Saturday, 02 August 2014 11:11

እስከ ‹ሮቦት› ብሄራዊ ቡድን?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

         አንዳንድ ዘገባዎች በሚቀጥሉት 20 ዓመታት በዓለም እግር ኳስ ስፖርት የሮቦት ዳኞች እና የሮቦት ተጨዋቾች ማሰለፍ የሚቻልበት የስልጣኔ ደረጃ ይመጣል ይላሉ፡፡ ምናልባትም የቴክኖሎጂ ድጋፍ አስፈላጊነቱ ከታመነበት ፊፋ የተርመጠመጠበትን የሙስና ችግር የሚያጋልጥ ቴክኖሎጂ ቢፈለሰፍ ብለው የማጣጣያ ትችት ያቀረቡ መረጃዎች፤ በሚቀጥሉት ሃምሳ ዓመታት ዓለም ዋንጫ በጨረቃ ላይ ሊስተናገድ ይችላል ብለው አሹፈዋል፡፡ኤችቲቢ ኤንድ ፊልቸር ቦነስ የተባለ ተቋም የዓለማችን የእግር ኳስ ስፖርት የወደፊት አቅጣጫዎች ብሎ በሰራው ምርምር ይፋ እንዳደረገው በሚቀጥሉት 50 ዓመታት ስፖርቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ለውጦች ማሳየቱ የማይቀር ይመስላል፡፡ ብዙዎቹ ቴክኖሎጂዎች እስከ 2022 እ.ኤ.አ ተግባራዊ ሊሆኑ እንደሚችሉም ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡

እንደተቋሙ ሪፖርት ከሆነ በሚቀጥሉት 15 ዓመታት በእግር ስፖርት በተጨዋቾች ማልያ ላይ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ለመቅረጽ የሚችሉ በዓይን የማይታዩ ካሜራዎች ይለጠፋሉ፤ የመጫወቻ ታኬታዎች ኳስን ለመቆጣጠር መጥኖ ለመምታትና አቅጣጫ ለመገመት የሚያስችሉ ይሆናል፤ የውድድር ዳኞች ማናቸውን የጨዋታ እንቅስቃሴ ለመበታተን እንዳይገባቸው ልዩ የካሜራ ሄልሜት ሊገጠምላቸውም ይችላል፡፡ ከስምንት ዓመታት በኋላ ኳታር በምታስተናግደው 22ኛው ዓለም ዋንጫ ዙርያ ከተነሱ አከራካሪ ጉዳዮች ዋንኛው የአገሪቱ ሙቀት ለውድድሩ አይመችም የሚለው ነው፡፡ የኳታር ዓለም ዋንጫ አዘጋጆች ግን ይህ ችግር በቴክኖሎጂ የሚፈታ ነው ብለው ተከራክረዋል፡፡

እስከ 45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርሰው የኳታር ሙቀት በስታድዬሞች በሚገጣጠሙ እና በሚሰሩ የማቀዝቀዣ ምሰሶዎች ለእግር ኳስ ጨዋታ የተመቹ እናደርጋቸዋለን በሚል ከወዲሁ ቃል ገብተዋል፡፡ ሰሞኑንም እስከ 7.4 ሚሊዮን ዶላር የወጣበትን የማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂን የፈተሹበት የሙከራ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ በርካታ ተመራማሪዎች እና ሳይንቲስቶች እግር ኳስ ከቴክኖሎጂ ጋር ተሳስሮ መቀጠሉን በመደገፍ የተለያዩ አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ ላይ ናቸው፡፡ በሚቀጥሉት ዓለም ዋንጫዎች ተግባራዊ ቢሆኑ ተብለው ሃሳብ ከተሰጠባቸው የቴክኖሎጂ ግኝቶች የመጀመርያው ኦፍሳይድ እና ኦንሳይድ የሆኑ ኳሶችን ለመለየት እንደ ግብ ማረጋገጫ ቴክኖሎጂ አዲስ አሰራር መፈልሰፉን የጠየቁ ናቸው፡፡ ሌላው ተጨዋቾች በተጋጣሚያቸው ፋውል ሲሰራባቸው በትክክል መሰራረቱን ወይም ለማታለል መወደቁን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሳርያም ቢኖር ተመኝተዋል፡፡ በራግቢ እና በአሜሪካን ፉትቦል ተግባራዊ የተደረገውና የሜዳ ላይ ትዕይንት በቀጥታ ተመልካች በቅርበት እየሰማ እንዲከታተል የታቀደው የቀረፃ ቴክኖሎጂም አለ፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በተጨዋቾች ማልያዎች ላይ በሚለጠፉ ልዩ ካሜራዎች ወይንም ደግሞ በነፍሳት መልክ በሚሰሩ እና ኳስ ጨዋታውን በመካተል በሚቀርፁ ልዩ ካሜራዎች ይህን ተግባር ለማከናወን እንደሚቻልም ይገለፃል፡፡

Read 1355 times