Tuesday, 29 July 2014 15:04

ፍቅረኛን የሚያስረሳ ቴራፒ! (Hypnosis)

Written by 
Rate this item
(10 votes)

ሰሞኑን በእጅጉ ማርኮኝ የተመለከትኩት “Trance” የተሰኘ ፊልም ላይ፣ ዋና ገፀ-ባህሪው ሳይመን ሳያውቀው የገባበት የቁማር ጨዋታ (gambling) የለየለት ሱሰኛ ያደርገውና የዕዳ አረንቋ ውስጥ ይዘፈቃል፡፡ ከቁማር ሱሰኝነቱ ለመላቀቅ የዘየደው መላ ወደ ቴራፒስት ዘንድ መሄድ ነው፡፡ በሂፕኖቴራፒ ከቁማርተኝነቱ ለመፈወስ፡፡ ሂፕኖሲስ የህክምናው (ቴራፒው) ሂደት ሲሆን ባለሙያው ወይም ባለሙያዋ ሂፕኖቲስት ይባላሉ፡፡ ቴራፒውን የወሰደው ሰው ደግሞ “ሂፕኖታይዝድ” ሆኗል ይባላል፡፡
በነገራችሁ ላይ ሂፕኖሲስ ታካሚውን በሰመመን ስሜት ውስጥ በማስገባት፣ ሃሳቡንና ትኩረቱን በአንድ የሆነ ጉዳይ ላይ እንዲያነጣጥር፣ የተወሰኑ ቃላትን ወይም ዓ.ነገሮችን በመደጋገም አሊያም የአዕምሮ ምስል በመፍጠር… የሚሰጥ ህክምና (ቴራፒ) ነው፡፡ ሂፕኖሲስ ያልተፈለገ ባህሪን (ድርጊትን) ለማስወገድ ወይም ለመቆ›ጣጠር በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ ከሲጋራ ሱሰኝነት ለመላቀቅ፣ ከእንቅልፍ እጦት (Insomnia) ለመገላገል፣ ከመጠን በላይ የመብላት ፍላጐትን ለማስወገድ …ወዘተ ሊያግዝ እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ወደ ፊልሙ ልመልሳችሁ፡፡ በቁማር ሱሰኝነት ኑሮው የተቃወሰው ሳይመን፤ ኤልዛቤት ላምብ የተባለች ቴራፒስት ዘንድ በመሄድ ችግሩን ተናግሮ ቴራፒውን ይጀምራል፡፡ የቁማር ሱሰኝነቱ ስር የሰደደ በመሆኑ ብዙ ጊዜ እንደሚወስድበት ይገለጽለትና ህክምናውን ይቀጥላል፡፡ በዚህ ሂደትም ከኤልዛቤት ጋር እየተቀራረበ ይመጣል፡፡ የጦፈ የፍቅር ግንኙነትም ይጀምራል፡፡
ቴራፒስቷ ከደንበኞቿ ጋር እንዲህ ያለ ግንኙነት ውስጥ መግባት እንደሌለባት ታውቃለች፡፡ ግን አንዴ ሆነ፡፡ እናም “የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም” ብላ ገፋችበት። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሳይመን ፍቅር ወደ ጥርጣሬና ቅናት እየተቀየረ መጣ፡፡ የት ገባሽ፣ የት ወጣሽ ማለት አበዛ፡፡ ፍቅረኛውን የሚያጣት፣ እየመሰለው ይጨነቅ ጀመር፡፡ ቅናቱ እየተባባሰ እንደ እብደት አደረገው፡፡ መላ ህይወቱን እሷ ላይ ጣለ፡፡ ከእሷ ከተለየ የሚሞት ሁሉ መሰለው፡፡ በዚህ የተነሳም ያፈቀራትን ያህል ጠላት፡፡ አንድ ቀን ሬስቶራንት ውስጥ ተቀምጠው ሳለ “ወንድ አየሽ” ብሎ በጥፊ አጠናገራት፡፡ ይሄን ጊዜ ነው ኤልዛቤት ከዚህ ጨዋታ መውጣት እንዳለባት የወሰነችው፡፡ ግን በየት በኩል? ሳይመን አለቅም ብሎ ሙጭጭ አለባት፡፡ ረዥም የይቅርታ ደብዳቤ ፃፈላት። እየደወለ ነዘነዛት፡፡ እያለቀሰ ተማፀናት፡፡ ኤልዛቤት ግን የዚህ መጨረሻ ምን እንደሚሆን አላጣችውም፡፡ ነገርዬው በዚህ ከቀጠለ የማታ ማታ እንደሚገድላት ቅንጣት አልተጠራጠረችም፡፡
ጉዳዩን ለፖሊስ ብታመለክትም ነገሬ ሳይሏት ቀሩ፡፡ ጠበቆች፤ ስሟን ቀይራ አገር ጥላ እንድትወጣ መከሯት፡፡ እሷ ደግሞ ይሄን ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረችም፡፡ ሁለት ጊዜ ተጎጂ መሆንን አልፈቀደችም፡፡ እናም ጉዳዩን በቁጥጥሯ ሥር ለማዋል መረጠች፡፡
ሳይመንን ከቁማር ሱሰኝነት ለመገላገል ወይም ቁማር ለማስረሳት ስትጠቀምበት የቆየችውን ቴራፒ ለዚህ ዓላማ አዋለችው፡፡ “መርሳት የምትፈልገው ቁማሩን ሳይሆን እኔን ነው” በማለት እርሷን እንዲረሳት ተከታታይ ቴራፒ ሰጠችው፡፡ ቀስ በቀስም እሷን እየረሳ መጣ፡፡ እሷን ብቻ ሳይሆን የፍቅር ግንኙነታቸውንም ጭምር ረሳው፡፡ ሁሉ ነገር ከአዕምሮ ትውስታው እልም ብሎ ጠፋ፡፡ የቁማር ሱሱን ሊረሳ ሄዶ ፍቅሩን ረስቶ ተመለሰ፡፡
አንዳንድ በፀብና በቅናት የተሞሉ አደገኛ የፍቅር ግንኙነቶች እንዲህ “ዲሊት” እየተደረጉ ከትውስታ ማህደር ቢጠፉ ብዙ ጥንዶችን ከከፋ ችግር ሊታደጉ ይችላሉ፡፡ በእርግጥ ወደ ፊልሙ መጨረሻ አካባቢ የሳይመን ትውስታ ይመለሳል፡፡ “ለምን እንድረሳ አደረግሽኝ?” ብሎ የቀድሞ ፍቅረኛውን ይጠይቃታል፡፡ ኤልዛቤትም “ትውስታህ በሰረገላ ቁልፍ ተከረቸመ እንጂ ከጥቅም ውጭ አልሆነም” ስትል ትመልስለታለች፡፡
ኤልዛቤት በሂፕኖቴራፒ ክህሎቷ ራሷን ከሞት፣ የቀድሞ ፍቅረኛዋን ደግሞ ከዕድሜ ልክ እስርና ፀፀት ለማትረፍ ችላለች፡፡ ይሄን ፊልም ተመልክቼ ስጨርስ ወደ አዕምሮዬ የመጣው፣ በሃይልና በዱላ የታጀበው የአገራችን የፍቅር ግንኙነት ነው፡፡ በበዛ ቅናት እየተሰቃየ ሚስቱን ለሚደበድብ ባል፤ ይሄ ቴራፒ ግሩም ይመስለኛል፡፡ ፍቅረኛውን ከእነ ትዝታዋ በማስረሳት አዲስ ህይወት እንዲመራ ለማድረግ ይረዳል፡፡
በሂፕኖቴራፒ ሰዎች እንዲረሱ ብቻ ሳይሆን የረሱትንም እንዲያስታውሱ (ትውስታቸው እንዲመለስ) ማድረግ ይቻላል፡፡ ሳይመን ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ያስቀመጠበት የጠፋበትን የመኪና ቁልፍ በሂፕኖሲስ እንዲያስታውስ አድርጋዋለች - ቴራፒስቷ ኤልዛቤት፡፡ ዓምና ለእይታ የበቃውን “Trance” የተሰኘ ፊልም ፈልጋችሁ ተመልከቱት፡፡ ድንቅ ፊልም ነው!! (በነገራችሁ ላይ እኔ የተረኩት ከሙሉ ፊልሙ እጅግ ጥቂቱን ብቻ ነው)

Read 6440 times