Saturday, 09 August 2014 11:17

መኢአድና አንድነት ውህደታቸውን ለማራዘም መገደዳቸውን ገለፁ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

ለውህደቱ መራዘም  ምርጫ ቦርድን ተጠያቂ አድርገዋል
መንግስት በግል ሚዲያዎች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አውግዘዋል

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ነገ ሊያካሂዱት የነበረውን ውህደት ለማራዘም መገደዳቸውን አስታወቁ፡፡ ለውህደቱ መራዘም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
በሌላ በኩል  መንግስት በግል ሚዲያዎች ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ፣ የህዝብን መረጃ የማግኘት መብት የሚገድብና የመናገር ነፃነትን የሚያሳጣ በመሆኑ እንደሚያወግዙት ፓርቲዎቹ ገልፀዋል፡፡
“መኢአድና አንድነት ወደ ሰላማዊ የትግል ጦርነት ውስጥ መግባታቸውን ለህዝብ ማሳወቅ ይወዳሉ” በሚል ርዕስ ከትላንት በስቲያ ፓርቲዎቹ  በሰጡት መግለጫ፤ “መኢአድ በ2005 ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ምዕላተ ጉባኤ ያልተሟላ በመሆኑ መዋሀድ አትችሉም የሚል ተልካሻ ምክንያት በማቅረብ ምርጫ ቦርድ  ውህደቱን እንድናራዝም አስገድዶናል  ብለዋል፡፡
በ2005 በተካሄደው ጉባኤ ከ600 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት 390 ያህሉ ተገኝተው ህጉ በሚፈቅደው መልኩ ጉባኤው መካሄዱን ራሱ ምርጫ ቦርድም ያውቃል ያሉት የመኢአድ ሃላፊዎች፤ጉባኤው ሲካሄድ የምርጫ ቦርድ ተወካዮች መጥተው ምዕላተ ጉባኤው መሙላቱን ቢያረጋግጡም ቦርዱ ግን ምዕላተ ጉባኤው አልተሟላም በሚል ለአንድ ዓመት ያህል አዎንታዊ ምላሽ ሳይሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
“በህወሓት /ኢህአዴግ የሚመራው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ፣ በሰላማዊ ትግሉ ላይ ከፍተኛ መሰናክሎችን በመፍጠር ከዚህ ቀደም የተደረጉ አገር አቀፍ ምርጫዎችን በማዘረፍ ህዝብ የድል ባለቤት እንዳይሆን አድርጓል” ያሉት ፓርቲዎቹ፤ አሁን ደግሞ ጠንካራ ፓርቲዎች ተዋህደው በተደራጀ ሃይል በሰላማዊ ትግሉ እንዳይገፉ አሳማኝ ያልሆነ ምክንያት በመደርደር ውህደታችንን እንዳንፈጽም የሚያደርገውን ጫና እንቃወማለን ብለዋል።
“ምርጫ ቦርድ እንቅፋት ቢፈጥርም ፓርቲዎቹ ግን በሃሳብና በቁርጠኝነት ተዋህደዋል” ያሉት የአንድነትና መኢአድ አመራሮች፤በተጠናከረ ሃይል በሰላማዊ ትግሉ በመግፋት አላማቸውን እንደሚያሳኩ ገልፀዋል፡፡
የምርጫ ቦርድን ውሳኔ አስመልክቶ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የአንድነት ፕሬዚዳንት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፤ በዚህ ጉዳይ ምርጫ ቦርድ ሄደው እንደነበር አስታውሰው መኢአድ በወቅቱ ለምርጫ ቦርድ የላከው የምዕላተ ጉባኤ ዝርዝር 285 እንደነበርና ኮረሙ ተሟላ የሚባለው ከ300 አባላት በላይ በስብሰባው ሲሳተፉ እንደሆነ  ከምርጫ ቦርድ እንደተገለፀላቸው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
መኢአድም የስም ዝርዝር ወረቀቶች ተረስተው መቅረታቸውን በመጠቆም  ለምርጫ ቦርድ 118 ተጨማሪ የተሳታፊ አባላትን ዝርዝር ቢያቀርብም  በወቅቱ ያልተላከ የአባላት ስም ተቀባይነትና ተአማኒነት የለውም በሚል የቦርዱ የህግ ክፍል አለመቀበሉን የገለፁት ኢ/ር ግዛቸው፤“መኢአድ ህጋዊና አገር አቀፍ ፓርቲ ሆኖ ሳለ በማህተምና በፊርማ የተረጋገጠ ማስረጃ ሲያቀርብ እንዴት አይታመንም ትላላችሁ፤አይታመንም የምትሉበትን ምክንያት በማስረጃና በመረጃ አቅርቡ” በማለት ቢከራከሩም ከቦርዱ ምላሽ  አለማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡  
“ኮረም ሞላ አልሞላ የሚለው ለውህደቱ እንቅፋትነቱ አላሳመነኝም” ያሉት የአንድነት ፕሬዚዳንት፤ ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤ ሲካሄድ የራሱን ታዛቢዎች በማስቀመጥ ታዛቢዎቹ ለቦርዱ ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ጠቁመው፣ቦርዱ ታዛቢዎች ያቀረቡለትን ሪፖርት ከፓርቲው ሪፖርት ጋር በማመሳከር ችግሩን መፍታት ይችል ነበር ብለዋል፡፡ “መኢአድ ጉዳዩን በአፋጣኝ ወደ ፍ/ቤት መውሰድና መብቱን በህግ ማስከበር አለበት” ሲሉም ኢንጂነር ግዛቸው አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የጽ/ቤቱ ምክትል ዋና ሃላፊ አቶ ወንድሙ ጐላ ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው ሲመልሱ፤ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎች የመሃድ መብት እንዳላቸውና መዋሃዳቸው የተሻለ እንደሚሆን እንደሚያምን ጠቁመው ነገር ግን ፓርቲዎቹ በምርጫ ቦርድ እንዲያሟሉ የሚጠየቁትን መስፈርት ማሟላት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ “በአሁኑ ወቅት እንዲያሟሉ የጠየቅናቸውን መስፈርቶች በደብዳቤ ገልፀናል” ያሉት ሃላፊው፤እነዚህን ነገሮች እስካሟሉ ድረስ መዋሃድ የማይችሉበት ምክንያት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲዎቹ እንዲያሟሉ የተጠየቁትን መስፈርቶች አስመልክቶ የጠየቅናቸው ሃላፊው፤ “አሁን ሩቅ ቦታ ነኝ፣ በእጄ ላይ ዝርዝሮቹ የሉም፣ ሆኖም ያላሟሉት ነገር እንዳለ ግን ግልጽ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል መኢአድና አንድነት፤መንግስት በግል ሚዲያዎች ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ የህዝብን መረጃ የማግኘት መብት የሚገድብና የመናገር ነፃነትን የሚያሳጣ በመሆኑ እንደሚያወግዙት አስታውቀዋል፡፡ ሰሞኑን የፍትህ ሚኒስቴር በአቴቪ ባሰራጨው መግለጫ፤ ህገመንግስቱን በሃይል ለመናድና የሃይማኖት አክራሪነትን በመስበክ አመፅ ቀስቅሰዋል ባላቸው አምስት ተጠርጣሪ የግል ፕሬሶች  ላይ  ክስ መመስረቱን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

Read 2715 times