Saturday, 09 August 2014 11:15

ሸራተን አዲስ ወደ ድርድር እንዲመለስ ፌዴሬሽኑ ጠየቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

“ሰራተኞቹን በጅምላ ያባረረበት መንገድ የአገሪቱንም ሆነ የዓለምን ህጎች የጣሰ ነው”

የቱሪዝም ሆቴሎችና ጠቅላላ አገልግሎት ሰራተኛ ማህበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን፤ የሸራተን ማኔጅመንት እምቢተኝነቱን ትቶ ወደ ሰላማዊ የህብረት ስምምነት ድርድሩ እንዲመለስ ጠየቀ፡፡ ፌዴሬሽኑ ሰሞኑን ባካሄደው 38ኛ መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባ፣ በሸራተን ጉዳይ ላይ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ ያወጣ ሲሆን መግለጫው ለጠ/ሚኒስትሩና ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርስ ወስኗል፡፡
የሠራተኞች የመደራጀትና የመደራደር መብት በህገ መንግስቱ የተረጋገጠ መሆኑን በአቋም መግለጫው ላይ የጠቀሰው ፌዴሬሽኑ፤ለድርድር የተጠየቀው የሸራተን ማኔጅመንት አለመግባባትን ፈጥሮ እንደነበረና ጉዳዩ ወደ ህግ ተወስዶ በአስማሚ አካል አማካኝነት ድርድር መቀጠሉን አስታውሷል፡፡
ሁለቱም ወገኖች የቅድመ ድርድር ሰነድ ተፈራርመው ወደ ድርድር ቢገቡም ማኔጅመንቱ ተደራዳሪ የሆኑ የማህበር መሪዎችንና በርካታ ሰራተኞችን በህገ ወጥ መንገድ ከስራ ማሰናበቱ የቅን ልቦና ጉድለት በመሆኑ የማህበር መሪዎች ወደ ስራቸው ተመልሰው የተቋረጠው ድርድር እንዲቀጥልና ሌሎች የስራ ውል የተቋረጠባቸው ሰራተኞችም ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ ፌዴሬሽኑ  አበክሮ ጠይቋል፡፡
የድርጅቱ የማኔጅመንት አካላት በሰራተኛው ላይ እየፈፀሙት ያለው ማስፈራራት፣ ስድብ፣ ዛቻና በአጠቃላይ የሰራተኛ የስራ ዋስትና ላይ እየፈጠሩ ያለውን ስጋት ለመቅረፍ የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን በማድረግ ሰራተኞችን እንዲታደጉም  ጥሪ አስተላልፏል፡፡ ባለ ሰባት ነጥብ የፌዴሬሽኑ የአቋም መግለጫ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለዓለም የስራ ድርጅት (ILO)፣ አዋጁን ለሚያስፈፅሙ አካላት፣ ለኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽንና ለአቻ ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኖች እንዲደርስ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ መወሰኑም ተገልጿል፡፡
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ቶሌራ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ “የሸራተን ማኔጅመንት እየወሰደ ያለው ፈር የለቀቀ ህገ-ወጥ እርምጃ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነው” ሲሉ ተችተዋል፡፡ “በአገራችን የሰራተኛ ቅነሳና ስንብት ማድረግ የተለመደ  ቢሆንም ህግና ደንቡን ተከትሎ ነው” ያሉት አቶ ቶሌራ፤ቅነሳው በሚደረግበት ወቅት መብታቸው ተከብሮ፣ ጥቅማ ጥቅማቸው ተጠብቆና የአገልግሎት ክፍያቸውን አግኝተው ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
የአገራችን መንግስት የዓለም የሥራ ድንጋጌን   ተቀብሎ እውቅና መስጠቱን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፤“ሸራተን ይህን ሁሉ ድንጋጌ ደፍጥጦ ሰራተኞችን ያለማስጠንቀቂያ በጅምላ ያባረረበት መንገድ የአገሪቱንም ሆነ የዓለምን ህጎች የጣሰ ነው” ብለዋል፡፡ ከአሁን በኋላ የሸራተን ጉዳይ የዘጠኙ ፌዴሬሽኖች፣ የ915 መሰረታዊ ሰራተኛ ማህበራትና የመላው ኢትዮጵያ ሰራተኞች አጀንዳ ይሆናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ሸራተን እምቢተኝነቱን ትቶ ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጣ አጥብቀው ጠይቀዋል፡፡
“ሸራተን ድርድሩን ሐምሌ 22 ረግጦ ከወጣ በኋላ ሐምሌ 23 ሰራተኛ ማባረሩ ይታወቃል” ያሉት የሠራተኛ ማህበሩ አመራሮች፤ አሁን ደግሞ አሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርዱ “ሸራተን ከተባረሩ ሰራተኞች ጋር አልደራደርም ብሏል” እያለ  “ድርድሩ ይቀጥል የሚል ድፍን ያለ ውሳኔ ሰጥቶናል” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡  

Read 2467 times