Saturday, 02 August 2014 10:42

“አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በወጣ የሙስና ዘገባ ምክንያት ከሥራዬ ተባረርኩኝ ”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

    “የተባረሩት ሙስና መኖሩን በመጠቆማቸው አይደለም”- ድርጅቱ

   በ“የእለት ደራሽ የእርዳታ ትራንስፖርት ድርጅት ሙስና እየተፈፀመ ነው” በሚል ርዕስ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በወጣ ዘገባ ምክንያት የድርጅቱ የህግ አገልግሎት ክልል ኃላፊ፤ ከስራ እንዲሰናበቱ መደረጋቸውን የገለፁ ሲሆን የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ በበኩላቸው፤ ስንብቱ የሙስና ጥቆማ ከማቅረባቸው ጋር የተያያዘ አይደለም ብለዋል፡፡ የእለት ደራሽ የእርዳታ ትራንስፖርት ድርጅት ህግ አገልግሎት ኃላፊ የሆኑት አቶ ያለው አክሊሉ፤ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከድርጅቱ የስነ-ምግባር መኮንን አቶ ሰማህኝ ተፈሪ እና ከመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበሩ ም/ሊቀመንበር ጋር በመሆን በተቋማቸው ከፍተኛ ሙስና እየተፈፀመ መሆኑንና የፌደራል የስነ-ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ጉዳዩን በቸልተኝነት እየተመለከተው መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ያለው አክሊሉ ሰኔ 30 ቀን 2006 በተፃፈ ደብዳቤ ከስራ በቀጥታ እንዲሰናበቱ መደረጉን ጠቁመው፤ ስነ ምግባር መኮንኑ አቶ ሰማኸን ተፈሪ በተፃፈ ደብዳቤ ለአዲስ አድማስ በሰጡት መግለጫ በድርጅቱ ውስጥ ያለው የኢንዱስትሪ ሰላም አንዲናጋና ሽብር እንዲፈጠር ማድረጋቸው ተገልፆ፤ በ3 ቀን ውስጥ አለኝ የሚሉትን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለድርጅቱ እንዲያቀርቡ፤ ይህ ባይሆን እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችል የሚያመለክት ደብዳቤ ደርሷቸዋል፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት በድርጅቱ ይፈፀማሉ ያልናቸውን የሙሰና ተግባራት ለህይወታችን ሳንሳሳ ለማጋለጥ ከፍተኛ ጥረት አድረገናል የሚሉት አቶ ያለው፤ “የፀረ- ሙስና ኮሚሽን ጥቆማችንን በቸልታ ስለተመለከተው ጉዳዩን ወደ ሚዲያ ማቅረብ አስፈላጊ ነው ብለን በማመን ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝርዝር መረጃውን ልንሰጥ ተገድደናል ብለዋል፡፡ ዘገባው በጋዜጣው ከተስተናገደ በኋላ የድርጅቱ ስራ አመራሮች ሠራተኞችን ስብሰባ ጠርተው በዘገባው ላይ ውይይት ማድረጋቸውን የጠቀሱት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በስብሰባው ላይ የድርጅቱን ስም እንዳጠፋን ተደርጐ በሁለት ቀናት ውስጥ እርምጃ እንደሚወሰድብን ለሠራተኛው ተገልጿል ይላሉ፡፡ ስብሰባው በተካሄደ በሁለተኛው ቀን “የስራ ሪፖርት ሲጠየቁ ስርአት የጐደለው ምላሽ አቅርበዋል” በሚል ምክንያት የስራ ስንብት ደብዳቤ እንዲደርሳቸው መደረጉን አቶ ያለው አስታውቀዋል፡፡ የተሰናበቱበት ምክንያትም ቀደም ሲል ለሠራተኞች ቃል በተገባው መሠረት ሳይሆን ስራ አስኪያጁ “የ5 ወራት የስራ ሪፖርት ይቅረብልኝ” ሲሉ በዘለፋ የታጀበ ያልተገባ ምላሽ ሰጥተሃል፤ በሚል ምክንያት እንደሆነ ያብራሩት አቶ ያለው፤“የተፈፀመብኝን በደል በድርጅቱ የስነምግባር መኮንን በኩል ለፌደራል የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የምርመራና አቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ባመለክትም ኮሚሽኑ እስካሁን ምላሽ አልሰጠኝም” ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል ለፀረ - ሙስና ኮሚሽን በድርጅቱ ተፈጽመዋል ያልናቸውን 56 አይነት ወንጀሎች በማስረጃ አስደግፈን አቅርበናል ያሉት አቶ ያለው፤ አሁንም ቢሆን ከዚህ ትግል የሚገታኝ የለም ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል መሃመድ በበኩላቸው፤ ግለሰቡ ከስራ እንዲሰናበቱ የተደረገው የ5 ወራት የስራ ሪፖርት በአግባቡ እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ፣በዘለፋ የታጀበና ከተጠየቀው ጋር ያልተገናኘ ምላሽ በመስጠታቸው የተወሰደ እርምጃ እንጂ የሙስና ጥቆማ ከማድረጋቸው ጋር የተያያዘ አይደለም ብለዋል፡፡ “ሠራተኛው ስብሰባ ተጠርቶ በዘገባው ላይ ውይይት ተካሂዷል የተባለው፣በወጣው ዘገባ ሠራተኛው ሳይረበሽና ሳይደናገጥ ስራውን እንዲያከናውን መመሪያ ለመስጠት ነው” ሲሉ መልሰዋል - አቶ ጀማል፡፡ የፌደራል የስነ - ምግባርና የፀረ - ሙስና ኮሚሽን የትምህርትና የስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ፤“አንድ የሙስና ጠቋሚ ከስራው ከተሰናበተ አሊያም ጥቅማ ጥቅሙን ካጣ፣በኮሚሽኑ ይህ የተደረገበት ምክንያት በሚገባ ከተጣራ በኋላ፣ ወደ ስራው እንዲመለስ አሊያም ያጣውን ጥቅማጥቅም መልሶ እንዲያገኝ ይደረጋል” ካሉ በኋላ “እንዲህ ያለ ጥቃት ደርሶብኛል የሚሉ ግለሰቦች በየድርጅቶቹ ካሉ የስነምግባር መኮንኖች ጋር በመሆን ወደ ኮሚሽኑ መጥተው ቢያመለክቱ ይመረጣል” ብለዋል፡፡

Read 3909 times