Saturday, 02 August 2014 11:40

“…ጋቢዬንና ዱላዬን ከወሰደብኝ በኋላ አላምነውም…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አንድ ወዳጄ የሚያዘወትረው ምግብ ቤት አለ። እናላችሁ…አንድ ቀን ከተገለገለ በኋላ ይከፍልና ይወጣል፡፡ ቤቱ ደርሶ የተመለሰለትን ሲያይ ወደ አሥራ ስምንት ብር ገደማ ጎድሎታል፡፡ በማግስቱ ሄዶ “አጎደላችሁብኝ…” እንዳይል አስቸጋሪ ነው። ወንድም፣ ወንድሙን በማያምንበት ዘመን ቢናገር እንደ አጭበርባሪ የሚቆጠረው እሱ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ብሩንም ተበልቶ ‘ስለማያምናቸው’ ሁለተኛ እዛ ቤት ላለመሄድ ወስኗል፡፡
እናላችሁ…አስቸጋሪ ዘመን ነው.፡ በዚህም በዚያም ለተወሰነ ጊዜ እምነታችሁን ጥላችሁበት የነበረው ሰው ወይ ድርጅት በአንድ ጊዜ ተገልብጦ ሲያሞኛችሁ ታገኙታላችሁ፡፡ የሁሉ ነገር አልፋና ኦሜጋ ‘ገንዘብ፣ ገንዘብና ገንዘብ ብቻ’ ሆነና ጥላችንን የማናምንበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ዘመዶቹን ሊጠይቅ አገር አቆራርጦ እየሄደ ነው፡፡ እናላችሁ…በመንገዱ ላይ ተከዜ ወንዝን መሻገር ነበረበት፡፡ መሻገሪያ ቦታ ሲደርስም ውሀው ብዙም ስላልነበረ በልቡ ሙሉነት ገባ፡፡ ከዛላችሁ…ግማሽ መንገድ ያህል እንደሄደ ከየት እንደመጣ ሳይታወቅ ውሀው እየተገማሸረ መጣላችሁ። ሰውየውንም መሀል ላይ አገኘው፡፡ መጀመሪያ ጋቢውን ወሰደበት። ቀጥሎ ደግሞ ዱላውን ወሰደበት፡፡ ሰውየውም እያዘነ መንገዱን ቀጠለ፡፡
ከጥቂት ወራት በኋላ ይሄ ሰው ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ራቅ ወዳለ ቦታ ሲሄዱ ተከዜ ወንዝ ይደርሳሉ። አሁንም ውሀው ብዙም አልነበረም፡፡ ታዲያማ ጓደኞቹ ገቡ፡፡ እሱ ግን ዳር ዳሩን እየሄደ በዱላው ውሀውን ነካ፣ ነካ ያደርጋል፡፡ ይሄኔ ሰዎቹ “ግባ እንጂ፣ ምን ታመነታለህ!” ይሄኔ ምን አለ መሰላችሁ… “ተከዜ ጋቢና ዱላዬን ከወሰደ በኋላ አላምነውም፡፡” አሪፍ አይደል፡፡
እናማ…እንደተከዜ “…ጋቢዬንና ዱላዬን ከወሰደብኝ በኋላ አላምነውም…” የምንልባቸው ምክንያቶች እየበዙ ነው፡፡
ለምሳሌ የሆነ ጤና ችግር ይገጥምና ክሊኒክ ትሄዳላችሁ፡፡ ሀኪማችሁ ደባብሶ ምናምን “ታይፎይድ ይዞሀል…” አይነት ነገር ይልና ኪኒን በቁና ያስታቅፋችኋል፡፡ ክኒኑ ሲያልቅ ‘ታይፎይድ’ ግን ሙጭጭ ይላል፡፡ ሌላ ሀኪም እውነተኛ ‘በሽታውን’ ያገኝላችሁና ይሻላችኋል፡፡ እናማ…በሌላ ጊዜ የሆነ ሰው “ታይፎይድ ይዞሀል…” የተባላችሁበትን ክሊኒክ ስም ጠርቶ “ይደክመኛል የምትለውን ለምን እነሱ ክሊኒክ ሄደህ አትታየውም…” ሲል መልሱ ምን መሰላችሁ… “…ተከዜን ጋቢዬንና ዱላዬን ከወሰደብኝ በኋላ አላምነውም…”
አንዳንዴ የትም አገር ይሁን የትም መቼም ቢሆን የማታምኗቸው አይነት ሰዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ‘ቦተሊከኞች!’ ለህ ነው ወንዝ በሌለበት “ድልድይ እናስገባለን…” አይነት ነገር የሚሉ ቦተሊከኞች ዓለምን የሚጫወቱባት፡፡ የምር እኮ…እውነተኛዋ ዓለም በእነ ቢቢሲና አልጀዚራ የምናያት ብቻ አይደለችም፡፡ ‘ቦተሊካ’ የሀቅ የምናምን ጉዳይ ሳይሆን የጨዋታን ህግ የማወቅ ጉዳይ ነው፡፡
‘መሬት ላይ የሚተኛ ከአልጋ አይወድቅም’ የሚሉት ነገር አለ፡፡ የጨዋታው ህግ መሬት ላይ መተኛት ሲሆን ‘አልጋ ላይ የሚወጣ’ ‘ቦተሊከኛ’ ሄዶ “ፍራሽ አዳሽ…” እያለ ቢጮህ ይሻለዋል፡፡ ‘የጨዋታውን ህግ’ አላወቀማ!
የ‘ቦተሊካ’ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ፖለቲከኛው ምርጫ ዘመቻ ላይ ሆኖ ህዝቡ እንዲመርጠው ንግግር እያደረገ ነው፡፡ “ወገኖቼ፣ እኔ ለዚች አገር ዕድሜ ልኬን ታግዬላታለሁ፡፡ አልጋ ላይ ተኝቼ አላውቅም፣ መኝታዬ ጦር ሜዳ ነበር፡፡ ቀና ስል የማየው የቤት ጣራ ሳይሆን የበረሀውን ሰማይ ነው። በዱር በገደሉ ስማስን ነው የኖርኩት፡፡ ብዙ ጦር ሜዳዎች ከመዋሌ የተነሳ የረገጥኩት መሬት ላይ ዱካዬ በደም ነው የታተመው፡፡ ስለዚህ ምረጡኝ፣” ይላል፡፡
ይሄኔ ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ ምን አለ መሰላችሁ… “ለአገርህ በጣም ብዙ ውለታ ነው የዋልክላት፡፡ ይሄን ሁሉ ዘመን ስላገለገልካት ደግሞ ደክሞሀል፡፡ አሁን ቤትህ ሄደህ ረጅም እረፍት ውሰድ፡፡ ግዴለም፣ እኛ ሌላ ሰው እንመርጣለን፡፡”
ስሙኝማ…ከአልጋ መውደቅ የሚሉት ነገር ካነሳን አይቀር የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ! እናላችሁ…ዘንድሮ መኪናው…ግንቡ… (ቂ…ቂ…ቂ…) የቢሮው ሶፋ ምናምን ሁሉ ‘የአልጋ ምትክ’ በሆነበት ጊዜ (የሚባለውን ነው)…አለ አይደል… ኑዛዜው “ከአልጋ ወድቂያለሁ…” ከሚለው ወደ ሌላ ይለወጥልን፡፡ ልክ ነዋ… “አልጋ” የሚለው ቃል ወይም “የመኪና ወንበር፣“ “የቢሮ ጠረጴዛ፣” “የሰው ቤት ግንብ (ቂ…ቂ…ቂ…)” ምናምን እየተባለ ‘ግልጥና ግልጥ’ ይሁንልንማ!  ወይንም “ከአልጋ ወድቂያለሁ…” ስንል…አለ አይደል… የንስሀ አባቶቻችን “አልጋ ስትል ግልጽ አድርገው…” ምናምን ብለው ማብራሪያ ይጠይቁን። ልክ ነዋ…የእንትን ፋብሪካ ስፖንጅ ፍራሽና የቶዮታ ኤክስኪዩቲቭ ‘ፍራሽ’ አንድ ነው! (እንትናዬ… እንግዲህ ሳይደርሱብሽ ሰው ላይ አትድረሺ! አሁን አንቺን የተናገረሽ አለ! እኔ የምለው…እዚች ግንባርሽ ላይ…ግንብ የገጨሽ መሰላሳ!) እናላችሁ…“ደግነቱ ‘ጉዞው’ ይለያይ እንጂ መድረሻው አንድ መሆኑ…” እንደማይጠፋን ልብ ይባልማ!
የምር ግን ምን መሰላችሁ…‘በዛኛው ጉዳይ’ ላይ የተገኘችውን አጋጣሚና ‘ስፔስ’ አብቃቅቶ በመጠቀም የሚወዳደረን እየጠፋ ነው፡፡ እኔ የምለው፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በነጠላ ተከናንቦ ‘ተራ መጠበቅ’ ፊልም ላይ እንኳን ላናየው ነው ማለት ነው! ገባ፣ ጸጥና ደብዘዝ ያሉ አካባቢዎች ኮሽታ በዛባቸዋ! ልጄ…ማን ፈረንጆቹ ‘ፎረ ኤ ላውዚ ቱ ሚኒት ፒሪዬድ’ ለሚሉት ሁለት ሰዓት ሙሉ ሲጠብቅ ያመሻል!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ የነጠላን ነገር ካነሳን አይቀር ከዚህ በፊት ያወራናትን እንድገማትማ፡፡
እሱ ሆዬ እንትናዬውን ‘ለዝግ ችሎት’ ይዞ የሚሄድበት የተለመደ ቦታ አለው፡፡ አለ አይደል…ከዘብ ጀምሮ ሰላምታ እየሰጡ የሚገቡበት አይነት ቦታ፡፡ እናላችሁ…በተለያዩ ምክንያቶች ለጥቂት ወራት ይጠፋና አንድ ቀን ከጁሊየቱ ጋር ይሄዳል። ታዲያላችሁ… ገና ሲገባ መቀመጫው ላይ ጥንድ፣ ጥንድ ሆኖ ተደርድሮላችኋል፡፡ ታዲያላችሁ …ሴቶቹ ሁሉ በነጠላ ተከናንበዋል፡፡ ይሄን ጊዜ አንዱን ሠራተኛ ጠርቶ ምን ቢለው ጥሩ ነው…
“አንተ፣ መቼ ነው ይሄ ቤት ክሊኒክ የሆነው!” ምን ያድርግ!…በኋላ ሁሉም ‘ሎካሉ’ም ሆነ የማሌዥያው ጨርቃ ጨርቅ ከየፍራሹ ስር እየተጎተተ ሊሰበሰብ፣ እንዲህ በሦስት ዙር የተጠቀለለ ነጠላ በትራስ ልብሱ ውስጥ ተወሽቆ ሊገኝ (ቂ…ቂ…ቂ…) የምን ክንብንብ ማብዛት ነው!
እናላችሁ…መታመን፣ መተማማን አስቸጋሪ የሆነበት ዘመን ነው፡፡ ስንት ዓመት በሀይወታችሁ ጭምር ታምኑት የነበረ ሰው ድንገት ተገልብጦ ቁጭ ይልና እምነታችሁን አመድ የሚያደርግ ነገር ይፈጽምባችኋል፡፡ ስንት ዘመን “ወዳጄ ሆዴ” እያላችሁ ስታጫውቱት የነበረውን ምስጢር ወስዶ አደባባይ ይዘረግፍላችኋል፤ በሺዎች ብር ስታበድሩትና ስታግዙት የኖራችሁት ሰው መቶ ብር በማትሞላ ገንዘብ ሲክዳችሁ ታገኙታላችሁ፤ ስንት ዓመት እንደ እህት ሲንከባከባት የነበረች እንትናዬአችሁን ድንገት “እነሆ በረከት እንባባል…” ብሎ ሲያስቸግር ታገኙታላችሁ፤ ስንትና ስንት ንብረት በአደራ እንዳልሰጣችሁት አንድ ቀን በትንሽ ነገር አደራችሁን ቀርጥፎ ሲበላ ታገኙታላችሁ….እናላችሁ ዘንድሮ “…ጋቢዬንና ዱላዬን ከወሰደብኝ በኋላ አላምነውም…” የሚያሰኙ ነገሮች እየበዙ ነው።
ሰውየው ከልብ ጓደኛው ጋር እያወራ ነው፡ የሆነ ምስጢር ቢጤ ኖሮት ለጓደኛው ግን ሊነግረው አልፈለገም፡፡ ጓደኝየውም “ለምን አትነግረኝም!”
“አልነግርህም፡፡”
“እኮ፣ ለምንድነው የማትነግረኝ?”
“በቃ አላምንህም፣ ሄደህ ምስጢሩን ልታወራ ትችላለህ፡፡”
“እና እኔን ምስጢር በመጠበቅ አታምነኝም ማለት ነው?”
“እንኳን አንተን ሚስቴን ምስጢር ታወጣለች ብዬ እጠረጥራታለሁ፣” ይላል ሰውየው፡፡ ይሄኔ ጓደኝዬው ምን ቢል ጥሩ ነው…“እሷን እንኳ እኔም ምስጢር ታወጣለች ብዬ እፈራታለሁ!” እንዲህም አለላችሁ! የሞኝ ነገር…ራሱ አፍረጥርጦት ቁጭ አለ!
እናላችሁ ዘንድሮ “…ጋቢዬንና ዱላዬን ከወሰደብኝ በኋላ አላምነውም…” የሚያስብል ነገር መአት ነው። ህሊና የሚባለው ነገር የት እንደጠፋ ግራ በገባን ዘመን መካካድና አለመተማመን ይህን ያህል መብዛቱ ላይገርም ይችላል፡፡ እንደ ለመድነው “የባሰ አታምጣ!” ብለን መጠበቅ ነው፡፡
የህሊናን ነገር ካነሳን ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው የስነ ልቡና ባለሙያ ዘንድ ሄዶ እንዲህ ይላል… “በሴቶች አካባቢ አጉል ጠባዮች እያሳየሁ ነው፡፡”
“ምን አይነት አጉል ጠባይ?”
“በቃ፣ ያገኘኋትን ዘልዬ መሳም ነው፡፡ እሺ ካለችኝም ማንኛዋም ሴት ብትሆን ያው የተለመደው ቦታ ይዤ መሄድ ነው፡፡”
“እና ዋናው ችግሬ የምትለው ምንድነው!”
“በቃ፣ ህሊናዬ አስቸገረኝ፡፡ አንዷን ከሳምኩ ወይም ሌላ ነገር ካደረግሁ በኋላ ህሊናዬ እንደ ጉድ ይቆጠቁጠኛል፡፡”
“አሀ… እኔ የስነ ልቡና ባለሙያ ስለሆንኩ ቁርጠኝነትህን እንዳጠናክርልህ ነው የምትፈልገዋ?”
“አይደለም፣ ህሊናዬን ብትችል ሙሉ ለሙሉ እንድታስወግድልኝ፣ ባትችል ደግሞ ለምንም ነገር ግድ የማይሰጠው ህሊና እንድታደርግልኝ ነው የምፈልገው።”
ልፋ ሲለው ነው ባለሙያ ዘንድ የሄደው፡፡ እዚህ አገር አይመጣም ነበር! ወላ መቆጥቆጥ የለ፣ ወላ መጠዝጠዝ የለ…እንደውም “ህሊና የምትሉት ነገር ምንድነው?” ብሎ እንዲጠይቅ እናደርገው ነበር፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4089 times