Tuesday, 29 July 2014 14:59

“ቢል ጌትስ…ስኬትህን ሳይሆን ምጽዋትህን እናከብራለን”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ከ“አነስተኛና ጥቃቅን” ተነስቶ፤ ዛሬ የአለማችን ባለ ሃብት ሆኗል!
እንደ ቻይና ወጣቶች በቢል ጌትስ የቢዝነስ አርአያነት ለብልጽግና እንጥራለን?
ወይስ እንደ ለማኝ በቢል ጌትስ ምጽዋት ተማምነን እጅ እንስማለን?

“የአገሬ ሰውና የአገሬ መንግስት ይመሳሰላሉ፤ ራሳቸውን ጠልፈው መጣል ይቀናቸዋል” በሚል ርዕስ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ የወጣው ጽሑፍ፤ በአንድ ሃሳብ ላይ የሚያጠነጥን ነበር። ስለ እድገትና ብልጽግና እናወራለን፡፡ ጥሩ ነገር መመኘት በጐ ነው፡፡ ነገር ግን ምኞታችንን እውን እንዳናደርግ፤ ራሳችንን ጠልፈን እንጥላለን ይላል ጽሑፉ፡፡ እንዴት?
ብልጽግናን፣ ቢዝነስን፣ ስኬታማንና ትርፋማነትን ከማክበር ይልቅ “የዚህ አለምን ህይወት” እየናቅን፤ መመነንን፣ ችግር መካፈልን፣ ምጽዋትን፣ ምስኪንነትንና መስዋዕትነትን እናመልካለን፡፡
በአንድ በኩል ብልጽግናን ብንመኝም፤ በሌላ በኩል ሁለመናችንን በፀረ ብልጽግና ሃሳቦችና ባህሎች ተብትበን አስረነዋል፡፡ እንዲህ ራሳችንን ጠልፈን የመጣል አባዜ እንደተጠናወተን የሚገልፀው ጽሑፍ፤ በርካታ ሰሞነኛ ዜናዎችን በማስረጃነት ያቀርባል፡፡ ይህ የምዕተ ዓመታት “በሽታ” ምንኛ ስር የሰደደና በሰፊው የተንሰራፋ እንደሆነም በዝርዝር ያስረዳል፡፡ እውነትም የባህል እና የአስተሳሰብ “በሽታ” ተጠናውቶናል፡፡ ሃሙስ እለት በቢል ጌትስ “የክብር ዶክትሬት” ሽልማት ላይም በግላጭ አየሁት - “የቢዝነስ ስኬትህን ሳይሆን የምጽዋት እጅህን እናደንቃለን” ብለን ሸለምነው፡፡
ይሄ ነው ዋናው በሽታችን - ለኋላቀርነትና ለድህነት የዳረገን ነባር በሽታ! በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች በሽልማቱ ዙሪያ ሌላ ሌላ ቅሬታ ሲያነሱ ሰምቻለሁ፡፡ ለምሳሌ፤ የስራ ባልደረባው በማኔጅመንት መስክ ትምህርቱን ተከታትሎና ጥናት አካሂዶ በዶክትሬት ዲግሪ እንደሚመረቅ የገለፀልኝ አንድ ባለሙያ፤ የዚህኛው ዶክትሬት “የክብር ዶክትሬት” አይደለም ወይ? ሲል ጠይቋል። በእርግጥም የትምህርት ተቋም ውስጥ ገብቶ፤ በዶክትሬት ዲግሪ መመረቅ…ማለትም በማንኛውም መስክ የእውቀትና የክህሎት፣ የአቅምና የብቃት ባለቤት ወይም ጌታ መሆን፣ ትልቅ “ክብር” ነው፡፡
በዚያው መጠን፤ ከትምህርት ተቋም ውጭም፤ ብቃቱን ተጠቅሞ የስኬትና የሃብት ባለቤት (ጌታ) ለመሆን የቻለም፤ ክብር ይገባዋል፡፡ ደግሞስ ሌላ ምን የክብር ምንጭ አለ? የአንዳች ጠቃሚ ነገር ባለቤት፣ ጌታ ከመሆን ውጭ ሌላ የክብር ምንጭ የለም፡፡ ከሺ ዓመታት በፊት በስልጣኔ ጐዳና ሲራመዱ የነበሩት ኢትዮጵያውያን፣ ይህ እውነት ገብቷቸው ነበር፡፡ “ባለ” ወይም “በዓለ” የሚሉ ቃላት በመጠቀም ነበር አክብሮትና አድናቆታቸውን የሚገልፁት - ዛሬ “ባለ ሀብት” እንደምንለው፡፡
“ባለ” ወይም “በዓለ”… የአንዳች ነገር ባለቤት ወይም ጌታ መሆንን - ያስገነዝባል፡፡ ከዚህም ጋር ክብርና አድናቆትን ይገልፃል፡፡ በዓል ማለት ጌትነትና ባለቤት ነው፤ ክብር እና ሞገስም ነው፡፡ ለአማልክት እና ለጀግኖች፤ “በዓል” የሚል የማዕረግ መጠሪያ ይጠቀሙ ነበር፡፡ ባለነበል (ነበል -ባል)፤ የእሳት ጌታ ነው እንደማለት፡፡ ባለሀብት፣ ባለአገር፣ ባለአምባ ወዘተ… ብቃትና ባለቤትነትን፣ ከጀግንነትና ከክብር ጋር አጣምረው ነበር የሚያስቡት፡፡ ቅዱስ ሲሉ ጀግና ማለታቸው ነበር፡፡
ከጊዜ በኋላ የስልጣኔ አስተሳሰብ ሲጠፋ የስልጣኔ ጉዞውም ተረሳ፡፡ “የዚህ አለም ነገር” ሁሉ ከንቱ ነው ተባለ፡፡ የእውቀትም ሆነ የብቃት፣ የስኬትም ሆነ የሃብት ባለቤትነት ተናቀ፡፡ ክብርም አጣ፡፡ በዚያው መጠን ድንቁርናና ምስኪንነት፣ ውድቀትና ድህነት የሚወደስበት ኋላቀር ባህል ወረስን፡፡ እናም፤ ስልጣኔንና ብልጽግናን የምንፈልግ ከሆነ፤ በትምህርት ተቋምም ሆነ በሌላው የህይወት አለም የብቃትና የስኬት ባለቤትነትን ማክበር ይገባል፡፡ ለቢል ጌትስ የተዘጋጀው “የክብር ዶክትሬት” በዓይነቱ በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው መባሉ ያልተዋጠላቸው ሰዎች በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ብቻ ሳይሆን መንግስት ጭምር የገባበት ጉዳይ መሆኑ እንደ ትልቅ ነገር መቆጠር የለበትም ብለዋል፡፡
ለተራ ነገርና ለቁም ነገር፣ ለትንሹም ለትልቁም… እንዲያው በዘፈቀደ “በአፍሪካ የመጀመሪያው…” እየተባለ ሲነገር መስማት ሊያስጠላ ይችላል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር፤ የጐዳና ቆሻሻ የሚያፀዱ መኪኖችን እንደሚገዛ የገለፀ ሰሞን፤ “በአፍሪካ ደረጃ በሁለተኝነት የሚጠቀስ” ማለቱን ታስታውሱ ይሆናል፡፡
እንግዲህ ነገሩን ስታስቡት፤ “በአፍሪካ የመጀመርያው፣ በአፍሪካ ሁለተኛው…” የሚያስብል ጉዳይ አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ መረጃው እውነት ነው፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት እዚሁ አገራችን ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጐዳና ማጽጃ መኪና ይጠቀም ነበር፡፡ በበርካታ የአፍሪካ አገራትም እንዲሁ ከአመታት በፊት ተጀምሯል፡፡ ይህንን መረጃ ለማግኘት፤ በኢንተርኔት አንድ ሁለት ደቂቃ ድረገፆችን ገለጥለጥ ማድረግ ይበቃል፡፡ ዛሬ‘ኮ …ክብር ለነ ቢል ጌትስ ይድረሳቸውና፤ ጀግኖቹ የቴክኖሎጂና የቢዝነስ ሰዎች በየበኩላቸው በተቀዳጁት የጥረት ስኬት አማካኝነት፤ እንደ “ተዓምር” በሚያስደንቅ ሁኔታ በቀላሉ ብዙ ብዙ መረጃ ማግኘት የምንችል ሰዎች ሆነናል፡፡ የብቃት ባለቤት አድርገውናል - የብቃት ባለቤት የሆኑ ጀግኖች፡፡
ለማንኛውም ለቢል ጌትስ የተሰጠ የክብር ዶክትሬት…”በዩኒቨርስቲ ብቻ ሳይሆን በመንግስትም ጭምር የተዘጋጀ ስለሆነ ከአፍሪካ የመጀመሪያው ነው” መባሉ ብዙም ትርጉም የለውም፡፡ “ከአፍሪካ የመጀመሪያው” የሚል ተቀጥላ ሳያስፈልገው፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግስት ለቢል ጌትስ ክብር እና አድናቆቱን ገለፀ ቢባል በቂ ነው፡፡ እንዲያውም “ትልቅ ቁም ነገር” ሊሆን ይችል ነበር፡፡ ለምን በሉ፡፡
ብዙዎቻችን ብልጽግናን እየተመኘን የስኬትን ወሬ ማዘውተር ጀምረን የለ? በጐ ጅምር ነው። መንግስትም እንዲሁ ስለ እድገትና ብልጽግና እየደጋገመ ማውራቱ መልካም ነው፡፡ “ዋናው ጠላታችን ድህነት ነው” በሚል አባባል የሚታጀበው የመንግስት ንግግር፤ የአገሪቱ የወደፊት ተስፋ ያለው “ሃብት ፈጣሪ የኢንዱስትሪ ቢዝነስ” ላይ እንደሆነ ይገልፃል፡፡
ሃብት ፈጣሪ የኢንዱስትሪ ቢዝነስ የሚስፋፋው እንዴት ነው? ብላችሁ ጠይቁት፡፡ ምላሽ ይሰጣችኋል፡፡ የመንግስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ፣ የአምስት አመት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ፣ አመታዊ የኢኮኖሚ ሪፖርት…እና ሌሎች ሰነዶችን ስትመለከቱ፤ ተመሳሳይ ምላሽ ታገኛላችሁ፡፡
ከድህነት በመላቀቅ ብልጽግናን እውን የምናደርገው፤ ሃብት ፈጣሪ የቢዝነስ ሰዎች ሲበራከቱ ብቻ እንደሆነ የሚገልፀው መንግስት፤ የተማሩ ወጣቶች በሥራ ፈጣሪነት በአነስተኛና ጥቃቅን የቢዝነስ መስክ እየተሰማሩ ስኬታማ ሲሆኑ፤ ትልልቅ የኢንዱስትሪ ቢዝነስ እንደሚስፋፋ ያስረዳል፡፡ በዚህም ምክንያት “የኢንተርፕርነርሺፕ አስተሳሰብ፣ እውቀትና ክህሎት” ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ሲልም በሰነዶቹ ይገልፃል - ለአገሪቱ የብልጽግና ተስፋ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ፡፡ በአጭሩ፤ ከችጋር ሳንላቀቅ በህይወት ለመቆየት ብቻ የምንፈልግ ከሆነ እርዳታና ምጽዋት ላይ ማተኮር እንችላለን፡፡ ድህነትን ወዲያ አሽቀንጥረን ወደ ብልጽግና ለመንደርደር ከፈለግን ግን፤ በአነስተኛና ጥቃቅን ቢዝነስ ላይ ተሰማርተው ለብልጽግና የሚጣጣሩ ሚሊዮን ወጣቶች፣ ስኬታማ ሃብት ፈጣሪዎች፣ ትርፋማ የቢዝነስ ሰዎች ያስፈልጉናል ይላል መንግስት፡፡
ታዲያ ሃብት ፈጣሪ ይሆናሉ ተብለው ለሚጠበቁ ለእነዚህ ወጣቶች፣ ከእነቢል ጌትስ የበለጠ አርአያና ጀግና ከወዴት ይገኛል? እንደ አብዛኛው አነስተኛና ጥቃቅን ተቋም፤ ቢል ጌትስ ከቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት ስር፣ ጠባብ ምድር ቤት ውስጥ ነው ቢዝነሱን የጀመረው፡፡ በአካባቢው ለሚገኙ ትናንሽ ድርጅቶች አነስተኛ አገልግሎቶችንና የቴክኖሎጂ መፍትሔዎችን በመስጠት የተጀመረው የቢል ጌትስ ቢዝነስ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው፤ ቀን ከሌት በየእለቱ ለ16 ሰዓታት ያህል ተግቶ ስለጣረ ነው፡፡
በሰፈርና በከተማ ታጥሮ አልቀረም፡፡ በአገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአለም ዙሪያ፤ የሰው ልጆችን ሕይወት የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር የአለማችን ቁንጮ ሃብታም ለመሆን በቅቷል። በስኬታማነቱና በጀግንነቱ የተነቃቁ እልፍ ወጣቶችም፤ በየራሳቸው መስክ ተዓምር የሚያሰኝ የሃብት መጠን እንዲፈጥሩ አርአያ ሆኗቸዋል- በአሜሪካ ብቻ አይደለም፡፡ በቻይናም ጭምር እንጂ፡፡ ሃብትን እንደ ኩነኔ፣ በሚቆጥር ጥንታዊ ባህልና ባለሀብትነትን እንደ ወንጀል በሚቆጥር የሶሻሊዝም አስተሳሰብ ለድህነትና ለረሃብ ተዳርጋ የነበረችው ቻይና፤ “ባለሀብትነት ቅዱስነት ነው” በሚል ሃሳብ ነው የብልጽግና ጉዞ የጀመረችው፡፡ በእርግጥም ባለፉት 20 ዓመታት የቻይና ወጣቶች በአድናቆት ከሚጠቅሷቸው ጀግኖች መካከል፣ ቢል ጌትስ ተጠቃሽ መሆኑ አይገርምም፡፡ እኛም ብልጽግናን ከምር የምናከብር ከሆነ የቢዝነስ ስኬታማነቱ ትልቅ ቁምነገር መሆኑን በመገንዘብ፣ አክብሮትና አድናቆታችንን ለመግለጽ፣ የክብር ዶክትሬት ብንሰጠው መልካም ነበር፡፡ በእርግጥ ቢል ጌትስ ለኢትዮጵያ ብዙ የገንዘብ እርዳታ ሰጥቷል፡፡ ማመስገን ይገባል፡፡
ነገር ግን እርዳታና ምጽዋት፤ ለጊዜው ድህነትን ለመቋቋም ይጠቅም እንደሆነ እንጂ ለብልጽግና አያበቃም፡፡ የላቀ ክብር እና አድናቆት መስጠት ያለብን ለቢዝነስ ስኬታማነትና ለሃብት ፈጣሪነት ነው - ብልጽግናን የምናከብር ከሆነ፡፡ አሳዛኙ ነገር፤ ከእርዳታና ከተመጽዋችነት በተቃራኒ፣ የቢዝነስ ስኬትና ሃብት ፈጠራ ዋና የአገሪቱ የብልጽግና ተስፋዎች ናቸው የሚል መንግስት፤ ለቢል ጌትስ የክብር ዶክትሬት የምንሰጠው በሃብት ፈጣሪነቱና በቢዝነስ ስኬታማነቱ ሳይሆን በእርዳታ ለጋሽነቱ ነው ማለቱ ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ፤ “ባለ ሃብትነቱንና ስኬታማነቱን እናከብራለን፤ እናደንቃለን፡፡ የዛሬው ሽልማት ግን ለሰጠን እርዳታ ምስጋናችንን የምንገልጽበት ነው” ብሎ መናገር ይቻል ነበር፡፡ ይሄም ይቅር፡፡ ግን፤ እርዳታ ለመስጠት የቻለው‘ኮ፤ በቢዝነስ ስኬታማነቱ ሃብት የፈጠረ ጀግና ስለሆነ ነው፡፡ ሃብት መፍጠር እንጂ ሃብት መስጠትማ ቀላል ነው፡፡ አርአያ አያስፈልገውም፡፡  

Read 4214 times