ፡፡ አንደኛው በመጥረቢያ ቅርንጫፍ እየቆረጠ ሳለ እጁና ሳያስበው ቆርጦ ጣለው፡፡
ጓደኝየው የተቆረጠውን ክንድ በፌስታል ውስጥ ከትቶ፤ እጁ የተቆረጠ ጓደኛውን ይዞ ወደ ቀዶ - ጥገና ሐኪም ወሰደው፡፡
ዶክተሩም - “በጣም ዕድለኛ ነህ እኔ የተቆረጡ አካላትን መልሶ የማጣበቅ ክሂል ባለሙያ ነኝ፡፡ በአራት ሰዓት ውስጥ ተመልሰህ ና” አለው፡፡
ጓደኝየው - “እሺ ዶክተር ባሉኝ ሰዓት እመጣለሁ” ይልና ይሄዳል፡፡
ከተባለው ሰዓት በኋላ ሲመለስ፤ ዶክተሩ፤
“እጨርሳለሁ ካልኩበት ሰዓት ቀድሜ ጨረስኩ፡፡ ገዋደኛህ ጤንነቱ ተመልሶ እዚህ ታች ወዳለው ግሮሠሪ ሄዷል፡፡”
ጓደኝየው በደስታ ጮቤ እየረገጠ ወደተባለው መጠጥ ቤት ሄደ፡፡ ጓደኝየው ጭራሽ የዳርት ውርወራ ግጥሚያ ይዟል፡፡
ከጥቂት ሣምንታት በኋላ ጓደኛሞቹ አሁንም ወደጫካ ሄደው እንጨት ቆረጣ ላይ ተሰማሩ፡፡ ባለፈው እጁን የቆረጠው ሰው አሁን ደግሞ እግሩን ቆርጦ ጣለው፡፡ ጓደኝየው እንዳለፈው ጊዜ የተቆረጠውን እግር ፌስታል ውስጥ ከትቶ ጓደኛውን ይዞ ወደዚያው የአካል ቀዶ ጥገና ሐኪም ዘንድ ይዞት ሄደ፡፡
ሐኪሙም፤
“አየህ፤ የእግር ቀዶ - ጥገና ትንሽ ከበድ ያለ ነው፡፡ ከስድስት ሰዓት በኋላ ተመለስ” አለው፡፡
ጓደኝየውም፤
“እንዳልከው አደርጋለሁ ዶክተር” ብሎ ሄደ፡፡
ከስድስት ሰዓታት በኋላ ተመልሶ ውጤቱን ለማወቅ ወደ ሐኪም ሲመጣ፤
ሐኪሙ “ይገርምሃል ከነገርኩህ ሰዓት አስቀድሜ ሥራ አገባደድኩ፡፡ ጓደኛህ እዚያ ታች ወዳለው እግር ኳስ ሜዳ ሄዶልሃል” አለው፡፡
ጓደኝየው ሐኪሙ አመስግኖ ወደ ኳስ ሜዳው ወርዶ ሲያየው፡፡ ያ እግረ የተገጠመለት ጓደኛው ምን የመሳሰሉ ጎሎች እያገባ ነው፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ግን፣ ያ ጓደኝየው እጅግ ከባድ የመኪና አደጋ ይገጥመውና አንገቱ ሙሉ ለሙሉ ተቆረጠ፡፡ ጭንቅላቱ ብቻውን ወደቀ፡፡
እንደተለመደው የፈረደበት ጓደኛ ጭንቅላቱን በፌስታል ከትቶ ቀሪውን የጓደኝየውን አካል ጭኖ ወደ ሐኪሙ በረረ፡፡
ሐኪሙም፤
“ጭንቅላት መግጠም እጅግ ከባድ ነው፡፡ ለማንኛውን ከአሥራ ሁለት ሰዓት በኋላ ተመለስ” አለው፡፡
ተመልሶ ሲመጣ፤ ሐኪሙ፡-
“ይቅርታ አድርግልኝ፡፡ ጓደኛህ ሞቷል” አለው፡፡
ጓደኛውም፤
“ዕውነትክን ነው፡፡ የጭንቅላት ነገር ከባድ መሆኑን እገምታለሁ” አለ፡፡
ሐኪሙም፤
“ቀዶ ጥገናውን እንኳ ደህና አድርጌ ነበር የሰራሁት፡፡ ግን አየህ፤ አንተ ስታመጣው እዛ ፌስታል ውስጥ ታፍኖ ትንፋሽ አጥሮት ነው የሞተው!”
*   *   *
እጅ እግሩን ከቆረጠበት አደጋ ያልተማረ፣ አንገቱን የሚቆረጥበት ሰዓት ይመጣል! ከስህተት አለመማር መዘዙ ራስን እስከማጣት ያደርሳል፡፡
የአካላችን ሁሉ አናት የሆነው ጭንቅላት የሁሉ ነገራችን መሪ ነው፡፡ አንዴ ካመለጠ የማይገጣጠም መሆኑም ይሄንኑ የሚያመላክተን ነው፡፡ ሁሉን ተግባራችንን በአቅል በአቅል የሚያስቀምጥልን፣ የሚያደራጁልን፣ መንገድ የሚያገባልን የህይወት መሪያችን እሱ ነው፡፡ በሀገር ደረጃ ሲታይም፤ ተቋሞቻችንን፣ ድርጅቶቻችንን፣ ት/ቤቶቻችንን፣ ኮሚሽኖቻችንን፣ ሚኒስቴሮቻችንን፣ ኢንዱስትሪዎቻችንን ወዘተ የሚመሩ ርዕሰ - አመራሮች እንደጭንቅላት ናቸው፡፡ የእነዚህ ጭንቅላቶች ልክ መሆን፣ ቅጥ መያዝና የድርና ማግ መቀናጀት ነው የሀገርን ጤና ልክነት የሚረጋግጠው፡፡ ይህ የጭንቅላት ክህሎት ከሌለ፣ ካልተባ፣ ከቀልብ ካልተዋሃደ ወጥነት ያለው አመራር ማግኘት አይቻልም፡፡ ጨርሶ ባዶ የሆነ ዕለት ደሞ መሄድ ቀርቶ መቆም ያቅታል፡፡
ገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ በ “በልግ” መጽሐፉ፤
“በዚህ በያዝኩት ጎራዴ፣ አንተግክን ቀንጥሼ ብጥለውም”
ከባርኔጣህ በስተቀር፣ ዋጋ ያለው ነገር አይወድቅም”
የሚለን ለዚህ ነው
“የዕውቀት ማነስ ፓለቲከኛ አደረገኝ” ከሚል ሰው ይሰውረን፡፡ አንዳንድ ፖለቲካ እጅግ አስመሳይ ከመሆኑ የተነሳ “የፆም መኪያቶ” “መኪያቶ” የሚባለውን ዓይነት ይሆናል፡፡ ወይ ሙሉውን መፆም ነው፣ አሊያ የሚለውን ሃሳብ ጨርሶ መርሳት ነው፡፡ “ፀብ ክርክር ካለበት ጮማ - ፍሪዳ፤ ፍቅር ያለበት ጎመን ይሻላል” ይላሉ አበው፡፡ በላሸቀ ኢኮኖሚ ውስጥ የፖለቲካ ጀግና መሆን እያደር ሽባ እንደሚያደርገን መገንዘብ ጭንቅላት ይዞ ማሰብን አይጠይቅም፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ ኢኮኖሚውን ማዳን ነው፡፡ የዝሆን ጥርስ አናት ያለው ጉልላት ላይ ያለ የታችኛው ህዝብ መከራ አይታየውም፡፡ ያም ሆኖ የማይለወጥ ነገር የለም ሁሉም የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ወይም እንደ ቪክተር ፍራንክል፤
“ሁኔታዎችን መለወጥ ካልቻልክ ራስህን ለመለወጥ ትገደዳለህ” እንላለን፡፡ ቪክተር ከ2ኛው ዓለም ጦርነት ሆሎኮስት ቃጠሎ እልቂት የተረፈ ሳይካትሪስትና ፀሐፊ ነው፡፡ ከእልቂት ከተረፈ በኋላ በሰው ልጅ ላይ ምን ለውጥ እንደሚመጣ አስተውሏል፡፡ ለእያንዳንዱ ለውጥ ያ ሁሉ መስዋዕትነት መደገም አለበት ማለት አይደለም፡፡ ከማዕበሉ በኋላ የረጋ አየር፣ አየርም ቢሉ ለውጥ የሰፈነበት፤ ይመጣል ማለት እንጂ!
የበላይም ይናገር የበታች ለሀገራችን የሚጠቅመው መደማመጥ ነው፡፡ በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንደሚኬድበት መንገድ (One way road) አንሁን፡፡ የሚነገረንን እንስማ፡፡ ሌላው ሰው ድንገት ከእኔ የተሻለ ሀሳብ ቢያቀርብስ? እንበል፡፡
ደራሲ ከበደ ሚካኤል
“አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ”
ያሉትን አለመዘንጋት ከብዙ አባዜ ያድናል፡፡ እርግጥ ይህንንም የሚሰማ ካለ ነው፡፡
አበሻ በኢኮኖሚው መዘበትና ምፀት ማውራት ይችልበታል፡፡ ኢኮኖሚው አላፈናፍን ሲለው መውጫው በግጥም መተንፈስ ነው፡-
“በቆሎ፤ በዝናብ፣ ሲጠብስ እያያችሁ
ሰዉ ሥራ አይሰራም፣ ለምን ትላላችሁ!”
የፖለቲካ ምፀት ሲያምረው ደግሞ፤
ዐይነ ስውር ድንጋይ ወርውሮ፣ ጠላቱን ስቶ ወዳጁን መታ፡፡
“ምነው? ወዳጅህን? ወዳጅህ ነኝ እኮ!” ቢለው፤
“ዝምበል፡፡ ዋናው አለመሳታችን ነው!” አለ ይባላል፤ ይላል፡፡




Read 7443 times