Print this page
Saturday, 02 August 2014 10:57

ሸራተን 80 ያህል ሰራተኞችን ከስራ አባረረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(11 votes)

        የሰራተኛ ማህበሩ አመራሮች በሙሉ ተባረዋል ከተባረሩት ውስጥ ታመው የተኙና በወሊድ ላይ ያሉ ይገኙበታል ተብሏል ሸራተን አዲስ ሆቴል 80 የሚጠጉ ሰራተኞቹን ከስራ አሰናበተ፡፡ የሰራተኛ ማህበሩ አመራሮች በጠቅላላ የተሰናበቱ ሲሆን ታመው ሀኪም ቤት የተኙና በወሊድ ፈቃድ ላይ ያሉ እንደተባረሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሸራተን ለተሰናባቾቹ ሰራተኞች በፃፈው የስንብት ደብዳቤ ላይ እንደገለፀው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በድርጅቱ ውስጥ በማኔጅመንቱና በሰራተኞች መካከል መልካም የሥራ ግንኙነት እየጠፋ፣ የሆቴሉ መልካም ገፅታ እየተበላሸና የኢንዱስትሪ ሰላም እየጠፋ በመምጣቱ ለችግሮቹ መንስኤና መባባስ ምክንያት ይሆናሉ ያላቸውን ወገኖች ለመለየት ለረጅም ጊዜ ክትትልና ጥናት ሲያደርግ መቆየቱን ገልፆ፣ በድርጅቱ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን የእነዚህ ሠራተኞች ከሥራ መሰናበት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ ለማሰናበት መገደዱን ጠቁሟል፡፡

ማኔጅመንቱና ሰራተኛ ማህበሩ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ ቀርበው በጠበቆቻቸው በኩል የፍርድ ሂደት መከናወኑ የሚታወስ ሲሆን አሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርዱ፣ የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አደራዳሪ እንዲመድብ እንዲሁም ሁለቱም ወገኖች ምን ደረጃ ላይ እንደደረሱ እስከ ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ለቦርዱ ሪፖርት እንዲያደርጉ በታዘዙት መሰረት ለድርድሩ ፈቃደኛ መሆናቸውን አስታውቀው ድርድሩ ተጀምሮ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የተጀመረው ድርድር እክል እንደገጠመውና ሸራተንም ሰራተኞችን ወደማባረር መሄዱን ተሰናባቾቹ ገልፀው በአገሪቱ አሰሪና ሰራተኛ አዋጅ መሰረት የተባረርንብት አግባብ ህጋዊ መሰረት የሌለውና ሰብአዊ መብታችንን የሚጥስ ነው ሲሉ ተቃውመውታል፡፡ በድርድሩ ዙርያ ያነጋገርናቸው የሰራተኛ ማህበሩ ጠበቃ አቶ ሰይድ ይመር፤ “ጉዳዩ መደበኛ በሆነ መንገድ በኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኑ አልተመራልኝም፣ የተሰናባቾቹን ደብዳቤም ቢሆን ያየሁት የአንድ የሁለት ሰው ብቻ ነው የድርድሩን ጉዳይ በተመለከተም ማክሰኞ ቀጠሮ ስላለ ከዚያ በፊት እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው ለማለት ይቸግረኛል” ብለዋል፡፡ ከሸራተን ተደራዳሪዎች አንዱ የሆኑት አቶ ክፍሌ ደረስ በበኩላቸው፤ ከሆቴሉ ማኔጀር በስተቀር መረጃ መስጠት ስለማይፈቀድ ምንም መረጃ ሊሰጡ እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ የሆቴሉን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ዣን ፒየር ማኒንጎፍን በስልክ ለማነጋገር ጥረት ብናደርግም የዋና ሥራ አስኪያጁ ፀሐፊ ወ/ሮ አፀደ ታደሰ ማኔጀሩ ቢሮ እንደሌሉና ከእሳቸው ውጭ ስለሆቴሉ አጠቃላይ ጉዳይ መረጃ መስጠት የሚችል ሰው እንደሌለ ገልፃልናለች፡፡ የሆቴሉ መሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር ሆቴሉ አደረሰብኝ ያለውን በደልና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከነገወዲያ ሰኞ ከ8፡00 ሰዓት ጀምሮ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ጋዜጠኞች በሀራምቤ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል፡፡

Read 3612 times