Saturday, 24 December 2011 09:58

ይህቺ አገር የማናት?

Written by  በፍቃዱ አባይ
Rate this item
(0 votes)

“ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል”

ይህቺ ናት…ይህቺ ናት ሐገሬ

የትውልድ መንደሬ…

የሚሉት የኩኩ ሰብስቤ ቆየት ያለ የዘመን አዝማች ግጥሞች ሰሞኑን አንደበቴን ተቆጣጥሮት ሰነበተ፡ አንዳንዴ ሆድ ሲብስ አሊያም በትዝታ ያለፉበትን ሲያስታውሱ እነዚህን መሰል ዜማዎች ማንጐራጐር የተለመደ ነው፡፡ እኔም ሰሞኑን እነዚህን አዝማች ስንኞች ስደጋግማቸውን የሰነበትኩት በቀዳሚው ምክንያት ነው፡፡ ህዳር 17 ቀን 2004 ዓ.ም የተካሄደውን የታላቁን ሩጫ በኢትዮጵያ መጠናቀቅ ተከትሎ በግሌ የደረሰብኝ ውጣ - ውረድ አንድም ለትዝታ ሌላም ለመከፋቴ ማጀቢያ ሆኖኝ ሰንብቷል፡፡

ሐገር ያለ ህዝብ ባዶ ነው፡፡ መንግስት ማለት ህዝብ የሚሆነውም፤ ህዝብ በወኪሎቹ ተስፋ ሲያደርግ ነው፡፡ ሰዎች ያለአግባብ የሚታሰሩባት፤ በአንድ ሐሳብ ላይ የሚነሱ ልዩነቶች ግለሰቦችን  ወዳልተፈለገ ችግሮች ሲመሩ፤ ይህቺ ሐገር የማናት? የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ እንደ ተሰጥኦአቸውና ፍላጐታቸው በጐ ስራን ለመስራት የሚነሱ ሰዎች ከጀርባህ ማን አለ? የሚል ማሸማቀቂያ ሲለጠፍባቸው፤ አለፍ ሲልም ለእስርና እንግልት ሲዳረጉ “ይህቺ ናት ሐገሬ”ን ያንጐራጉራሉ፡፡ በመንግስታዊ መዋቅር ስር ባሉ ግለሰቦች አሊያም አስፈፃሚዎች የተሳሳቱ አሰራሮች ምክንያት ግለሰቦች ጣታቸውን ወደ መንግስት ለመቀሰር ይገደዳሉ፡፡ ለተወለዱባት ሐገር፤ እትብታቸውን ለቀበሩባት ከተማ፤ ከልጅነት እስከ ጉልምስና ላሳደገ ማህበረሰብ የአቅምን ለማበርከት ማንንም ከጀርባ ማሰለፍ፤ ከማንም ጀርባ መሰለፍም አያስፈልግም የሚል እምነት አለኝ፡፡ አንድ ግለሰብ በተሰጠው ሐላፊነት ብቻ ታምኖ ሰዎችን የሐጢያት ካባ ሲደርብባቸው ዝም ብሎ መመልከት ለመንግስትም ለህዝብም አይመችም፡፡ የከሳሽንም የተከሳሽንም ግራና ቀኝ ማየት፤ ማመዛዘንና መጠየቅ ያስፈልጋል፡ ማንም ቢሆን ከህግ በላይ መሆን የለበትም፡፡ ሲያጠፋ  ሊጠየቅ፤ በህግ አግባብም ተገቢውን ቅጣት ሊያገኝ ግድ ይለዋል፡፡ ይህ ዓለማቀፋዊ ስምምነት የሚፈፀምበት አግባብ ግን ሊለያይ ይችላል፡፡ ከጀርባህ ምን አለ ሳይሆን ከጀርባው ምን እንዳለ አረጋግጦ ለህግ የሚያቀርብ የህግና የደህንነት አሰራር ያስፈልገናል፡፡ ሰዎችን አስሮ ማስረጃ የሚያፈላልግ፤ ላሰራቸው ግለሰቦች ተጨባጭ የሆነ ማስረጃ የማያቀርብ ወይም ሰዎችን አስሮ ማስረጃ መፈለግ የሚጀምር የህግ አሰራር  እንዲኖረን መመኘት የለብንም፡፡ ምክንያቱም በእነዚህ መጣረሶች መሐከል የሚጉላሉት ሰብአዊ ፍጡራን በመሆናቸው ብቻ ሊጐናፀፉአቸው የሚገቡና የተረጋገጡ መብቶቻቸውን ሊነፈጉ ይችላሉ፡፡ ችግሩን ሰፋ አድርገን ስናየውም በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ስር የሚተዳደሩ በርካታ ቤተሰቦች፤ መከወን የሚገባቸው ስራዎች፤ በእነዚህ ስራዎች  መከወን ተጠቃሚ የሚሆኑ ግለሰቦች፤ ድርጅቶችና መንግስት ተገቢውን ጥቅም ያጣሉ፡፡

ይህንን ሐሳቤን በግልጽነትና ካለምንም መቀባባት ለአዲስ አድማስ አንባቢያን በማድረስና ባለማድረስ ረገድ ከራሴ ጋር ስሟገት ሰንብቻለሁ፡፡ የኔን የ10 ቀናት የእስር ቤት ቆይታና ተጠርጥሬ የተከሰስኩበትን የክስ አይነት በመግለጽና ባለመግለጽ መሀከል ስላሉት ልዩነቶችም ስመዝን ቆይቻለሁ፡፡ ጉዳዩ አስቀድሞ ራስን መከላከል ይመስልብኝ ይሆን? ስልም ከራሴ ጋር ተጣልቼአለሁ፡፡“ዝምታ ወርቅ ነው” የሚለውን የሐገሬን ብሂልም ከእውነት አንጻር መዝኜዋለሁ፡፡ ይህንን ጽሑፍ በመጻፌ ሊከሰቱ በሚችሉ መጻኢ ችግሮች ዙሪያም አስቤበታለሁ፡፡ ከልቤ የምወደውን የጋዜጠኝነት ሙያዬንም ከግምት ውስጥ አስገብቼዋለሁ፡፡ በአስር ቀናት የእስር ቤት ቆይታዬ ቤተሰቦቼ፤ ጓደኞቼ፤ የስራ ባልደረቦቼ፤ ወዳጆቼና ሌሎች ስለእኔ የደከሙትን ሁሉ አስቤላቸዋለሁ፡፡ አብረውኝ ስላሳለፉት የጭንቅ ቀናትም አክብሮቴና ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው፡፡ እኔ የማንም የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊም ተቃዋሚም ስላለመሆኔም ለራሴ አውቃለሁ፡፡ በእነዚህ ሙግቶቼ መሐከል ግን ሐሳቤን መግለጼ አመዝኖ አሸነፈኝ፡፡ ይህ ሐሳቤን ማካፈሌም ለአዲስ አድማስ አንባቢያን ብቻም ሳይሆን ለመንግስት ባለስልጣናትም ጭምር ጠቀሜታ እንዳለውም አመንኩ፡፡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ፤ ሐገሬ የኔም የሁላችንም ስለመሆኗ ተቀበልኩ፡፡ ይህንን ሐሳቤን ለመንግስት ባለስልጣናት ጭምር የምገልፀውም ከህዳር 17 ቀን 2004 ዓ.ም እስከ ህዳር 27 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ የነበርነውን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተጠርጣሪዎች ሁኔታ አያውቁም ከሚል የዋህ መነሻ በመነሳትም አይደለም፡፡ ከዝምታ ሐሳብን መግለጽ ይሻላል ከሚል የዜግነት ግዴታ በመነሳት ነው፡፡

በዚህች አጭር የህይወት ዘመኔ በሙያዬ፤ ባለችኝ ትንሽ ልምዴና በፍላጐቴ ሐገሬንም ራሴንም በመጥቀም ላይ እንደምገኝ ይሰማኛል፡፡ ለዚህም ነው “ማንበብ ሙሉ ያደርጋል” ብለን ከባልደረቦቼ ጋር የበኩላችንን ለመወጣት የምንውተረተረው፡፡ ሐሳቤን በነጻነት እንድገልጽ የሚያስገድደኝም ይህ አቋሜ ነው፡፡ በትክክልም ማንበብ ሙሉ ያደርጋል፡፡ የሚያነብ ህብረተሰብ ያላቸው ሀገራት ለዕድገታቸው መፋጠን እገዛ ካደረጉላቸው ጉዳዮች መሀከል በንባብ የበለፀገ ልማድ ባለቤቶች መሆናቸው ነው፡፡ ሰዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው ከመማራቸው ባሻገር በንባብ የሚያገኙአቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ምክንያት ለራሳቸውም ሆነ ለሐገራቸው የሚበጁ ፋይዳዎችን ለማበርከት ችለዋል፡፡ ህይወት በሂደት ከምትለግሳቸው ትምህርትና በተቋማት ደረጃ ከሚያገኟቸው ዕውቀቶች ያመለጡትን ዕውቀቶችና ተሞክሮዎች በንባብ በማዳበርና ክፍተቶቻቸውን በመሙላት አሁን የደረሱበትን ደረጃ ለማረጋገጥ ችለዋል፡፡ ሐገራችንም በተለይ በአሁኑ ወቅት የሚያነብ፤ የሚመራመር፤ የሚጠይቅ፤ ራሱንና ማንነቱን ጠንቅቆ የሚያውቅ ትውልድ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ደርሳለች፡ ደካማ የንባብ ባህል ይዞ ማ ደግ፤ መለወጥ፤ ከዘመን ዕኩል መራመድ፤ ራስን ከአካባቢ ጋር ማዋሐድና መፍትሔ ማፍለቅ አይቻልም፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብቶ በመማር የሚገኘውን ዕውቀት በንባብ ማዳበር ካልተቻለ ከጥቂት አመታት በኋላ በትምህርት የተገኘው ዕውቀት ባይጠፋ እንኳ በመደብዘዙ አይቀርም፡፡የእኔና የባልደረቦቼ ጥቂት ጥረትም ይህን ክፍተት ለመሸፈን የሚደረገውን ሙከራ ለማገዝ ነው - የኤፍ ኤም አዲስ 97.1 የስራ ባልደረቦችና የኮሚሽኒንግ ዳይሬክቶሬት እገዛ ታክሎበት፡፡ ለእስር የተዳረኩበትና የተከሰስኩበትን የክስ አይነት ወደፊት በፍ/ቤት የምከራከርበት ሆኖ ስለተነሳሁበት ዓላማና ስለአያያዜ እንዲሁም በአስር ቀናት የእስር ቤት ቆይታዬ የታዘብኳቸውን ዕይታዎች እነሆ ብያለሁ፡፡

የህዳር 17 ውሎና የእቅዶቼ መሰናከል

አዲስ አበባ በእቴጌ ጣይቱ እንደ ከተማነት ተመስርታ አመታትን ማስላት ከጀመረች 125 ዓመታትን የምትቆጥርበት ዕለት ህዳር 17 ቀን 2004 ዓ.ም ነበር፡፡ እጄ ላይ ባለው መረጃ መሰረት አሁን ከተማችንን በማስተዳደር ላይ እስከሚገኙት ክቡር ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ድረስ 28 ከንቲባዎችን የምታውቀው መዲናችን፤ በዚህ የልደቷ ቀን ሰላሳ አምስት ሺህ ተሳታፊዎችን ያካተተውን የታላቁ ሩጫ ውድድርን ማድረጓ ለልደቷ ልዩ ድምቀት አጐናጽፏታል፡፡ በዚህ የሐሳብና የአካል መዋሀድ ውስጥ ሆኜ ነው የእለቱን ውሎዬን ለመጀመር በዚህ ታላቅ ውድድር ላይ የተሳተፍኩት፡፡ በየአመቱ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሰራተኞች በቡድን በቡድን በመሆን ይሮጣሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚም የተቋሞቻቸውን አላማዎች የሚያስገነዝቡ መልዕክቶችንም ለታዳሚው ያስተላልፋሉ፡፡ በዘንድሮው ሩጫ ላይ የነበረው መንፈስም ከወትሮው የተለየ ባለመሆኑ እኔና የስራ ባልደረቦቼ፣ በኤፍ.ኤም.አዲስ 97.1 ላይ ዘወትር እሁድ ምሽት ከ2፡00-4፡00 ሰዓት ድረስ የሚተላለፈውንና በንባብ ባህል መዳበር ላይ የሚያተኩረውን “ብራና” የተሰኘውን የሬዲዮ ፕሮግራም ለማስተዋወቅ ዕቅድ ይዘን በውድድሩ ተሳትፈናል፡፡ “ማንበብ ሙሉ ያደርጋል” በሚል መሪ ቃል ስር ዝግጅታችንን አስተዋውቀን ከጨረስን በኋላ የገጠመኝ ሐቅ ግን የተለየ ነበር፡፡

ውድድሩን ጨርሼ ሜዳልያዬን ተረክቤ ወደ መኖሪያ ቤቴ በመሄድ ወደ ቀጣዩ የእለቱ ዕቅዴ ለማምራት የነበረው ጉዞዬ የተሰናከለው፣ ሂልተን ሆቴል በር ላይ በጥበቃ ስራ ላይ ተሰማርቶ የነበረ የፌዴራል ፖሊስ አባል እኔና ጓደኛዬን እንደሚፈልገን ከገለፀልን በኋላ ነበር፡፡ ቆየት ብሎ የመጣ ሲቪል ለባሽ የደህንነት ሰራተኛም ለጥያቄ እንደምንፈለግ ገልጾ ወደ ቂርቆስ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ (የቀድሞ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ) ወሰደን፡፡ ከቀኑ  በስምንት ሰዓት በብሔራዊ ሙዚየም ትንሿ አዳራሽ፣ በሚዩዚክ ሜይዴይ አማካይነት የሚካሄደውን የመጻሕፍት ውይይት መድረክ የምመራው እኔ በመሆኔ፣ ከጣቢያው ጥያቄ በኋላ በፍጥነት ወደ ስራዬ ለመመለስ ፍላጐቴ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ለ10 ቀናት በእስር ላይ መቆየት ነበረብኝ፡፡ በእለቱ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የመጻሕፍት ውይይትም ሳይካሄድ ቀረ፡፡ በዕለቱ ሌላው የተስተጓጐለው ስራዬ ለ“ብራና” የሬዲዮ ፕሮግራም ብዬ የአዲስ አበባን የ125ኛ አመት በማስታከክ፣ ለአድማጮች ያዘጋጀኋቸውን መረጃዎች ለማድረስ ያለመቻሌ ነው፡፡ ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ እንዲሉ ፍ/ቤት የሰጠን ዋስትና ተጠብቆ፣ ከቤተሰቦቼና ከወዳጆቼ ጋር ዳግም ለመገናኘት አስራ አንድ ቀናትን መጠበቅ ነበረብኝ፡፡

 

የተከሰስንበት የወንጀል ክስ አይነትና እኔ

ፖሊስ ለፍ/ቤት ባቀረበው የክስ መዝገብ ላይ እንደገለፀው፤ በሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት በመሞከር ወንጀል” የሚል ርዕስ ያለው የክስ አይነት ለእስር የዳረገን የወንጀል ጭብጥ ነው፡፡ በዕለቱ በተካሄደው የሩጫ ውድድር ላይ ከእኔ ጋር 27 ተጠርጣሪዎች ባይሳካላቸውም ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ሙከራ አድርገዋል፤ መንግስትን በፀያፍ ቃላት ሰብደዋል በሚል ተከሰናል፡፡ መተሳሰባችን፤ ጨዋታዎቻችንና የሌሎቹ እስረኞች እንክብካቤ ባይኖር ኖሮ እንደኔ በቀን ውስጥ የተለያዩ የመዲናዋን መንደሮች በስራው ጠባይ ምክንያት ለሚያካልል ሰው አስሩ ቀናት አስር አመታት ይሆኑበት ነበር፡፡ በእስር ቤቱ ካሉት ስድስት ክፍሎች መሐከል አምስቱ በወንድ እስረኞች ሲያዝ፤ ቀሪው አንድ ክፍል ለሴት እስረኞች የተለቀቀ ነው፡ እነዚህ ክፍሎች የብዛታቸውን ያህል ያላቸው ስያሜም የተለያየ ነው፡፡ እኔ የነበርኩበት ክፍል ካለው ስፋት፤ በውስጡ ከሚታሰሩ እስረኞች ስብጥና አንጻርና በሌሎች መመዘኛዎች ቦሌ የሚል ስያሜን አግኝቷል፡፡ ባንጻሩ በክፍሉ ጥበት፤ በእስረኞች ቁጥር መብዛትና የተጠርጣሪዎች ማንነት አንጻር ጨርቆስ የሚል ስያሜን ያገኘ ክፍልም አለ፡፡ ሌላው በእስር ቤት ያስተዋልኩት ችግር በተለያዩ ክሶች ተከሰውና በፍ/ቤት ዋስ ተብለው የዋስ መብቶቻቸውን የሚያስከብርላቸው ዘመድ አዝማድም ሆነ የተጠየቁትን ገንዘብ ለመክፈል ባለመቻላቸው ለረጅም ጊዜያት በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ማግኘታችን ነው፡፡ ከአንድ መቶ እስከ አንድ ሺህ ብር የሚደርስ ዋስትና በማጣት በጣቢያው ይገኙ የነበሩ ስምንት እስረኞችን ገንዘብ በማዋጣት እንዲፈቱ ማድረጋችን በአስርቱ ቀናት ቆይታችን ከተደስትንባቸዉ ምግባሮቻችን መሐከል የሚጠቀስ ነው፡፡ እስራችን ለበጎ ነው ብለን እንድንጽናና ያደረገንም ለእነዚህ ወገኖቻችን መድረስ በመቻላችን ነው፡፡ ይህን መሰል ዕድል በተሰጣቸው ጊዜ መሰረት ለማሟላት ባለመቻላቸው ዳግም መዝገባቸው የተከፈተባቸው እስረኞችንም ሳስታውስ ምነው ቀደም ብለን ባገኘናቸው አብስሎኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማንም ሰው በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥሮ ሲታሰር በግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ የምንወስዳቸው የማግለል እርምጃዎች ዞረው ዞረው የሚጎዱት ራሳችንን እንደሆነ ትምህርት አግኝቻለሁ፡፡ እነዚህ ተጠርጣሪዎች ለዚህ መሰሉ ድርጊት የሚጋለጡባቸው መንስኤዎችን በማጥናት መልካም ዜጋ ሊሆኑ የሚችሉባቸው እድሎችን በከንቱ እያባከንናቸው፤ ወጣቶቹም በኛ ተስፋ እየቆረጡ በወንጀል ድርጊቶቻቸው እንደሚገፉ ተረድቼአለሁ፡ ወጣቶቹ ቀርቦ ላናገራቸው ልባቸው ክፍት፤ አንደበታቸው ለስላሳ ነው፡፡

ነጻ ፍ/ቤት

በፍትህ ስርአት ውስጥ ሊኖር ስለሚገባ ትክክለኛና ነጻ ውሳኔ አስመልክቶ የተለያዩ ክርክሮች ይደረጋሉ፡፡ ለአንድ ሀገር የመልካም አስተዳደር መጓደልም ሆነ መጠናከር እንደ ማሳያ ከሚጠቀሱት መለኪያዎች አንደኛው በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚታዩ አሰራሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ መለኪያዎት በትክክል ይፈጸሙባቸዋል በሚባሉ ሐገራትም ዜጎች በእኩልነትና በነጻነት የመዳኘት እድል ባለቤት ይሆናሉ፡፡ ከማንም ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት የጸዱ ውሳኔዎችን መስጠት የሚችሉ የፍትህ አካላት ለዜጎች እኩልነት መኖር የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ፡፡ በዚህ ረገድ ፍ/ቤቶቻችን ስላላቸው የአሰራር ነጻነትና ወገንተኛነት በተመለከተ የሚሰጡት አስተያየቶች ለየቅል  እንደሆኑ  ከምሰማቸውና ከማነባቸው መረጃዎች አንጻር ወደየትኛው ማመዘን እንዳለብኝ ሳልገነዘብ ቆይቻለሁ፡፡በእኔ የፍርድ ቤት የአራት ጊዜያት ምልልስ ብቻ የተነገዘብኩት እውነት ግን የፍርድ ቤቶችን ነጻ መሆን ነው፡፡ ጉዳያችን ፖለቲካዊ በመሆኑ የተነሳ መፍትሔ ማግኘትን በተመለከተ በእስር ቤት ቆይታችን ወቅት የነበረን ስምምነትም ጉራማይሌ ነበር ለማለት እችላለሁ፡፡ በዚህ በኩል ቀደም ሲል እንሰማቸው የነበሩ ታሪኮች ተጽዕኖ እንዳሳደሩብንም የተገነዘብኩት ዘግይቼ ነው፡፡ ከመጀመሪያው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ አንስቶ (ከህዳር 18 ቀን 2004 ዓ.ም) የዋስ መብታችን ይከበር ዘንድ በፍርድ ቤት የተሰጠንን ውሳኔ በመቃወም፣ ጉዳዩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በይግባኝ ሰሚ ሰበር ፍ/ቤት እስከታየበት የመጨረሻ የፍርድ ቤት ውሎዬ (ታህሳስ 26 ቀን 2004 ዓ.ም) ድረስ በግሌ ለመታዘብ የቻልኩት የፍርድ አሰጣጥ ሒደቱ ከምንም አይነት ተጽዕኖ ነጻ መሆኑን ነው፡፡ እንደኔ ከዚህ ቀደም ፍ/ቤት በተከሳሽነት ቀርቦ ለማያውቅ ተጠርጣሪ፤ ዳኞች ከከሳሻችን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተወካዮች ጋር በማስረጃ አቀራረብና በጊዜ ቀጠሮ አጠያየቅ ዙሪያ የነበራቸው የህግ መሰረት ያለው ከርክር የማይታመን ነበር ለማለት ይቻላል፡ በተለይም ባልዋልኩበት የወንጀል ክስ ያለአግባብ ታስሬያለሁ ለሚል ተከሳሽ ሂደቱ ክስተት ነበር፡ ዳኞች፤  ተከሳሾች ያለአግባብ እንዳንጉላላ፣ ተገቢ የተባለና የተረጋገጠ ማስረጃ በመጠየቅ፤ የፖሊስን ተጨማሪ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ በመመርመርና በሌሎች መከራከሪያ ጭብጦች ላይ ያሳዩት ነጻ ህግንና ህሊናን መሰረት ያደረገ ውሳኔ የማይታመን ትዕይንት ነበር፡፡ ማየት ማመን ከሆነ የእኛን የፍርድ ቤት ሂደት ፍትሐዊነት መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከማንም የበላይ አካል ተጽዕኖ ነጻ የነበረ የፍርድ ቤት ሂደትን ለሌሎችም መመኘትም መልካም ይመስለኛል፡፡

የታላቁ ሩጫ አዘጋጆች

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላለፉት አስር አመታት እያሳያቸው ያሉት እመርታዎች  የትየለሌ ናቸው፡፡ በገንዘብ ልገሳ፤ በተሳታፊዎች ቁጥር፤ ተቀባይነትን በማግኘት ረገድ፤ በመልካም አርአያነት እና ሊዘረዘሩ በሚቻላቸው ተጨማሪ ስኬቶቹ ለአዘጋጆቹ ከፍ ያለ ክብር አለኝ፡፡ ይህ አመታዊ ውድድር ከውድድርነቱ ባሻገርም ሰዎች እርስ በእርስ  ያላቸዉን ግንኙነት የሚያጠብቁበትና ለጤናቸውም ትኩረት እንዲያደርጉ ቆም ብለው እንዲያስቡ እድል የሚያገኙበት ታላቅ ውድድር ነው፡፡ ከዚህ በተለየ መልኩ ግን ለመንግስትም ሆነ ለተወዳዳሪዎች ስጋት መሆን ያለበት አይመስለኝም፡፡ መንግስት ህዝብ ምን ይላል? እያለ የሚሰጋበትና ከተወዳደሪው ያላነሰ የደህንነት ሰራተኞችን እያሰማራ ያሻውን የሚይዝበት መድረክ መሆንም አይገባውም፡፡ ተወዳዳሪዎችም ከወጡበት አላማ ውጪ ስጋት ውስጥ እየገቡ የሚሳቀቁበት እንዲሆን መፍቀድ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ መንግስት እንደሚለው የተለየ አጀንዳ ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖችም ካሉ ለሰላማዊው ተሳታፊ ጠንቅ መሆን ሊፈቀድላቸው አይገባም፡፡ ስፖርት የሰላም እንጂ የስጋት መድረክ እንዳይሆን በመጠንቀቅ ውድድሩን ማካሔድ የአዘጋጆቹ አንደኛው ሐላፊነት መሆን ይገባዋል፡፡ ከዚህ አንፃር በውድድሩ ወቅት እንዲህ እንደኛ ለእስር የሚዳረጉ ተሳታፊዎች መኖራቸውን በማጣራት ስለተፈጠሩት ችግሮች ማረጋገጥና እውነቱን ከውሸት መለየት ይገባቸዋል፡፡ እኔ እንደታዘብኩት ግን የውድድሩ አዘጋጆች በእለቱ ውድድር ምክንያት ለእስር ከተዳረግነው ተሳታፊዎች መሐከል አንዳችንም ለማነጋገርና ለመጎብኘት ሲሞክሩ አላጋጠመኝም፡፡ የመረጃ እጥረት አለ እንዳይባል ሰፊ ሽፋን ያገኘ ዜና ነበር፡ ከኛ መታሰር ይልቅ የሻ/ቃ ሐይሌ ገ/ስላሴን ኪስ ዳብሶ በጸጥታ ሐይሎች የተያዘው የኪስ ቀበኛ ዜና ለአዘጋጆቹ ሚዛን ሳይደፋ የቀረ አይመስለኝም፡፡ እንደሚመስለኝ ችግሩን የጋራ  አድርጎ ያለመውሰድ ችግር ይመስለኛል፡፡ በግሌ ለራሴና ለቤተሰቤ ደህንነት ስል ከዚህ በኋላ በታላቁ ሩጫ ላይ ላለመሳተፍ ወስኛለሁ፡፡ ምክንያቱም በስጋት መሳተፍ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ብዬ ስለማምን ነው፡፡

አንድም ቀን “ይህቺ ናት ሐገሬ?” ብዬ ተክዤም ጠይቄም አላውቅም ነበር፡፡

በታላቁ ሩጫ የገጠመኝ ችግር ግን ይህንን ዕንድል አስገደደኝ፡፡ ያም ቢሆን ታዲያ ተስፋ አልቆርጥም፡፡ ሐገሬ ከኔ የምትፈልገው ትልቅ የቤት ስራ ከፊቴ እንደተደቀነ ሁሌም  አስባለሁ፡፡ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል፡፡

 

 

Read 3310 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 10:09