Tuesday, 29 July 2014 14:40

የአቶ መላኩ ፈንታን ቀሪ ምስክሮች ለመስማት ለመጪው ዓመት ተቀጠረ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

    የቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ በተናጥል በቀረቡባቸው ክሶች ላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን የመስማት ሂደት በመጪው ሳምንት በጊዜ መጣበብ ምክንያት ሊካሄድ የማይችል ከሆነ ለመጪው ዓመት ይተላለፋል በማለት ፍ/ቤቱ መደበኛ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት፣ ከትናንት በስቲያ ሀሙስ በጠዋት ክፍለ ጊዜው የአቃቤ ህግን አንድ ምስክር ካስደመጠ በኋላ፣ በሰጠው ትዕዛዝ በአቶ መላኩ ላይ በቀረቡ ቀሪ ክሶች ላይ ምስክሮችን ለመስማት የሚያስችል ጊዜ በመጪው ሣምንት ስለመኖሩ አቃቤ ህጎች በፅ/ቤት በኩል ጠይቀው እንዲረዱ፣ ካልሆነም ጉዳዩ ወደ ቀጣይ ዓመት ተሸጋግሮ ከጥቅምት 24-27 ምስክሮች በተከታታይ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ከትናንት በስቲያ አቃቤ ህግ ያቀረባቸው ምስክር የጉምሩክና ገቢዎች መ/ቤት ሠራተኛ ሲሆኑ “ያማቶ ኢትዮጵያ” የተባለው ድርጅት ላስገባው እቃ ቀረጥ ስለመክፈሉ እንዲያጣሩ በመስሪያ ቤታቸው በኩል የስራ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው እንደነበር በመግለጽ ነው ምስክርነት መስጠት የጀመሩት፡፡ የማጣራት ሂደቱን ሲያከናውኑም ኩባንያው ከተቋቋመበት 1996 እስከ 2001 ዓ.ም ጀምሮ የሉዲ ቀለምን በብቸኝነት ወደ ሃገር ውስጥ አስገብቶ ለሶስት ግለሰቦች ያከፋፍል እንደነበር፣ ይህን ሲያደርግም ሽያጩን ያለ “ቲን ነምበር” እንደሚያከናውን እንዲሁም የሶስቱ ነጋዴዎች አድራሻን መዝግቦ አለመያዙ እንደተደረሰበት፣ የኩባንያው ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ ኢብራሂም “ለምን ያለ ቲን ነምበር ትሸጣላችሁ?” ተብለው ሲጠየቁ “አናውቅም ነበር፤ ለወደፊት እናዘጋጃለን” በማለት በራሳቸው ሳይሆን በሚስታቸው ስም “ቲን ነበር” አውጥተው ሽያጭ ማከናወን እንደጀመሩ አብራርቷል፡፡
በምርመራው ወቅትም ሉዲ ቀለምን ከ “ያማቶ ኢትዮጵያ” የሚረከቡት የሶስቱ ነጋዴዎች የባንክ ሂሳብ አቶ ሙደሰር ጢሃ በተባሉት አንደኛው ነጋዴ የሚንቀሳቀስና እቃዎቹን ከ “ያማቶ” ተረክበው በአንድ መጋዘን እንደሚያከማቹ እንደተደረሰበት ምስክሩ አስረድተዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪም አድራሻና “ቲን ነበር” የሌላቸው እስከ 200 ሺህ ብር ግብይት የተፈጸመባቸው ደረሰኞች መገኘታቸውን ምስክሩ አስረድተዋል፡፡
ምስክሩ ከተከሳሽ ጠበቆች የቀረቡላቸውን መስቀለኛ ጥያቄዎችና የፍ/ቤቱን የማጣሪያ ጥያቄ ከመለሱ በኋላ ፍ/ቤቱ ከላይ የተመለከተውን ትዕዛዝ ሰጥቶ የግማሽ ቀኑ ችሎት ተዘግቷል፡፡

Read 1856 times