Saturday, 02 August 2014 11:23

ኢቦላ - ሰሞንኛው የዓለም ስጋት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

በ11 የአፍሪካ አገራት ተሰራጭቷል

          ባለፈው ማክሰኞ ማለዳ… ሲኤን ኤን ከወደ ሴራሊዮን አንዳች አሳዛኝ ነገር ስለመከሰቱ ዘገበ፡፡ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር በሴራሊዮን የተከሰተውን አሰቃቂ የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ ለመግታት ሌት ተቀን ደፋ ቀና ሲሉ ከነበሩት ታዋቂ ሃኪሞች አንዱ ሴራሊዮናዊ ዶ/ር ሼክ ሁማር ካሃን ሞቱ፡፡ የአገሪቱ መንግስት በህክምናው መስክ ከሚኮራባቸው ዜጎቹ የመጀመሪያው እንደሆኑ በይፋ የሚናገርላቸውና “ብሄራዊ ጀግናዬ” ብሎ የሰየማቸው ታላቅ ሰው፤ ኢቦላን በመሳሰሉ በቫይረስ የሚከሰቱ በሽታዎች ህክምና ዘርፍ በአለማችን ስማቸው ጎልቶ ከሚጠቀስ ቀዳሚ የህክምና ሊቃውንትና ባለሙያዎች አንዱ የነበሩት ሃኪም አረፉ፡፡ ከአገሪቷ መዲና ፍሪታውን 185 ማይሎች ርቃ በምትገኘው ኬኔማ የተባለች ከተማ ሆስፒታል ውስጥ የኢቦላ ህክምና የሚሰጠውን ቡድን በመምራት ከፍተኛ ስራ ተጠምደው የሰነበቱት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኢቦላ ተጠቂዎችን ከሞት ለማዳን አልህ አስጨራሽ ትግል ሲያደርጉ የነበሩት ዶ/ር ካሃን፣ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነበር፣ ህመም ቢጤ ተሰምቷቸው እንደምንም ስራቸውን ገታ አድርገው ለማረፍ ወደ አልጋ ያመሩት፡፡

ህመሙ ግን እንዳሰቡት ቀላልና ቶሎ የሚድን አልነበረም፡፡ እያደር ባሰባቸው፡፡ ካሊሁን በምትባል ከተማ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ተኝተው፣ በድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ህክምና ሲደረግላቸው ቢቆዩም አልዳኑም፡፡ ታዋቂው ሴራሊዮናዊ የኢቦላ ሃኪም በ39 ዓመታቸው ሞቱ፤ የሞታቸው ሰበብ ደግሞ ኢቦላ መሆኑ ታወቀ - ሲታገሉት የሰነበቱት ቀሳፊ በሽታ፡፡ ይህ ድንገተኛ መርዶ፣ በኢቦላ ወረርሽኝ የተመቱ የምዕራብ አፍሪካ አገራትን ብቻም አይደለም ያስደነገጠው፡፡ ከአራት ወራት በፊት በጊኒ አሃዱ ብሎ ጀምሮ ወደ ላይቤሪያ የዘለቀው፣ ፍጥነቱን ጨምሮ ወደ ሴራሊዮን የተሻገረው ይህ ክፉኛ አሰቃይቶ ገዳይ ቫይረስ፣ ድንበር ሳያግደው መሰራጨቱን ቀጥሏልና፣ የዶ/ሩ ሞት በሌሎች አገራት ብሎም አህጉራት ለሚኖሩ ዜጎች የችግሩን መባባስ የሚመሰክር መርዶ ነበር የሆነው፡፡ አዎ!... አሁን በታሪክ እጅግ አደገኛው የተባለለት የኢቦላ ወረርሽኝ አለማችንን ጭንቀት ውስጥ ከቷታል፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት ከአስር ቀናት በፊት ነበር፣ በምዕራብ አፍሪካ በሚገኙ አገራት ከ800 በላይ ሰዎች በኢቦላ በሽታ ተይዘው በመሰቃየት ላይ እንደሚገኙ በይፋ ያስታወቀው፡፡

ድርጅቱ በወቅቱ ይህን ይበል እንጂ፣ ሲኤንኤን ግን የታማሚዎች ቁጥር ከ 1 ሺህ 200 በላይ እንደሚሆንና ቫይረሱም ከአገራቱ አልፎ በስፋት በመሰራጨት የአህጉሪቷ ብሎም የዓለም ስጋት ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች የሰጡትን አስተያየት በመጥቀስ አበክሮ ተናግሮ ነበር፡፡ እንደተባለውም ኢቦላ የዓለም ስጋት ለመሆን የፈጀበት የቀናት ጊዜ ብቻ ነበር፡፡ በምዕራብ አፍሪካ የተቀሰቀሰውና እስካለፈው ሳምንት ድረስ በአካባቢው 672 ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረገው የኢቦላ ወረርሽኝ፣ አሁን የመላ አለም ሰሞንኛ የጭንቀት ምንጭ ሆኗል፡፡ ዛሬ ኢቦላ የአንዲት አህጉር ሶስት አገራት ራስ ምታት ብቻም አይደለም፡፡ የቶጎው አየር መንገድ ኤስካይ፣ ቫይረሱን እንዳያሰራጭ በመስጋት ወደ ሴራሊዮንና ወደ ላይቤሪያ የሚያደርጋቸውን በረራዎች ሙሉ ለሙሉ አቋርጧል፡፡ በናይጀሪያዋ ሌጎስ የኢቦላ ሟቾች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን ተከትሎ፣ በመላ አገሪቱ የወረርሽኝ ስጋት አንዣቧል፡፡ ታላቁ የአገሪቱ አየር መንገድ አሪክ ኤርም፣ ቫይረሱን ፍራቻ ወደ ላይቤሪያ ድርሽ ላለማለት ምሏል፡፡ ቫይረሱ እንደተፈራው በየአቅጣጫው በመሰራጨት የአገራትን ድንበር ተሻግሮ እየገባ እንደሆነ በርካታ የዓለማችን መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው፡፡ ዩኤስ ቱዴይ ከትናንት በስቲያ ባሰራጨው ዘገባ እንዳለው፣ የእንግሊዝና የሆንግ ኮንግ መንግስታት ከሰሞኑ የበሽታው ምልክቶች የታዩባቸውን የአውሮፕላን መንገደኞች በፍጥነት በመያዝ በተከለለ ቦታ ውስጥ እንዲቀመጡና ቫይረሱ ወደሌሎች እንዳይዛመት ለማድረግ አፋጣኝ እርምጃ ወስደዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ፣ ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ፣ የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ አየር መንገዱ ከምዕራብ አፍሪካ በሚመጡ መንገደኞች ላይ ጠበቅ ያለ የጥንቃቄ የማጣራት ስራ እንደሚጀምርና ለበረራ ሰራተኞቹ ስለ በሽታው ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚያስችላቸው ስልጠና መስጠቱን ገልጧል፡፡ የእንግሊዝ የጤና ሚኒስቴር ባለፈው ረቡዕ ከናይጀሪያ በመነሳት በፓሪስ አድርጎ ወደ በርሚንግሃም የገባ አንድ ግለሰብ የበሽታው ምልክቶች ታይተውበት በሃኪሞች እንዲያዝ ቢደረግም፣ ኢቦላ እንደሌለበት ተረጋግጧል፤ እስካሁንም በአገሪቱ የኢቦላ ታማሚ አልተገኘም ቢልም፣ ብዙዎች ግን መስጋታቸውን አላቋረጡም። የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ጸሃፊ ፍሊፕ ሃሞንድ፣ በዚያው ዕለት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ከፍተኛ ባለስልጣናትና ባለሙያዎች ያሳተፈና ኢቦላን ወደ አገሪቱ እንዳይገባ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከረ አስቸኳይ ስብሰባ ያደረጉትም ጉዳዩ ስላሰጋቸው ነው፡፡ በሩቅ ያለችው አሜሪካም ብትሆን፣ ከወደ አፍሪካ የተነሳው መቅሰፍት ዜጎቿን እንዳያገኝባት ሰግታለች፡፡ ከላይቤሪያ በመነሳት ሚኒሶታ ውስጥ በተደገሰው የልጁ ልደት ላይ ለመገኘት ጓጉቶ ወደ ሚኒሶታ ሊጓዝ የተሰናዳው ዜጋዋ ፓትሪክ ሳውየር፣ ሌጎስ ውስጥ አውሮፕላን ውስጥ እያለ በኢቦላ ለሞት መዳረጉን ስትሰማ ደግሞ ስጋቱ ጨምሮባታል፡፡ በዚህም አላበቃም፡፡ በላይቤሪያ መዲና ሞንሮቪያ የህክምና እርዳታ በማድረግ ላይ የነበሩ ሌሎች ሁለት ዜጎቿ በኢቦላ ተይዘው እንደሚሰቃዩ ተረጋገጠ፡፡

እንዲህ ያለው መጥፎ ወሬ ያስደነገጣት አሜሪካ፣ በሰው አገር ያሉ ዜጎቿ ጉዳይ ቢያሳዝናትም፣ አገር ቤት ያሉት ግን እንዳይሰጉ እየመከረች ነው፡፡ ሲዲሲ የተባለው የአሜሪካ የጤና ተቋም ባለፈው ሰኞ በሰጠው መግለጫ፣ በአገሪቱ ይህ ነው የሚባል የኢቦላ ወረርሽኝ ስጋት እንደሌለ አረጋግጧል፡፡ ይህም ሆኖ ግን በሽታው አደገኛ በመሆኑ መጠንቀቅ ይበጃል ብሏል ተቋሙ፡፡ በሽታው ከተከሰተባቸው የአፍሪካ አገራት የሚመጡ መንገደኞችን ወደ አሜሪካ አለማስገባት ሁነኛ መከላከያ መላ ነው ይላሉ- የሲዲሲ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ዶ/ር ማርቲ ሴትሮን፡፡ በቅርቡ ከእነዚያ አገራት የመጡና የኢቦላ ምልክቶች የተሰሟቸው ሰዎችም፣ ዛሬ ነገ ሳይሉ በአፋጣኝ ወደ ህክምና መሄድ እንደሚኖርባቸው ዶክተሩ መክረዋል፡፡ በአገራቱ የሚኖሩ ዜጎችም፣ የበሽታውን መተላለፊያ መንገዶች ጠንቅቀው በመረዳት ራሳቸውን እንዲጠብቁ ተናግረዋል፡፡ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ጸሃፊ ፍሊፕ ሃሞንድን ጠቅሶ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ሰሞኑን እንደዘገበውም፣ በመስፋፋት ላይ የሚገኘው የኢቦላ ወረርሽኝ ለእንግሊዝም ሆነ ለሌሎች የአውሮፓ አገራት ከፍተኛ ስጋት ነው፡፡

በሬዲንግ ዩኒቨርሲቲ ታዋቂ የህክምና ባለሞያ የሆኑት ዶ/ር ቤን ኒውማን በበኩላቸው፣ ኢቦላ በአገረ እንግሊዝ የመከሰት እድሉ ከፍተኛ በመሆኑ ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ ማስጠንቀቃቸውንም አስታውሷል፡፡ ጉዳዩ ያሰጋው የአውሮፓ ህብረትም፣ ወረርሽኙ ውቅያኖስ ተሻግሮ አሰቃቂ ጥፋት ሊያደርስ የማይችልበት ዕድል የለም ብሏል፡፡ የህብረቱን ከፍተኛ ባለስልጣን ሰቅሶ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንዳለው፣ ከሰሞኑ ስፔን ውስጥ አንድ ዜጋ በኢቦላ ተጠርጥሮ አፋጣኝ የህክምና ክትትል ተደርጎለታል፡፡ ግለሰቡ እንደተፈራው ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ ቢረጋገጥም፣ በሌሎች የአውሮፓ አገራት የበሽታው ምልክት የሚታዩባቸው ሰዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱንና አገራቱ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ህብረቱ መምከሩንም ዘገባው ያሳያል፡፡ ህብረቱ አባል አገራቱን ከወረርሽኙ እንዲጠነቀቁ ከማሳሰብ አልፎ፣ ወረርሽኙን ባለበት ለመግታት ችግሩ ወደ ተከሰተባቸው የአፍሪካ አገራት ከላከው 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዩሮ በተጨማሪ ሁለት ሚሊዮን ዩሮ የእርዳታ ገንዘብ እንደሚልክ፣ ሃኪሞችንም ወደ አገራቱ በብዛት እንደሚያሰማራ አስታውቋል፡፡

በሽታው ኢቦላ ነውና፣ እርግጥም የመንግስታቱ ስጋት ተገቢነት ያለው ነው፡፡ ኢቦላ ምንም አይነት ክትባት ያልተገኘለትና ይህ ነው የሚባል ህክምና የሌለው ገዳይ በሽታ ነው፡፡ ብርድ ብርድ በማለትና በማንቀጥቀጥ ጀምሮ፣ የማያቋርጥ ትውከትንና ተቅማጥን በማስከተል በአፋጣኝ ለከፍተኛ ስቃይ የሚዳርገው ይህ አሰቃቂ በሽታ፣ ለህልፈተ ህይወት ሲያበቃ ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ በዚህ ቫይረስ ከተጠቁ ታማሚዎች፣ 90 በመቶ ያህሉ መጨረሻቸው ሞት እንደሚሆን ይነገራል፡፡ የቫይረሱን የመዛመትና ሰዎችን የማጥቃቱን ፍጥነት ከፍተኛ ያደረገው ደግሞ የሚተላለፍበት መንገድ ነው፡፡ ሽንት፣ ላብ፣ ደምና አክታን የመሳሰሉ የሰውነት ፈሳሾች አማካይነት የሚደረግ የአካል ንክኪ፣ በሽታውን ከታማሚው ወደ ጤነኛው ሰው በአፋጣኝ ያስተላልፋል፡፡ ወረርሽኙ የተቀሰቀሰባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገራት፣ በቂ የህክምና አገልግሎትና መሰረተልማት በአግባቡ ያልተሟላላቸው መሆናቸው ችግሩን የከፋ እንደሚያደርገው እየተነገረ ነው፡፡ ሲኤንኤን እንዳለው፣ ወረርሽኙ በፍጥነት በመሰራጨት የ11 የአፍሪካ አገራትን ገፈት ቀማሽ አድርጓል፡፡ መሰራጨቱንም ቀጥሏል፡፡ ዓለምም በዚህ ቀሳፊ በሽታ ስጋት ተውጣ ሰንብታለች፡፡

Read 5329 times