Saturday, 02 August 2014 11:45

የፍቺ ዘርፈ ብዙ ቀውሶች!

Written by  ከወንድወሰን ተሾመ
Rate this item
(5 votes)

(ከአልታ ምርምር፣ሥልጠናና ካውንስሊንግ)

          ሰሞኑን በኤፍኤም 98.1 አዲስ ጣዕም ፕሮግራም ላይ ገጣሚ ታገል ሰይፉ ፍቺ የፈፀሙ ሰዎች አንዱ ሌላውን የሚጠራበት አንድ ቃል እንደሌላቸውና ለመጠራራት ወይም ለሌላው ሰው ግንኙነታቸውን ለመንገር እንደሚቸገሩ  ገልፆ ወንዱ “የቀድሞ ሚስቴ”  ከሚል ይልቅ “ ፍችሪቴ” ማለት እንደሚችል፣ ሴቷ ደግሞ የቀድሞ ባሏን “የቀድሞ ባሌ” ከምትል ይልቅ በቀላሉ “ፍችራዬ” ማለት እንድትችል አዲስ ቃል አውጥቶላቸዋል፡፡
የፍችራው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ፊደላት የተገኙት “ፍች” ከሚለው ሲሆን  የመጨረሻዎቹ ሁለት ቃላት ደግሞ “ሙሽራው” ከሚለው ቃል ተገንጥለው የተወሰዱ መሆኑን ጠቅሶ የፍችሪትም እንዲሁ “ ፍች” ከሚለው ቃልና “ሙሽሪት” ከሚለው  የመጨረሻ ሁለት ፊደላት ተወስዶ “ፍችሪት” እንደተባለች ተናግሯል፡፡ “ከባዱን” ነገር “አቀለላቸው” ማለት ነው፡፡  ለኛም አቀለለልን ልበል?
ለመሆኑ ፍችራውና ፍችሪት ቀድሞውኑ ለምን ተፋቱ?
ፍችሪት ሚስት በነበረችበት ዘመን  ከፍችራው (ያኔ ባል ነበር ) ጋር የነበራትን የትዳር ግንኙነት እንደሚከተለው ትገልፃለች፡-
“ፍችራዬ ለቤቱ ገንዘብ በመስጠትም ሆነ የሚያስፈልገኝን ነገር በማሟላት ረገድ ችግር አልነበረበትም፡፡ ትልቁ ችግሩ የነበረው እኔን አለማመኑና ከፍተኛ የሆነ ጥርጣሬ በኔ ላይ መኖሩ ነው፡፡ እኔን ከሌላ ወንድ ስለሚጠረጥረኝ ከቤት መውጣት አይጠበቅብኝም። ቤት ውዬ ቤት አድሬ ከሌላ ወንድ እንደምማግጥ ያስባል፡፡ ሁለታችንም ሰራተኞች ነበርንና ጠዋት አብረን ወጥተን  መስሪያ ቤቴ በር ላይ በመኪና ያደርሰኝና በስራ ሰዓታት ብቻ  ተለይቼው ቆይቼ፣ በስራ መውጫ ሰዓት ከመስሪያ ቤት ደጃፍ ላይ ተቀብሎኝ ወደ ቤት እንሄዳለን፡፡ ቤት እንደደረስን የመጀመሪያ ስራችን እንደምታስበው ልብስ መቀየርና መተጣጠብ እንዳይመስልህ፡፡ እየተቻኮለ የዕለቱን ወሎዬን በተመለከተ ለመነጋገር እንደሚፈልግ ገልፆ፣ ጠዋት መስሪያ ቤቴ በር ላይ ካደረሰኝ ጀምሮ ከስራ እስከወጣሁበት ጊዜ ድረስ የነበረኝን የስልክ ልውውጥ፣ ያገኙሁትን ሰው፣ ከዚያ ሰው ጋር ምን እንደተነጋገርን፣ ስንነጋገር ምን አይነት ስሜት በሌላው ሰው ፊት ላይ እንደተነበበ፣ ከዚያ ምን እንዳደረግን ወዘተ ማለቂያ የሌለው ጥያቄ ይጠይቀኛል፡፡
ምንም እንኳን ደግና መልካም ሰው እንደሆነ  ባውቅም፣ ይሄ የእለት ተእለት ጭቅጨቃ ከፍተኛ ጭንቀትና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይከተኝ ጀመር። ለነገሩ በመስሪያ ቤቱም ከስራ ባልደረቦቹ ጋር ጥሩ ግንኙነት የለውም፡፡ በስራዬ ይቀናሉ፣ ሊያፈናቅሉኝ ያደባሉ፣የኔን ሥራ ሰርቀው ራሳቸው እንደሰሩት አድርገው ያቀርቡብኛል እያለ ይበሳጫል።
“ነገሩ እየባሰ ሲሄድ ከእሱው ጋር ተስማማንና ስራ ለቀኩኝ፡፡ የቤት እመቤት ሆንኩና ከቤት ሳልወጣ እውል ጀመር፡፡ ሆኖም ይሄም አላዳነኝም፤ በየአስር ደቂቃው በመስመር ስልክ እየደወለ ከማን ጋር እንደሆንኩ፣ ስልኩን ለማንሳት ‘የዘገየሁት’ ከ አንዱ ጋር እየማገጥኩ አንደሆነ፣ ምን ቢያደርገኝ አርፌ እንደምቀመጥ ወዘተ ይነዘንዘኝና እንደገና 10 ደቂቃ ሳይሞላ ደግሞ ይደውላል- በሞባይል እንዳይደለ ልብ በልልኝ፣ ከቤት እንዳልወጣሁ ለማረጋገጥ አስቦ ነው! ለመፀዳዳት እንኳን ወደ መታጠቢያ ቤት ከገባሁና ድንገት ከደወለ አለቀልኝ ማለት ነው፡፡ ለኔ ይሄ ቀላል አልነበረም፡፡  
በእጮኝነት ዘመናችሁ ይቀና ነበር?
“ወንድ አየሽ ብሎ ስንት ጊዜ አጩሎኛል መሰለህ - በአደባባይ፡፡ ግን በሁለታችንም ዘንድ ፍቅሩ ስለነበረ የሚቀናው ስላላገባኝ ነው፣ የሱ መሆኔን እርግጠኛ ስላልሆነ ነው፣ሲያገባኝ ጥርጣሬውንና ቅናቱን፣ ጭቅጭቁንም ጭምር እርግፍ አድርጎ ይተዋል የሚል እምነት ስለነበረኝ ምንም ሳላቅማማ አገባሁት፡፡
“ይገርምሃል - የሰርጉ እለት እኔ ደስተኛ ብሆንም እሱ ከመጠን በላይ ተናድዶና በሽቆ ነው የዋለው። መድረክ ላይ ቁጭ ብለን ሰዎች ወደ መድረኩ እየመጡ ደስታቸውን በሚገልጹበት ወቅት እንኳን በሁለታችንም ዘንድ የሚታወቁ  ወንዶች እኔን ሲጨብጡ ይናደድ ነበር።
እዛው መድረክ ላይ እጁን በቬሎው ውስጥ አሾልኮ ሁለቴ ቆንጥጦኛል። ከዚያም ያደረገው ነገር ቢኖር ከቀድሞ ጓደኞቼ በሙሉ ቀስ በቀስ እንድለያይና ብቻዬን እንድቀር ነው፡፡ እኔም ከጭቅጭቁና እሱን ለማረጋጋት በሚል ሰበብ እርግፍ አድርጌ ጓደኞቼን ተውኳቸው። የቤቴንም ሚስጥር ለመጠበቅ ብዬ እነሱን የተውኩበትን ምክኒያት እንኳን ፍቺ እስክፈፅም ድረስ አልነገርኳቸውም። ፍቺውን ከፈፀምን በኋላ በጣም የተጎዳሁት በመሃል በተፈጠሩት ሁለት ልጆቻችን ነው------- ፍችራዬ  ለምን እንደዚህ  አይነት ሰው እንደሆነና እንደሚጠረጥረኝ አላውቅም።----” ፍችሪት በሀዘን ስሜት ውስጥ ገባች፡፡
ፍችሪት ይህን ያህል ከነገረችን  ለጊዜው ይበቃታል። ቆየት ብለን ደግሞ እናገኛታለን፡፡ አሁን ስለ ፍችራው ችግር  ዝርዝሩን እንመልከት፡፡
የፍችራው ችግር ምንድነው?
የስነ ልቦና ባለሙያው ዝርዝር መረጃ ከወሰደ በኋላ የፍችራው ችግር  ጥጋብና ክፋት እንዳልሆነና (ፓራኖይድ) የስብዕና ቀውስ መሆኑን አረጋግጧል። በሳይኮሎጂስቶች ስምምነት መሰረት ይህ የስብዕና ቀውስ የሚከተሉት ምልክቶች አሉት፡፡
መሰረት ሳይኖር ሰዎች ይጠቀሙብኛል፣ ይጎዱኛል ወይም ያታልሉኛል ብሎ ይጠራጠራል።
ምክኒያት ወይም ማረጋገጫ  ሳይኖር  በወዳጆቹና በስራ ባልደረቦቹ ዕምነትና ታማኝነት ላይ በጥርጣሬ ሃሳብ ይያዛል፡፡
መረጃዎችንና ሃሳቦቹን ለሌላው ሰው ከመግለጥ ይቆጠባል። ምክኒያቱም መረጃዎቹ እሱን በጭካኔ ለማጥቃት ሊውሉ እንደሚችሉ  በመገመት ይፈራል።
በትናንሽ ነገሮችና ሁኔታዎች ውስጥ የተደበቁ አደጋዎችን ትርጉም ሰጥቶ ያነብባል።
ዘላቂ የሆነ ቂም ይቋጥራል። ይህም ማለት መጠነኛ የሆኑ ስድቦችንና ጉዳቶችን ይቅር ማለት ይቸገራል።
ለሌሎች ግልፅ ባልሆነ መልኩ በስሙና በማንነቱ ወይም በክብሩ ላይ ጥቃት ሊያደርሱበት እንደሚችሉ በማሰብ ፈጥኖ የማጥቃትና በንዴት የመገለጥ አዝማሚያ ያሳያል።
ምንም ማስረጃ በሌለው ነገር ተደጋጋሚና ቋሚ የሆነ ጥርጣሬ በሚስቱ ወይም በወሲብ አጋሩ ታማኝነት ላይ አለው።
ከላይ የተጠቀሰው የሥነልቦና ችግር በአብዛኛው በወንዶች ላይ እንደሚከሰት ጥናቶች የሚጠቁሙ ሲሆን በልጅነት ወይም በወጣትነት ዘመን  ከሚያጋጥም ብቸኝነት (solitariness)፣ ከአቻ ጋር የሚኖር ዝቅተኛ ግንኙነት(poor peer relationship)፣በትምህርት ዝቅተኛ ውጤት ማምጣት (low school performance)፣ በነገሮች ቶሎ መነካት (hypersensitivity ) ጋር እንደሚያያዝ ተጠቁሟል፡፡
ከጠቅላላ ህዝብ መካከል ከ 0.5% እስከ 2.5% የሚሆነው የዚህ ችግር ሰለባ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።  ከ85 ሚሊየን ህዝብ መካከል ከ425,000  እስከ2,125,000 ሰው በዚህ ስነልቦናዊ ችግር ይጠቃል እንደማለት ነው። ሆኖም ይህ ስነልቦናዊ ችግር በተለያዩ ተጨባጭ ምክኒያቶች የሚጠራጠሩ፣ የሚሰጉና በሌሎች ላይ እምነት የሚያጡ ሰዎችን አይመለከትም፡፡ ሆኖም “ያልጠረጠረ ተመነጠረ” የሚለውን ጥቅልል አባባላችንን በዚህ አጋጣሚ ልንሽረው ያስፈልጋል፡፡
ፍችሪት ስለ ልጆቿ ምን ትላለች?
“ልጆቻችን የ 4 እና የ 2 ዓመት ከ 10 ወር  ዕድሜ ያላቸው ህፃናት ናቸው፡፡ የመጀመሪያዋ ሴት ስትሆን ሁለተኛው ወንድ ነው፡፡ ከአባታቸው ጋር በጣም የሚቀራረቡ ሲሆን ከንዴቱና ከኔ ጋር ከነበረው ንጭንጭ ፋታ ሲያገኝ ከእነሱ ጋር ይጫወታል፣ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ያደርግላቸዋል፡፡ በጣም የሚገርመው ነገር አንዳንዴ እነዚህን ልጆች ከሌላ ወንድ እንደወለድኳቸው ያስባል። ሆኖም አባት ነኝ የሚል ስለጠፋ እንጂ አልፎ አልፎ የሚያነሳብኝና የሚዘገንነኝ ጉዳይ ነው፡፡ እንደዚህም ቢያስብ ግን ልጆቹን በጣም ይወዳል፣ጊዜም ይሰጣቸዋል።
“ምንም እንኳን ልጆቹ ከኔ ጋር ቢኖሩም አባታቸውን እንደበፊቱ የማግኘት እድል ስለሌላቸው በጣም ተጎድተዋል፡፡ ድንገት “አባዬ ናፈቀኝ፣ ለምን ጠፋ ወዘተ” የሚሉት የልጆቼ ጥያቄዎች እኔንም ያስለቅሰኛል። በተለይ ትልቋ ትተክዛለች፣ እንደ ድሮው የምግብ እና የጨዋታ ፍላጎት የላትም። ባህሪዋ በጣም ተለውጦብኛል፡፡ የወደፊቱም የልጆቼ ሁኔታ ያሳስበኛል፡፡”
ፍቺ በልጆች ህይወት ላይ ምን ተፅዕኖ አለው?
ፍቺ በልጆች ላይ የሚያመጣው ተፅእኖ በርካታ እንደሆነ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ በተደረገ ጥናት፤ ወላጆቻቸው በጋብቻ  ካሉ ወጣቶች ይልቅ ወላጆቻቸው በፍቺ የተለያዩ ወጣቶች ሲጋራ ማጨስን እንደሚለማመዱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአልበርታ ዩኒቨርሲቲ (University of Alberta) ጊዜ ዘለቅ ምርምር (longitudinal survey) መሰረት፤ በፍቺ ቤተሰብ ውስጥ ያለፉ ልጆች የተወሰኑቱ ከሌሎቹ ይልቅ ጭንቀት ይጠናወታቸዋል። በ2011 በዊስከንሲን ዩኒቨርሲቲ (University of Wisconsin) በተደረገ ጥናት ደግሞ እነዚህ ልጆች ማህበራዊ ክህሎቶች እንደሚጎድሏቸውና በአጠቃላይ በማህበራዊ ግንኙነቶቻቸው ላይ ችግር እንደሚገጥማቸው ጠቅሶ በጭንቀትና በዋጋ ቢስነት ስሜት (low self esteem) እንደሚሰቃዩ ጠቁሟል፡፡ ዩታ ዩኒቨርሲቲ (Univesity of Utha) ባጠናው ጥናት፤ እነዚህ ልጆች ካደጉ በኋላ የራሳቸውን ትዳር የመፍታት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው ብሏል፡፡
ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ኮንግረስ (World Congress of Families) ባጠናው ጥናት መሰረት፤ ፍቺ የሚፈጥረውን ተፅእኖ በአምስት ጎራ ከፍሎ ያስቀምጠዋል።
በቤተሰብ ደረጃ፡-
በልጆችና በወላጆች መካከል ያለን መልካም ግንኙነት ለዘለቄታው ያዳክመዋል /ይቀንሰዋል/። ይህም ማለት ትልቁ ፍቺ በባልና ሚስት መካከል ቢደረግም ትንሹ ፍቺ ደግሞ በወላጆችና በልጆች መካከል እንደተፈፀመ ይቆጠራል ይላል።
ፍቺ ልጆች ችግሮቻቸውን በሰለጠነ መልኩ መፍታት የሚችሉበትን አቅም ያዳክማል፣ ወላጆቻቸው ግጭቶችን መፍታት እንዳልቻሉ ሁሉ ልጆቻቸው ይህንኑ የአቅመቢስነት ባህሪ የመውረስ ዕድላቸው የሰፋ እንደሆነና ግጭትን በመደባደብና ሃይልን በመጠቀም የመፍታት ነገራቸው እንደሚጨምር ጥናቱ ይጠቁማል፡፡
ከጓደኞቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነቶች የማህበራዊ አቅም (Social competence) ያጣሉ። በዚህም አቅም ማነስ ምክኒያት በትምህርት ቤቶቻቸው የመደባደብ፣የመስረቅና ሌሎች ፀረ-ማህበራዊ ባህሪያት ይታይባቸዋል።
እነዚህ ልጆች በሌሎች እንደሚወደዱ ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡ የተቃራኒ ፆታ ፍቅርንም ለመጀመር እምነት የማጣት ችግር ይፈጠርባቸዋል።
ከጋብቻ በፊት በተለያዩ ስሜቶች ገፋፊነት ወሲብ የመፈፀምና የልጅ እናት ወይም አባት የመሆን፣ ከበርካታ ወንዶች ወይም ሴቶች ጋር ወሲብ የመፈፀም ባህሪን መለማመድ ሊገጥማቸው ይችላል።
በራሳቸው ትዳርም ፍቺን ለመፈፀም ይቀላቸዋል፡፡
በመንፈሳዊ ህይወታቸው ዙሪያ፡-
በቤተክርስቲያን ወይም በሃይማኖት ተቋማት ተገኝተው መንፈሳዊ ፕሮግራሞችን  ለመካፈል ዝቅተኛ ፍላጎት ያሳድራሉ።
በትምህርት ዙሪያ፡-
የልጆችን የመማር አቅም ያዳክማል፡፡ በተለይ በሂሳብ ትምህርት ደካማ እንደሚሆኑና ክፍል እንደሚደግሙ ተጠቁሟል፡፡
ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የመግባት ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው፡፡
በማህበረሰብ ደረጃ፡-
ወንጀልን ይጨምራል-የተደረገው ጥናት ፍቺ ወንጀልን የመጨመር አቅም እንዳለው ይጠቁማል፡፡
የዕፅና የአልኮል ተጠቃሚነት ይጨምራል-ጥናቱ፤ ልጆች ለእንጀራ እናት ወይም አባት የሚዳረጉበት ከፍተኛ እድል እንዳለ ጠቁሞ ይህም በልጆች ላይ ስነልቦናዊ ቀውስ እንደሚፈጥር ከዚህም ጋር ተያይዞ ልጆች አሉታዊ ባህሪያትን እንዲያዳብሩ ተፅእኖ አንደሚያሳድርባቸው ገልጿል።
በራስ ላይ የሚፈጠር ጫና ሰለባ ይሆናሉ፡-
ወዲያው ፍቺው ሲፈፀም በልጆች ላይ የስሜት፣የአዕምሮና የባህሪ ጉዳት ይጨምራል። ፍርሃት፣ ሀዘን፣ መገለል፣ በራስ የመተማመን ስሜት ማጣት፣ጭንቀት፣ብቸኝነት፣ድብርት ወዘተ ሊጠናወታቸው ይችላል። እነዚህ ስሜቶች ሊዘልቁም ይችላሉ፡፡
ራስን የማጥፋት ሃሳብ፡- በበርካታ ጥናቶች፤ ከጋብቻ መፍረስ ጋር ተያይዞ በልጆች ላይ የሚፈጠር ሃሳብ እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡
የጤና መታወክ መጨመር- ከጋብቻ መፍረስ ጋር ተያይዞ የልጆች አካላዊ ጤንነትም ይጎዳል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት በጥናት የተደገፉት ጉዳቶች በፍቺ ቤተሰቦቻቸው በተለያዩ ልጆች ሁሉ ላይ ይፈጠራሉ ማለት እንዳይደለ መገንዘብ ያስፈልጋል። በተለያዩ ምክኒያቶች የዚህ ጉዳት ሰለባ ሳይሆኑ በጤናማ ኑሮ ውስጥ የሚያልፉ ጥቂት ልጆች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
በፍቺ የተለያዩ ሰዎች ስለ ልጆቻቸው ሊያስቡ ይገባል፡፡ ሆኖም አንዳንዶች ለልጆቻቸው ደንታ ያላቸው አይመስሉም፡፡ ዋና ሥራቸው እልህ መያያዝና ልጆች ማሸሽ ነው፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ሰጎን የሚያወራ ክፍል አለ፡፡ ሰጎን በባህሪዋ እንቁላል ትጥልና እንቁላሎቿን በአሸዋ ውስጥ ትቀብራቸዋለች፡፡ የዱር አውሬ ቢረግጣቸው ደንታም የላትም፡፡ የራሷን ኑሮ ትቀጥላለች፡፡ አንዳንድ በዱር አውሬ ከመረገጥ የተረፉቱ እንቁላሎች ይፈለፈሉና የማደግ ዕድል ያጋጥማቸዋል። የሚገርመው ነገር ሰጎን ራሷን እንድትተካ ትልቅ የመውለድ ፀጋ ተሰጥቷታል፣ ነገር ግን ተፈጥሮዋ ሆኖ  ፀጋዋን አትጠቀምበትም፡፡ አንዳንድ ወላጆችም እንዲሁ ናቸው፡፡
ፍችሪት አንድ ነገር አስባለች፡-
ነገሩ የስነ ልቦና ቀውስ ከሆነና የትዳሩ መፍረስ በልጆቻቸው ህይወት ላይ ይህን ያህል ከባድ ችግር የሚያመጣ ከሆነ፣ ፍችራው በስንት ጉትጎታ አሁን የተቀበለውንና እየተከታተለ ያለውን የስነልቦና ህክምና መፍትሄ በማግኘት ካጠናቀቀ፣ ትዳሯን እንደገና ለመቀጠል አስባለች፡፡ ይሄ ውሳኔ የፍችራው ሙሉ ደስታ እንደሚሆን ምንም ጥርጣሬ የላትም፡፡
ውድ አንባቢያን፡-  ሰዎች ከላይ በተጠቀሰው ከባድ ችግር ብቻ ሳይሆን በውይይት ሊፈቱ በሚችሉ ችግሮች ፍቺ ይፈፅማሉ፡፡ በፍቺ ምክኒያት በልጆች ላይ የሚደርሰው ስነልቦናዊ ጉዳት ቀላል አይደለም። “ሁለት ዝሆኖች ሲጣሉ የሚጎዳው ሳሩ ነው” የሚለውን አባባል እዚህ ጋ መጥቀስ ያስፈልጋል። በየቦታው ያሉ  ፍቺ የፈፀሙ ሰዎች  እንደገና አብረው ለመኖር የማይችሉ ከሆነ የሚከተለውን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡-
በልጆች ዙሪያ የሚደረጉ ውሳኔዎች(የት ይኑሩ፣የት ይማሩ፣ምን ይልበሱ፣ምን ይብሉ፣ ምን ይጠጡ ወዘተ ውሳኔዎች) መሰረታቸው የልጆቹ ስሜት፣ፍላጎትና የወደፊት ህይወት  መሆን አለበት። ይህም ማለት የባል ወይም ሚስት ፍላጎት መሆን የለበትም። እልህ መገባባትም አያስፈልግም።
ልጆች አባታቸውን ወይም እናታቸውን (አብረው የማይኖሩት ወላጅ) በነፃነት የማግኘትና አግባብ በሆነ የጊዜ ገደብ ውስጥ በቋሚነት አብረውት እንዲያሳልፉ፣እንዲያወሩ እንዲጫወቱ፣ አላማቸውንና እቅዳቸውን እንዲያወሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በእኛ አገር አልተለመደም እንጂ ፍችሮች የጋራ ልጆቻቸውን በጋራ የሚያገኙበትና ለልጆቻቸው ያላቸውን  ፍቅር የሚገልጹበት ጊዜ ቢኖራቸው መልካም ነው፡፡
ፍችራው ስለ ፍችሪት ወይም ፍችሪት ስለ ፍችራው  መጥፎነት ፈፅሞ ለልጆቻቸው መናገር የለባቸውም፡፡ ፍችሪት ለልጆቿ እናት መሆኗ ፍችራውም ለልጆቹ አባት መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ልጆችን ከራሳቸው ወገን  ለማድረግ ስለሌላው ወገን መጥፎ የሚናገሩ ፍችሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ይህን በማድረጋቸው ልጆቻቸውን ጤናማ በሆነ መልኩ  የራሳቸው ሊያደርጓቸው አይችሉም፡፡
ውድ አንባቢያን፤ በፍችራውና በፍችሪት “ገፀ ባህሪ”  ስለ ፓራኖይድ ስብዕና ቀውስ ተነጋግረናል፡፡ ለአዳዲሶቹ  ቃላት ታገል ሰይፉን አመስግነን በዚሁ ብናበቃስ? ቸር እንሰንብት!!
(ፀሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል)

Read 5684 times