Saturday, 02 August 2014 11:49

ኢምፔሪያል ሆቴልን የገነቡት የንግድና የሥነፅሁፍ ሰው

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሰበ ተፈሪ ያጠናቀቁት አቶ አስፋው ተፈራ፤ ወደ አዲስ አበባ መጥተው በሊሴ ገብረማርያም፣ በኮልፌ የእደ ጥበብ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ በተግባረ ዕድና በመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም የተማሩ ሲሆን ከዚያም በደብረብርሃን ኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት የመምህርነት ሥራ እንደ ጀመሩ “እኔ ማን ነኝ?” በሚለው መፅሃፋቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
ለአንድ ዓመት በመምህርነት ካገለገሉ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገብተው መማር የጀመሩ ሲሆን ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በአርበኞች ትምህርት ቤት አስተምረዋል፡፡ ወደ እንግሊዝ አቅንተውም ትምህርታቸውን ቀጥለዋል፡፡
በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመምህርነት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የጥናትና ምርምር ክፍል በሕዝብ አስተዳደር ዘርፍ፣ በተባበሩት መንግስታት በሚደገፈው ዩኔስኮ በሕዝብ አስተዳደር የምርምርና ጥናት ክፍል፣ በባህር ኃይል ወደብ አስተዳደር መስሪያ ቤት፣ ሌጎስ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጸሐፊነት ያገለገሉት አቶ አስፋው፤ ከዚያ በኋላ የመንግስት ኃላፊነታቸውን በመተው የጽሕፈት መሳሪያ መሸጫ መደብር በመክፈት ስኬታማ የንግድ ሥራ ማከናወናቸውን በፅሁፋቸው ገልፀዋል፡፡
“የንግድ ጽንሰ ሐሳብ በውስጤ የተፈጠረው በተወለድኩበት ገጠር ነው፡፡ አባቴ የራሴ የሆነ መሬት ሰጥቶኝ አርስ ነበር፡፡ በመጀመሪያው አዝመራ ሶስት ኩንታል እህል አገኘሁ፡፡ እህሉን ገበያ ወስጄ በመሸጥ ለራሴ ልብስ ገዛሁ፡፡ ለአባቴ እጀ ጠባብና ነጠላ ገዛሁ፡፡ ተደንቆ ተደስቶ መረቀኝ፡፡ ፍየልና ዶሮዎችም ገዛልኝ፡፡ ይህ ገጠመኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ገበያንና ከገበያ የሚገኘውን ጥቅም አሳውቆኛል” የሚሉት አቶ አስፋው፤ በግል የንግድ ሥራቸው የተለያዩ ፈተናዎችን ቢጋፈጡም ከጊዜ ወደ ጊዜ ቢዝነሳቸው እያደገ መሄዱን ያወሳሉ፡፡
በ1958 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ሕንፃ ምድር ቤትን በመከራየት ቼምበር ማተሚያ ቤትን አቋቁመዋል፡፡ “ወደ ማተሚያ የገፋፋኝ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ስነ ጽሑፍ መውደዴ ነው፡፡ ሌላው በለንደን ትምህርቴን ስከታተል በትርፍ ጊዜዬ ዩናይትድ ፕሬስ በተባለ ድርጅት እሠራ ነበር። ሌጎስ በነበርኩበት ጊዜ ኢትዮጵያ ኤምባሲ አጠገብ የነበረው ራብዌይ ፕሪንተርስ ተጨማሪ ተጽእኖ እንዳሳደረብኝ እገምታለሁ፡፡ “Africa’s March to Unity” የተባለው መጽሐፌ የታተመው በዚሁ ማተሚያ ቤት ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ወደ ህትመት ሙያ እንዳቀረቡኝ እገምታለሁ” ሲሉ ፅፈዋል፡፡
ሥራቸው እያደገ ሲመጣ መሬት ገዝተው ለማተሚያ ቤት የሚሆን ሕንፃ ገነቡ፤ ቼምበር ማተሚያ ቤትም ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ወጥቶ ወደ አዲሱ ሕንፃ ተዛወረ፡፡ በደርግ ዘመን የገጠማቸውን ችግር በመሸሽ ወደ ጅቡቲ ተሰደው ነበር፡፡ እዚያም በግል ሥራ መንቀሳቀስ ቀጠሉ። በወቅቱም ወደ ኬኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ማልታና አሜሪካ ተጉዘዋል፡፡ በጅቡቲ ሆቴል ለመክፈት አቅደው ሳለ ነው ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ጅቡቲን በጎበኙበት ወቅት እዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ሰብስበው “የፖሊሲ ለውጥ ስላደረግን አገራችሁ መጥታችሁ አልሙ” የሚል ጥሪ ያቀረቡት፡፡ አቶ አስፋው ተፈራም ወደ አገራቸው በመመለስ ገርጂ አካባቢ ኢምፔሪያል ሆቴልን አስገነቡ፡፡
እኒህ ሰው “እኔ ማን ነኝ?” የተሰኘውና የህይወት ታሪካቸውን የሚያትተው መፅሃፋቸውን ጨምሮ የታሪክ፣ የልቦለድ፣ የግጥም፣ የጠቅላላ ዕውቀት… በአጠቃላይ 14 መፃሕፍትን በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች አሳትመዋል፡፡ በ1977 ዓ.ም “ዶን ኪሾቴ” በሚል ርዕስ ተርጉመው ባሳተሙት መጽሐፍ የትርጉም ባለቤትነት ክስ ተመርስቶባቸው ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ መቋጨቱን የሚያስታውሱት አቶ አስፋው፤ ይሄም በሕይወታቸው ከገጠሟቸው ፈተናዎች አንዱ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
በ1974 ዓ.ም “የኢትዮጵያ ደራሲያን አንድነት ማህበር” ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል፤ የኢትዮጵያ መፅሐፍ ቅዱስ ማህበር አባልና ፕሬዚዳንትም ሆነው አገልግለዋል፡፡
አቶ አስፋው በሚያዚያ 1922 ዓ.ም ሐረር ውስጥ ነው የተወለዱት፡፡ በ75 ዓመታቸው የህይወት ታሪካቸውን የሚያትት “እኔ ማን ነኝ?” የተሰኘ መፅሃፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ ደራሲና የንግድ ባለሙያ የሆኑት አቶ አስፋው ተፈራ ታሪካቸውን በመፅሃፍ ለማዘጋጀት ሰበብ የሆናቸው የልጆቻቸው ጉትጎታ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ሰው ራሱን ሆኖ ለመኖር ባለመቻሉና በተፈጥሮ የታደለውን የተሰጥኦ ድንበር ዘሎ በማለፉ ምክንያት ለበርካታ ግለሰባዊ፣ ማህበረሰባዊ፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ቀውሶች መፈጠር ምክንያት ሆኗል በማለት የሚጀምሩት አቶ አስፋው፤ ራስን ማወቅ ብዙ ጥረት የሚይጠይቅ ከባድ ነገር እንደሆነ በመጽሐፋቸው ያስረዳሉ፡፡
በሰው ልጅ ተፈጥሮ ላይ ጥናት ያደረጉ የስነ ልቦና ምሁራን፤ ጠባይና ፍላጎቱን በስድስት ከፍለው መድበውታል ይላሉ ደራሲው፡፡ ከተጨባጭ ነገር ይልቅ በንድፈ ሀሳብ ላይ የሚያተኩሩ ሰዎች፤ ህልምና ፍላጎታቸውን ለማሳካት ገንዘብ ማጠራቀም ላይ ትኩረት የሚያደርጉ የምጣኔ ሀብት ሰዎች፤ ለውበት ቅድሚያ የሚሰጡ ተፈጥሮ አድናቂ ሰዎች፤ በማህበራዊ አገልግሎት ላይ የሚያተኩሩ የማህበራዊ ጥናት ሰዎች፤ ችግሮች ሁሉ በብቁ አመራር ይወገዳሉ ብለው የሚያምኑ የፖለቲካ ሰዎች፤ እምነትና ተስፋቸውን በፈጣሪ ላይ አድርገው የሚንቀሳቀሱ የሃይማኖት ሰዎች በማለትም ይዘረዝሯቸዋል፡፡
በዚህች ምድር ላይ ለ75 ዓመታት ከኖሩ በኋላ “ራስን መመርመርና ማጥናት ከምንም በላይ ከባድና አስቸጋሪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ” የሚሉት ደራሲው፤ “ስለ እኔ የማውቀው ነገር ብዙና የተሟላ ሲመስለኝ ቢኖርም ራሴን ለመግለጽ ስሞክር ግን ስለራሴ ምንም እንደማላውቅ ተረዳሁ” ይላሉ፡፡
በ1953 ዓ.ም ከመሰረቱት ትዳር ሶስት ወንድና ሁለት ሴት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ እዚህ ደረጃ በመድረሳቸው ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑት እኚህ የንግድ ባለሙያና ፀሐፊ፤ “እኔ ማን ነኝ?” ለሚለው ጥያቄያቸው ራሳቸው መልስ ይሰጣሉ - በ283 ገፆችና በ20 ምዕራፎች ተቀንብቦ በተሰናዳው የህይወት ታሪክ መፃህፋቸው፡፡    

Read 2240 times