Print this page
Saturday, 02 August 2014 11:16

ሾፌር አልባ መኪኖች በእንግሊዝ አገልግሎት ላይ ሊውሉ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

         የእንግሊዝ መንግስት ያለ አሽከርካሪ በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ መኪኖች ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ በአገሪቱ መደበኛ መንገዶች አገልግሎት ላይ እንዲውሉ መፍቀዱን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ የተሻሻለ ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑት እነዚህ መኪኖች፣ ተሽከርካሪዎች በሚበዙባቸው መንገዶች ላይ ያለ አሽከርካሪ ራሳቸውን ችለው መጓዝ፣ ፍጥነታቸውን መመጠን፣ አመቺ አቅጣጫዎችን መምረጥና መሰል ስራዎችን መከወን የሚችሉ ናቸው ተብሏል፡፡ የሌሎችን ተሽከርካሪዎች ሁኔታ ግምት ውስጥ ባስገባና ለአደጋ በማያጋልጥ መልኩ ራሳቸውን ችለው እንደሚንቀሳቀሱ የተነገረላቸው እነዚህ መኪኖች፣ በእያንዳንዷ ሰከንድ እንቅስቃሴያቸው አቅጣጫ ጠቋሚ ቴክኖሎጂዎችንና የሳተላይት ካርታዎችን እንደሚጠቀሙ ተገልጿል፡፡

ሾፌር አልባዎቹ መኪኖች አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸውን የሚቆጣጠር ኮምፒውተርና በሁሉም አቅጣጫ ያለውን ሁኔታ በማሳየት አካሄዳቸውን በተገቢው መንገድ እንዲያስተካክሉ የሚያግዟቸው ካሜራዎች የተገጠሙላቸው ናቸው። መኪኖቹ አገልግሎት ላይ ከመዋላቸው በፊት ባሉት ጊዜያት የሚመለከታቸው የአገሪቱ የትራንስፖርት ተቋማት በዘርፉ ይሰራባቸው የነበሩ የመንገድ ደህንነትና የተሽከርካሪ አጠቃቀም ህጎችን እነዚህን አዳዲስ ሾፌር አልባ መኪኖች ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ እንዲያሻሽሉ ተጠቁሟል፡፡ የአገሪቱን ኢኮኖሚና ማህበረሰብ ወደ አዲስ ምዕራፍ የማሸጋገር ዕድል ይፈጥራል የተባለው ይህ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ የሚውልበትን መንገድ በተመለከተ፣ የአገሪቱ የትራንስፖርት ዘርፍ መሃንዲሶችና የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተሳተፉበት ጥናት ሲደረግ መቆየቱንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

እንግሊዝ ለመሰል መኪኖች ፍቃድ ብትሰጥም፣ ሌሎች አገራት ግን ጉዳዩ ስጋት ውስጥ ስለከተታቸው የሙከራ ስራ ከመስራት ባለፈ መኪኖቹ በመደበኛነት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ አለመፍቀዳቸው ተገልጧል፡፡ ቶዮታ፣ ቢኤምደብሊው፣ መርሴድስ ቤንዝ፣ ኒሳንና ጄነራል ሞተርስን የመሳሰሉ የዓለማችን ታዋቂ የመኪና አምራች ኩባንያዎች የየራሳቸውን ሾፌር አልባ መኪኖች ዲዛይን በማድረግ ለዕይታ ማብቃት ከጀመሩ አመታት መቆጠራቸውን የጠቀሰው ዘገባው፣ ይሄም ሆኖ ግን አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገር መንግስታት ከደህንነት ስጋት ጋር በተያያዘ መኪኖቹ በብዛት ተመርተው በስራ ላይ እንዳይውሉ መከልከላቸውን አስታውሷል፡፡

Read 1652 times
Administrator

Latest from Administrator