Saturday, 02 August 2014 10:54

የመንግስት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ለሐምሌ ወር አልደረሰም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(36 votes)

“ከተፈቀደበት ጊዜ አንስቶ ጭማሪው ተሠልቶ ይከፈላል”

      ለመንግስት ሠራተኞች ከሃምሌ ወር ጀምሮ የደሞዝ ጭማሪ ይደረጋል ቢባልም ጭማሪው ከሐምሌ ወር ደሞዝ ጋር ባለመሰጠቱ ሠራተኞች ቅር የተሰኙ ሲሆን የሲቪል ሠርቪስ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ የደሞዝ ጭማሪው እየተሰራ መሆኑን ጠቁሞ፣ የሃምሌ ወሩ ጭማሪ ቃል በተገባው መሠረት ተሰርቶ ባለቀ ጊዜ ተሰልቶ ይከፈላል ብሏል፡፡ ከሐምሌ 1 ጀምሮ ጭማሪው ተግባራዊ ይደረጋል መባሉን ተከትሎ፣ በጉጉት ሲጠብቁት እንደነበር የተናገሩ የመንግስት ሠራተኞች፤ ደሞዝ ሲቀበሉ የተባለው ጭማሪ አለመታከሉ በኑሮአቸው ላይ ጫና እንደሚፈጥር ገልፀዋል፡፡ በአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በግዥ ኦፊሠሪነት የሚሰራ አንድ ወጣት የደሞዝ ጭማሪውን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት፤ “መንግስት አስቀድሞ ደሞዝ ሊጨምር መሆኑን በማወጅ በመንግስት ሠራተኛውም ሆነ በሌላው ህብረተሰብ ላይ ከቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ አንስቶ የኑሮ ውድነት እንዲፈጠር የቅስቀሳ ስራ መስራቱ አግባብ አልነበረም” ብሏል፡፡ አብዛኛው ሠራተኛ ጭማሪውን በወሩ መጨረሻ ላይ ጠብቆት እንደነበረ የገለፀው ሌላው አስተያየት ሰጪ፤ ጭማሪው ከወዲሁ ተግባራዊ ቢደረግ ኖሮ፣ ነጋዴው በሸቀጦች ላይ ያደረገውን የዋጋ ጭማሪ ለመቋቋም ያስችል ነበር ብሏል፡፡

ነጋዴዎች ያደረጉትን የዋጋ ጭማሪ ወደነበረበት እንዲመልሱ መንግስት እርምጃዎችን እየወሰደ ቢሆንም ውጤታማ አልሆነም፤ ይህ ደግሞ የመንግስት ሠራተኛውን ይበልጥ ተጐጂ ያደርገዋል ሲል ተናግሯል፡፡ የሲቪል ሠርቪስ ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ መሐመድ ሰይድ፤መንግስት ለሠራተኛው ከሃምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ደሞዝ እንዲጨመር መፍቀዱን አስታውሰው፣ ቀን ባይቆረጥለትም ዝርዝር ሁኔታው ተሰርቶ እንደተጠናቀቀ ከተፈቀደበት ጊዜ አንስቶ ጭማሪው ተሠልቶ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡

Read 8068 times