Tuesday, 29 July 2014 15:05

ሰበር ዜና! ጠ/ሚኒስትሩ በተቃዋሚ ፓርቲ የምስረታ በዓል ላይ ንግግር አደረጉ

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(7 votes)

ፓርቲዎች የየራሳቸውን የቢሮ  ህንፃ እንዲገነቡ የባንክ ብድር ተፈቀደላቸው
ተቃዋሚዎች በየሳምንቱ የ60 ደቂቃ የቴሌቪዥን አየር ሰዓት ተመደበላቸው
በ“ሽብር” የታሰሩ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በምህረት ተለቀቁ  

ቀኑንና ዓመተ ምህረቱን አላስታውሰውም፡፡ እለቱ ግን አርብ ነው፡፡ እኔ ቢሮዬ ውስጥ ነው ያለሁት፡፡ “ፖለቲካ በፈገግታ”ን እየፃፍኩ፡፡ አልፎ አልፎ በመስኮት በኩል የማየው ሰማይ ሰፊ ባህር ይመስላል፡፡ በጋዜጣው ዝግጅት ክፍል እንደወትሮው ወከባ አይታይም፡፡ ጋዜጣው የሚወጣበት ቀን ግን አልተለወጠም - ያው ቅዳሜ ነው፡፡
አንጋፋው የግል ጋዜጣ፣ከአንጋፋው ማተሚያ ቤት ከብርሃንና ሰላም ጋር ከተለያየ ጥቂት ወራት  ተቆጥረዋል፡፡ አሁን ጋዜጣው የሚታተመው በራሱ ማተሚያ ቤት ነው፡፡ እጅግ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ የህትመት ማሽን አስመጥቷል - 100 ሺ ኮፒ በ30 ደቂቃ ውስጥ አትሞ የሚገላግል፡፡ ለዚህ ነው አርብ አርብ ወከባ የቀረው፡፡
አዲስ አድማስ ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ የግል ጋዜጦች የራሳቸው ማተሚያ ማሽን አስገብተዋል (እንደነ “ዋሽንግተን ፖስት” ወግ ደረሰን!) ጋዜጦች የሚሸጡት እንደ ድሮው ጎዳና ላይ አይደለም፡፡ ራሳቸው ባዘጋጁት ቄንጠኛ ኪዮስኮች ውስጥ ሆኗል፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ግን በጋዜጦች የስርጭት መጠን (ኮፒ) ላይ የታየው ለውጥ ነው፡፡ በሳምንት ከ100 ሺ በታች ቅጂዎች የሚያሳትም ጋዜጣ ፈልጎ ማግኘት አይቻልም፡፡ (አትጠራጠሩ! የማወራው ስለ ኢትዮጵያ ነው!)  አብዛኞቹ ጋዜጦችም ከኪራይ ቢሮ ወጥተው ራሳቸው ባስገነቡት ባለአምስትና ስድስት ፎቅ ህንፃ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ኢህአዴግ ቁጥር 1 የግል ፕሬሱ አጋር ከሆነ ከራርሟል፡፡ የማተሚያ ማሽን ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ ከመፍቀዱም ባሻገር ለሁሉም የግል ጋዜጦች የህንፃ መስሪያ ቦታ በነፃ አከፋፍሏል፡፡ ባይገርማችሁ ለማመን እሚያዳግቱና ትንግርት የሚመስሉ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምርጫ ሰሞን በስንት ውዝግብ ያገኙት የነበረው የቴሌቪዥንና ሬዲዮ የአየር ሰዓት አሁን በሽበሽ ሆኗል፡፡ (“ኢህአዴግ ለብቻው ሲጠቀምበት የኖረውን ሚዲያ ለህዝብ ጥቅም ሲባል  ተቆጣጥረነዋል” አልተባለም እንጂ!) የምርጫ ሰሞን ብቻ ሳይሆን በአዘቦት ቀንም እያንዳንዱ ተቃዋሚ ፓርቲ በሳምንት አንድ ቀን የ60 ደቂቃ የአየር ሰዓት ተመድቦለታል፡፡ በኢህአዴግ ችሮታ አሊያም  በተቃዋሚዎች ትግል የተገኘ አይደለም፡፡ ሁለቱም ተስማምተው ባፀደቁት አዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ላይ ተደንግጓል፡፡ ይሄ ለማመን እንደሚቸግር ይገባኛል - ግን ግዴለም እመኑት፡፡ (“እቺ ናት አገርህ” አለ ገጣሚው!) ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እላይና እታች ማለት  ቀርቶላቸዋል፡፡ ከእነሱ የሚጠበቀው ከ24 ሰዓት በፊት ለሚመለከተው ወገን በኢ-ሜይል ማሳወቅ ብቻ ነው፡፡ “የስብሰባ እንጂ የቅስቀሳ ፈቃድ የላችሁም” በሚል ከየመንገዱ ሰብስቦ ማሰር መልሶ ያሳስራል፡፡  
እንዲያም ሆኖ ግን ሰላማዊ ሰልፍ በሽበሽ አይደለም፡፡ ከስንት አንዴ በናፍቆት የሚታይ “ብርቅዬ ነገር” ሆኗል፡፡ ተቃዋሚዎች ችግራቸውን ከኢህአዴግ ጋር በመወያየት መፍታት ስለጀመሩ ህዝቡን ለሰላማዊ ሰልፍ መጥራት እርግፍ አድርገው ትተዋል፡፡ ብቻ ምን ልበላችሁ? ኢትዮጵያ የምታስቀና አገር ሆናለች፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገራት ፖለቲከኞች እንደ ውሃ ቀጂ  ይመላለሱባታል - የፖለቲካ ልምድ ለመቅሰም፡፡  
የስብሰባ አዳራሽ ፍለጋ ከአንዱ ሆቴል ሌላው ሆቴል መኳተንም ተረት ሆኗል፡፡ “ስብሰባችንን ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ውስጥ ነው የምናካሂደው” ካላሉ በቀር የህዝብ አዳራሾች ለእነሱም ለኢህአዴግም እኩል አገልግሎት እንዲሰጡ በአዋጅ ተደንግጓል፡፡
 የጋዜጣችን ሪፖርተር፤ በኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ በክብር እንግድነት መጋበዛቸውን ሰምታ መገረሟን ነገረችኝ (እሷ የምታውቀው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ አባላት ሲጋበዙ ነዋ!) ለነገሩ እኔም የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር በተቃዋሚ ፓርቲ የምስረታ በዓል ላይ ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸውን በኢቴቪ አይቻለሁ፡፡ ያኔ ነው ተቃዋሚዎች ለቢሮ የሚያገለግላቸው ህንፃ እንዲገነቡ ከባንክ ብድር የተፈቀደላቸው፡፡  
ምርጫ በመጣ ቁጥር ለፓርቲዎች ውዝግብ መነሻ የሚሆነው “የምርጫ ቦርድ” መፍትሄ እንደተገኘለት ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ማስታወቃቸውም የ“ህዳሴው አብዮት” አካል ነው ተብሏል፡፡ መግለጫው እንደሚለው፤ቦርዱን ከገዢው ፓርቲና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የተውጣጡ አባላት እንዲመሩት ተደርጓል (“አሹ” አላላችሁም!) የህዳሴው ፍሬ ገና አላለቀም፡፡ እንደውም የበለጠ የሚያስገርሙና አፍ የሚያሲዙ ጉዳዮች  ይቀራሉ (የልብ ችግር ያለባችሁ ጠንቀቅ በሉ!)   
በቅርቡ… ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር ተደራድረው “በሽብርተኝነት” ተከሰው የተፈረደባቸው ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን ጨምሮ በርካታ እስረኞች በምህረት ተለቀዋል፡፡ (የሰለጠነ ዘመን ይሏል ይሄ ነው!) እዚያው ቢሮዬ ውስጥ እንደተቀመጥኩ ኢቴቪ ሰበር ዜና (breaking news) ሲል ሰማሁና ቀና ብዬ መመልከት ጀመርኩ፡፡ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፤ በፓርላማ “ሽብርተኛ” ተብለው ከተፈረጁ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል አልቃይዳና አልሸባብ ሲቀሩ ለሌሎቹ ምህረት ማድረጉን አስታወቀ፡፡ ለተለያዩ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “በሽብርተኝነት ለተፈረጁት የፖለቲካ ድርጅቶች ምህረት የተሰጠው ከትጥቅ ትግል ወጥተው ወደ ሰላማዊ ትግል በመግባት ለእናት አገራቸው በጎ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ በሚል እምነት ነው” ብለዋል (“ለሁሉም ጊዜ አለው” አለ ጠቢቡ ሰለሞን!)
ኢህአዴግ ለበርካታ ዓመታት “ዓይንህ ለአፈር” ሲለው የነበረው (በአሮጌው ዘመን ማለቴ ነው!) ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን፤ የኢትዮጵያ መንግስትን የሰብዓዊ መብት አያያዝ የሚያደንቅ ጉደኛ ሪፖርት አወጣ፡፡(“ዘይገርም” እኮ ነው!) የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትሩ በበኩላቸው “በእውነተኛ የህዳሴ አብዮት የተፈጠረችው ኢትዮጵያ ብዙዎችን እያስደመመች ነው” ሲሉ በፌስ ቡካቸው ላይ ፅፈው አነበብኩ፡፡ (እንኳን የአዳም ዘር ፈጣሪም ተደምሞባታል!) እስካሁን የተረኳት ዓይነት ኢትዮጵያ ገና አልተፈጠረችም፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢቴቪም እንኳ አያውቃትም፡፡  ሰሞኑን እቺን ህልም የምትመስልና የምታስቀና ኢትዮጵያ ለመፍጠር የሚያስችል አዲስ ፕሮፖዛል ስቀርፅ ነው የሰነበትኩት። የፕሮፖዛሌን ዝርዝር በጥሞና ተከታተሉኝ፡፡ የዚህን ፕሮፖዛል መነሻ ሃሳብ ያገኘሁት “Trance” ከተሰኘው ፊልም ላይ እንደሆነ ለመግለፅ እፈልጋለሁ (የኮፒራይት መብት ለማክበር ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እስክትሆን መጠበቅ የለብንም!) እናላችሁ… በአዲሱ ፕሮፖዛሌ መሰረት ከላይ የተገለፀችውን የህልም ዓለም የምትመስል ኢትዮጵያ ለመፍጠር እያንዳንዱ ፖለቲከኛ (ገዢውንም ተቃዋሚዎችንም ይመለከታል!) ከስልጣን ሱስ ሙሉ በሙሉ መላቀቅ ይኖርበታል፡፡ ለእስከዛሬው የአገራችን የፖለቲካ ቀውስ ሰበቡ ሌላ ሳይሆን ሥልጣንና ሥልጣን ብቻ እንደሆነ ፕሮፖዛሌ ይጠቁማል፡፡ ስለዚህ የአገሬ ፖለቲከኞች ሃሳባቸውንም ሆነ ስሜታቸውን ከስልጣን ማላቀቅ አለባቸው፡፡ በቃ ሥልጣንን እርስት ያደርጉታል፡፡ ይሄ ግን በራስ ጥረት ብቻ የሚሳካ አይደለም፡፡ በ “Trance” ፊልም ላይ ሳይመን ከቁማር ሱስ (gambling addiction) ለመገላገል  ወደ ቴራፒስት ዘንድ እንዳመራው ሁሉ፣ ፖለቲከኞቻችንም ተመሳሳይ ህክምና (ቴራፒ) ማግኘት እንዳለባቸው በአፅንኦት ይገልፃል - ፕሮፖዛሌ፡፡ (ሥልጣን ከቁማር የባሰ ሱስ ነው!)እናም ፖለቲከኞች በሂፕኖቴራፒ---- የሰመመን ዓለም ውስጥ እንዲገቡ ተደርገው ሥልጣን የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ከአዕምሮአቸው ውስጥ ይወጣል፡፡ ስልጣን ላይ ያሰፈሰፈ አዕምሮአቸው በምትኩ በአገር ፍቅር… በሰብዓዊ መብት አከባበር… በልማትና ብልፅግና ላይ ብቻ እንዲያተኩር ይደረጋል። በሌላ አነጋገር “ሂፕኖታይዝድ” ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ቴራፒውን በተከታታይ ወስደው በስኬት ሲያጠናቅቁም  ከስልጣን ጋር የማይተዋወቁ ፖለቲከኞች ሆነው ቁጭ ይላሉ፡፡ ቴራፒው ሥልጣንን ያብሰለስል የነበረውን የአዕምሮአቸውን ክፍል በሰረገላ ቁልፍ ይከረችመዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ሥልጣን ለእነሱ የማያውቁት አገር ሆነ ማለት ነው፡፡ (“ጅብ የማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ” አሉ!)
ይሄኔ ብቻ ነው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር በኢህአዴግ ጉባኤ ላይ ሊገኝ የሚችለው፡፡ ይሄኔ ብቻ ነው የታሰሩ ፖለቲከኞች በድርድር ሊፈቱ የሚችሉት፡፡ ይሄኔ ብቻ ነው ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በጥላቻ  መተያየታቸውን እርግፍ አድርገው የሚተዉት፡፡ ይሄኔ ብቻ ነው አንዱ ሌላውን ጠልፎ ለመጣል ከማሴር የሚታቀበው፡፡ ይሄኔ ብቻ ነው ተቃዋሚዎች በየሳምንቱ 60 ደቂቃ የቲቪ የአየር ሰዓት ሊመደብላቸው የሚችለው፡፡ ለምን መሰላችሁ? ፖለቲከኞች “የሰይጣን ቁራጭ” የሚሆኑት ሥልጣን ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በተረፈ ግን  እንደነሱ መላእክ የለም!
ከምሬ ነው የምላችሁ----ያቺ የህልም ዓለም የምትመስል ኢትዮጵያ የምትፈጠረው ፖለቲከኞቻችን በሂፕኖቴራፒ ሥልጣንን እንዲረሱ ስናደርጋቸው ብቻ ነው፡፡ የፓርቲዎች ዓላማ ሥልጣን መያዝ መሆኑ ጠፍቶኝ እንዳይመስላችሁ ----- ከሥልጣን ጋር እንዲፋቱ “ሂፕኖታይዝድ” ይሁኑ የምለው፡፡ ከሁሉም በፊት ውስጣዊ የስልጣን ጥማት ከሚፈጥረው የአመጻ፣ የፀብ ጫሪነት፣ የጉልበተኝነት፣ የማን አለብኝነት፣ የኢሰብአዊነት … ወዘተ ስሜት መላቀቅ አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ፍቱኑ መድኀኒት  ሂፕኖሲስ ብቻ ነው፡፡
አይዞአችሁ----ለዝንተ ዓለም ሥልጣንን እንደረሱ አይቀሩም፡፡ ፖለቲከኞች አደብ መግዛታቸውና ሰከን ማለታቸው ከታየ በኋላ በተመሳሳይ የህክምና ዘዴ (Hypnosis) የረሱትን ሥልጣን እንዲያስታውሱ ይደረጋሉ፡፡ (ሂፕኖሲስ የማስረሳትም የማስታወስም አቅም አለው!!)
በነገራችሁ ላይ የዚህ ፕሮፖዛል አላማ እነ አሜሪካ በተፈጥሮአዊ የፖለቲካ ሂደት እውን ያደረጉትን ሥርዓት ለጦቢያ በቴራፒ ማምጣት ነው፡፡ የማታ ማታም ያቺን ህልም የምትመስል ኢትዮጵያ መፍጠር! (“የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” አሉ!)  እንግዲህ-----ይሄ ፕሮፖዛሌ ተቀባይነት ካገኘ የመጀመሪያ ሥራ መሆን ያለበት (የውጪ ድጋፍ ጠይቀንም ቢሆን!) በርካታ የሂፕኖቴራፒ ባለሙያዎችን በጥራትና በብቃት ማሰልጠን ነው፡፡ ያለበለዚያ ይሄም እንደ እነ ቢፒአር የመክሸፍ  ዕጣ አይቀርለትም (ከመክሸፍም ከማክሸፍም ያውጣን!!)

Read 4227 times