Saturday, 02 August 2014 11:50

ሰማይ ላይ ምን አለ?!

Written by  ደመቀ ከበደ - ጣና ዳር
Rate this item
(8 votes)

አዕዋፋት ሁሉ ሽቅብ ይበራሉ
አክናፎቻቸውን - ያወናጭፋሉ
በደመነ ሰማይ - በጉም በጠቆረ
ዝንብ መስሏል ላዩ - አንዳች የአዕዋፍ ዘር - ከጎጆው አልቀረ
ሰማይ ላይ ምን አለ?!...
ጭልፊት ታፏጫለች
መንቁሯን አሹላ - ትሽከረከራለች
ጥንብ አንሳም ያውና - ከብዶት ሰውነቱ
ከጉም ጋር ይጋፋል - ከነፋስ በብርቱ
ሰማይ ላይ ምን አለ?!...
ቆቅ እንኳን ከጫካ - ከጅግራ ሸፍታ
እፍ እፍ ትላለች - እፍ እፍ ሁሉ ቦታ
ደበኔዋም ያቻት - እዚያ ላይ ከፍ ብላ
ቁራንና እርኩምን - ከኋላ አስከትላ
ድንቢጥና ዋኔ - ድርጭትም አልቀሩ
እኒያው ይታያሉ - ሰማይ ላይ ሲበሩ፤
ሰማይ ላይ ምን አለ?!...
እንኳን አዕዋፋት - ባለ አክናፎቹ
ዶሮም ሰማይ ላይ ናት - ያቺውናላቹ፤
ዳክዬ ከውሃ - ወታለች ለዛሬ - ሰማይ ነው ባህሯ
ትርመሰመሳለች - በደመናው መሀል - ያለ ድሮ ግብሯ
ክንፍ ያለው ነፍስ ሁሉ - ባለ ላባ ገላ
ትንሽ የለ ትልቅ - የአዕዋፍ ዘር ሁላ
እንደ የዝርያው - መደዳ እየሰራ ይበራል ወደ ላይ - ሽቅብ ወደ ሰማይ
ወደ ላይ ወደ ላይ - ወደ ላይ ወደ ላይ…
እንጃ ምን አውቃለሁ - ሰማይ ምን እንዳለ
ከመሬት ግር ብሎ - አዕዋፍ ኮበለለ፤
ጠርጥር ያገሬ ሰው - ተርጉም የወፍ ቋንቋ - እስኪ ተነጋገር
ወፍ የጠላው መሬት - አያጣውም አሳር - አያጣውም ነገር!...

Read 3774 times