Tuesday, 29 July 2014 14:59

“…እኛ መች አጥተነው ነው የሚነግሩን…”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“ወራሪም ፈጣሪን ላያቅ
የጣለውን በስሏል እንጂ፣ ወድቋል ብሎ ግፉ ላያልቅ…”
ይላል ሎሬት ጸጋዬ፡፡ እኛም ዘንድሮ የጣልነውን “ወድቋል” ሳይሆን “በስሏል” የምንልበት ዘመን ይመስላል፡፡ በየዓለም ጥጉ ሁሉ የምታዩት ነገር “ወድቋል” ማለት ቀርቶ “በስሏል” ማለቱ የሰውን ልጅ የሚያግባባ ብቸኛው ቃል የሆነ ይመስላል፡፡
የምር ግን…ዓለማችን ችግሯ በዛሳ! አንዱ የቸገረው ምን አለ መሰላችሁ…“ምናልባት ይቺ ምድራችን የሌላ ዓለም ገሀነም ልትሆን ትችላለች፡፡”አሪፍ አባባል አይደል! አሁን፣ አሁን የምንሰማውና የምናየው ነገር ሁሉ…አለ አይደል…“የሰው ልጅ ወደ ድንጋይ ተመለሰ እንዴ!” ያስብላል፡፡
የምር እኮ… እንዴት ነው እውቀት እየበዛ ሄደ በሚባልበት ዘመን ይሄን ሁሉ ጭካኔ የምናየው! እናላችሁ…ምድራችን በአንዱ ሲብስባት በሌላው እንኳን እንዳንጽናና ‘የተካበ’ የሚመስለው ሁሉ እየተሰነጣጠቀ ግራ ገብቶናል። ሸሽተን የምንሸሸግባቸው የውጪ ‘ቻነሎች’ የሚያሳዩን ነገሮች ሁሉ “ይሄ ስምንተኛው ሺህ ሚሌኒየሙን አልፎ… አዘናግቶ መጣብን እንዴ!” ያሰኛሉ። (በነገራችን ላይ…አሁን ያለንበትን ዘመን ከኃይማኖታዊ አስተምህሮቶችና ትንቢቶች ጋር እያጣቀሱ ‘ጊዜው መድረሱን’ የሚናገሩ እየበዙ ነው።)
ቦምብ ከሚንዳት ምድር አላቆ አበባ የሚያብባት ምድር ያድርግልንማ! እናማ…የባሩድ ሽታ በጽጌረዳ መአዛ የተተካባት ምድር ያድርግልንማ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ካወራናት እንድገማትማ…ሰውየው የገጠር ሰው ነው፡፡ እናላችሁ…የሰው ነፍስ ያጠፋና ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ ታዲያ ‘ለማተቡ፣ ለክሩ’ የሚቆም ስለሆነ መግደሉን እንደሚያምን ለዘመዶቹ ይነግራቸዋል፡፡ ስለ ህጉ ብዙም ዝርዝር ስለማያውቅ የሚወሰንበትን ግን አላሰበውም። ታዲያማ፣ ችሎት ቀርቦ የእምነት ክሀደት ቃል ሊጠየቅ ሲል አጎቱ ማስጠንቀቂያ ሹክ ሊለው ጠጋ ይለዋል፡፡ ይሄን ጊዜ ዳኛው ያዩትና “እዛ’ጋ፣ ተጠርጣሪውን ምንም ነገር ማናገር ክልክል ነው!” ብለው ይቆጣሉ፡፡ ይሄኔ አጎትየው ወደኋላ ያፈገፍግና ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ጌታዬ፣ ቢያምን እንደሚሞት፣ ቢክድ እንደሚተርፍ እሱ መች አጥቶት ነው እኔ የምነግረው!” ብሎ አረፈው፡፡
ዘንድሮ ያልሆነው ሆነ፣ የሆነው አልሆነም እየተባልን በአጠቃላይ “…እኛ መች አጥተነው ነው የሚነግሩን…” የሚያስብሉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በዓይናችን በብረቱ አጥርተን የምናየው፣ በጆሯችን አጥርተን የምንሰማው ነገር ተመልሶ ሲነገረን፡፡
እናላችሁ…አንዳንዴ ስለተለያዩ ነገሮች ሲወራ እኛ ያለንባት ራሷ ጦቢያ መሆኑን ረስተን… “እስቲ ይቺን የምታወሩላትን አገር አሳዩን… ልንል ምንም አይቀረን፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ስለ መግባባት ካወራን ይቺን ስሙኝማ… ሰውየው ክፍል ውስጥ አማርኛ እያስተማረ ነው፡፡ ደግሞላችሁ…ተማሪዎቹ ገና ጀማሪዎች በመሆናቸው ስለ ስዋስው ምናምን ብዙም የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡
እናላችሁ…በሚገባ ሳያስረዳቸው ምን ብሎ ይጠይቃቸዋል፣ “‘አበበ ከበደን በዱላ መታው’ የሚለው አረፍተ ነገር ውስጥ ግሱ የምን ግስ ነው?” ብሎ ይጠይቃል፡፡
አንደኛው ተማሪ ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ…“የወንጀል ክስ ነው፡፡” ልክ ነዋ…በዱላ መምታት ወንጀል ነዋ! “በዱላ መታው” ካሉ በኋላ ወላ ‘ገቢር ግስ’፣ ወላ ‘ተገብሮ ግስ’ ብሎ ነገር የለማ! ቂ…ቂ…ቂ… (አስተማሪው ያቀረበው የምሳሌ ዓረፍተ ነገር “አበበ ከበደችን በከንፈሮቹ ሳማት…” ቢሆን ኖሮ ግሱ ‘ተሻጋሪ’ ግስ ይሆን ነበር! ሳይገባኝስ!)
እናማ…ችግሩ የመላሹ ሳይሆን የአስተማሪው ነው፡፡ ዘንድሮም አብዛኛው ችግር የእኛ ‘የመረጃ’ ተቀባዮች ሳይሆን የእነሱ ‘የመረጃ’ ሰጪዎቹ ነው። የእውነት መረጃ የሚሰጡን ሳይሆን እኛ ጥቁር ያልነውን እነሱ “ቀይ ነው ብያለሁ ቀይ ነው…” አይነት ነገር ይሆናል፡፡ ይሄኔ ታዲያ እኛ ደግሞ…ጮክ ብለን ባንናገር እንኳን በሆዳችን “…እኛ መች አጥተነው ነው የሚነግሩን…” እንላለን፡፡
(ያን ሰሞን የድራፍት ዙሪያ ‘ሀሜታ’ ላይ “እንኳን ጮክ ብለን ጠንከር አድርገን ስንተነፍስም ዓይን በዝቶብናል…” ያልከው ወዳጄ ‘አድናቂህ’ ነኝ።) በነገራችን ላይ…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…በአንድ ተጠባባቂ ተጫዋች ብቻ የነጥብ ዓለም አቀፍ ጨዋታ በመጫወት ከዓለም ስንተኛ ነን! አይ ጦቢያ! እኔ የምለው… ‘እሱ ሰፈር’ በዛ ሰሞን “ተሽሎታል…” ምናምን ሲባል አልነበረም እንዴ! ኮሚክ ነገር እኮ ነው…ፓስፖርት ላይ የተጻፈ ዓመተ ምህረት አይቶ ‘ለመደመርም’ ካሽ ሬጂስተር ማሺን ምናምን ሊያስፈልገን ነው ማለት ነው!
ደግሞላችሁ የኳስ ነገር ካነሳን አይቀር… ኳስ ጨዋታዎች በቲቪ ላይቭ ሲተላለፍ ‘ኮሜንተሪ’ የሚያሰሙት…ሁሉም እንቅስቃሴ ‘ሙሉ አረፍተ ነገር’ መሆን አለበት እንዴ! “የእንትን በረኛ ለመሀል ተከላካዩ…” እንዳቀበለው በመግለጽ የተጀመረው ዓረፍተ ነገር እስኪጠናቀቅ ኳሷ በሰባት በስምንት እግሮች ተነክታ ትመለሳለች። እንዴ… ጨዋታውን እኛም እያየነው እንደሆነ ልብ ይባልልና! አለበለዛ “ስምንት ቁጥሩ አንጋጋው አናጌ ከባላጋራ ተጫዋቾች መሀል ከፍ ብሎ ዘሎ ኳሷን በጭንቅላቱ ገጫት…” አይነት ነገር ግስ፣ ስም፣ ተውላጠ ስም፣ ተሳቢ፣ ቦዝ አንቀጽ ምናምን አሥራ ስምንት የንግግር ክፍል ያለበት ይመስላል፡፡ ዓረፍተ ነገሩ ሲጀመር ምጥ የጀመራት ሲያልቅ ልትወልድ ትችላለች እኮ! (ቂ…ቂ…ቂ… እኛም የማጋነን ዕድል ይድረሰና!)
የምር ግን ላይቭ ኮሜንታሮቻችን ዘዴያቸውን መፈተሽ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡  ደግሞ የተጫዋቹ ቁጥር እየቀረ ስም ከእነ አባቱ ሳይቀር ሁሉም መባል የለበትም፡፡ አንጋጋው አናጌ በአንድ ጨዋታ ላይ ሙሉ ስሙ የተጠቀሰውን ብዛት ከቄስ ትምህርት ቤተ ጀምሮ መዝገቦች ላይ የተጻፈው ተደምሮ አይደርስበትም፡፡ (‘ማጋነን’ ለመደብኝ ማለት ነው!)
ከተጨዋወትን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…‘በኮሚዋ’ ሩስያ ዘመን የኮሚኒስት ፓርቲው የምስረታ በዓል እየተከበረ ነበር፡፡ እናላችሁ…በአንድ የሀገሪቱ አውራጃ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ልዩ ዝግጅት ነበር፡፡ በዝግጅቱም ላይ የአካባቢው የፓርቲ ሊቀመንበር ንግግር ያደርጋል።
“የተወደዳችሁ ጓዶች!” ከአብዮቱ በኋላ ፓርቲያችን ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ልብ በሉ። ለምሳሌ እዚህ አጠገቤ ያለችውን ማሪያን ተመልከቱ፡ ከአብዮቱ በፊት ምን ነበረች? ማንበብ መጻፍ የማትችል መሀይም አርሶ አደር፡፡ የነበራት አንዲት ቀሚስ ብቻ ነበረች፣ ጫማም ስላልነበራት በባዶ እግሯ ነበር የምትሄደው፡፡ አሁንስ? አሁን በአካባቢያችን ቤት ለቤት በመዞር ወተት በመሸጥ ትታወቃለች፡፡ ወይንም ኢቫን አንድሪቭን ተመልከቱት፡፡
በሰፈራችን የነጣ ድሀ ነበር፡፡ ፈረስ የለው፣ ላም የለው፣ መጥረቢያ እንኳን የለውም ነበር። አሁንስ? አሁን ትራክተር አሽከርካሪ ነው። ደግሞም ሁለት ጫማ አለው፡፡ ዕድሜ ለአብዮቱ ሁለት ጫማ! ወይ ደግሞ ትሮፊም ሴሜኖቪች አሌክሲቭን ተመልከቱት፡፡ የለየለት ወሮበላ፣ ሰካራምና መቼም የማይጸዳ ነበር፡፡ ያገኘውን ምንም ነገር ከመስረቅ ስለማይመለስ ማንም ሰው አያምነውም ነበር። አሁን ግን ዕድሜ ለአብዮቱ የፓርቲ ኮሚቴው ጸሀፊ ሆኗል።”
እኔ የምለው…እኛ ዘንድ ተመሳሳይ ‘ስኬቶች’ ካሉ ይገለጹልንማ!
እናላችሁ… በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን፣ በእነፌስቡክ ዘመን፣ በትዊተር ዘመን፣ በዩ ቲዩብ ምናምን ዘመን “…እኛ መች አጥተነው ነው የሚነግሩን…” ባንባባል አሪፍ ነው፡፡ አሥር ወር ገበያ ላይ ቆይቶ መውጣቱን እንኳን ሰው ነገሬ ያላላውን አልበም “በከፍተኛ ደረጃ እየተሸጠ ነው…” አይነት ነገር ስንባል፤…ሰው ሳይበዛ ገብተን እንደ ቲያትር ቤት መዳፋችን የዝንጀሮ እንትን እስኪመስል ድረስ ካላጨበጨብን አስተናጋጆች ብቅ የማይሉበትን ሬስቱራንት “በዚህ ሬስቱራንት ደንበኛ ንጉሥ ነው…” ምናምን ስንባል፤ ሀሳብ የሚሰጥ ጠፍቶ ሰብሳቢዎቹ… አለ አይደል… የስብሰባው መሪዎችም፣ የስብሰባው ንቁ ተሳታፊዎችም እነሱ ብቻ በሆኑበት “ከፍተኛ የሀሳብ ልውውጥ የተደረገበት ስብሰባ…” ሲሉን…በቃ ቀሺም ነገር ነው፡፡
በትንሹም በትልቁም “…እኛ መች አጥተነው ነው የሚነግገሩን…” የማንባባልበትን ዘመን ያምጣልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3795 times