Print this page
Tuesday, 29 July 2014 14:28

2014 ለአለማችን የአየር ትራንስፖርት የቸር አመት አልሆነም

Written by 
Rate this item
(2 votes)
  •      መንገደኞች በአውሮፕላን መጓዝ እየፈሩ ነው፣ ባለሙያዎች አደጋ ቀንሷል እያሉ ነው
  • የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በአመት 65 ሚ. ዶላር ይሰበስባሉ፣ በ5 ወር ብቻ 600 ሚ. ዶላር ካሳ ይከፍላሉ

            አመቱ ለአለማችን የአየር ትራንስፖርት የቸር አልሆነም - በተለይ ደግሞ ለማሌዢያ፡፡ ከወራት በፊት የማሌዢያ አየርመንገድ ቦይንግ 777 አውሮፕላን 239 ሰዎችን ይዞ ከኳላላምፑር ወደ ቤጂንግ በመብረር ላይ ሳለ፣ ድንገት ከራዳር እይታ ውጭ ሆነ፡፡ አለም ድንገት ደብዛው የጠፋውን አውሮፕላን ፍለጋ ውቅያኖስ አሰሰ፤ ከወዲያ ወዲህ ተራወጠ፤ ወደ ሰማይ አንጋጠጠ፡፡ ከዛሬ ነገ ይገኛል በሚል ተስፋ ፍለጋው ለወራት ዘለቀ - ተስፋ እንደራቀ፡፡ አንዳች እንኳን ተጨባጭ መረጃ ሳይገኝ፤ አውሮፕላኑን የበላው ጅብ ሳይጮህ፣ ነገሩ እንቆቅልሽ እንደሆነ ዘለቀ፡፡ ማሌዢያ በላይዋ ላይ የደረበችውን ማቅ ሳታወልቅ፣ ያለፈው ሃዘን ሳይወጣላት፣ በሆነው ነገር ሳትጽናና ሌላ ነገር ሆነ - ሌላ አውሮፕላኗ በአሰቃቂ ሁኔታ ተከሰከሰ፡፡ ይህ ክስተት ለማሌዢያ ብቻም ሳይሆን ለአጠቃላዩ የአቪየሽን ኢንዱስትሪና ለመላው አለም አስደንጋጭ መርዶ ነበር፡፡

የማሊዢያው አየር መንገድ አውሮፕላን ከቀናት በፊት በበረራ ቁጥር ኤም ኤች 17 ከአምስተርዳም ተነስቶ ወደ ኳላላምፑር በመጓዝ ላይ እያለ፣ ዩክሬንንና ሩስያን በሚያዋስነው ድንበር ላይ በሚሳዬል ተመትቶ መውደቁንና 298 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ፣ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የአየር ክልል ውስጥ መብረር ወይም አለመብረር የዓለማችን ታላላቅ አየር መንገዶች ዋነኛ ጥያቄና ጭንቀት ሆኗል፡፡ ብዙዎቹ አለማቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ተቆጣጣሪዎች በዚህ የግጭት አካባቢ በረራ እንዳያደርጉ በአየርመንገዶች ላይ እገዳ ባለመጣላቸው ወይም ማስጠንቀቂያ ባለመስጠታቸው፤ አብዛኛዎቹ አየርመንገዶች የአየር ክልሉን በማቋረጥ ከአውሮፓ ወደ ደቡብ ምስራቅ እስያ መጓዛቸውን ቀጥለው ነበር፡፡ በአካባቢው የተቀሰቀሰው ግጭት ስጋት ያጫረባቸው ኤር በርሊን፣ ኮሪያን ኤርና ኤር ስፔስን የመሳሰሉ የተለያዩ አገራት አየር መንገዶች ግን፣ ወደዚህ አየር ክልል ድርሽ ማለት ካቆሙና ዙሪያ ጥምጥም መብረር ከጀመሩ ወራት አልፏቸዋል፡፡ “መሰል ግጭቶች ያሉባቸው አካባቢዎች ለአየር መንገዶችና ለአጠቃላዩ የአለማችን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ስጋት ሆነዋል፡፡

እኛም ስጋት ስለገባን በተቻለን መጠን ከአካባቢዎቹ ስንርቅ ቆይተናል፡፡ ከግጭት አካባቢዎች ለመሸሽ የበረራ መስመሮችን መቀየር፣ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጉ አይቀሬ ነው። አየር መንገዳችን ግን፣ ለደህንነት ሲል ተጨማሪ ወጪ ሲያወጣ ነው የቆየው” ብለዋል የኤዥያና አየር መንገድ ቃል አቀባይ፡፡ የማሌዢያ ትራንስፖርት ሚኒስትር ሊሎ ቲዮንግ የአገራቸው አውሮፕላን ከሰሞኑ አደጋ ላይ መውደቁን ተከትሎ ከተለያዩ አካላት ለምን በአደገኛ አየር ክልል ውስጥ በረረ በሚል የተሰነዘረበትን ትችት አልተቀበሉትም፡፡ “ይህን የአየር ክልል እያቋረጥን መጓዝ ከጀመርን አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ምንም የገጠመን ችግር አልነበረም፡፡ ደህንነቱ የተረጋገጠ ክልል ነው፡፡ ሌሎች አየር መንገዶችም ይሄን ክልል እያቋረጡ መብረራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ታዲያ እኛ ለምንድን ነው የምናቆመው?” ሲሉ ጠይቀዋል ቲዮንግ፡፡ የማሌዢያው አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ኣለምን አሳዝኖ ሳያበቃ፣ ከቀናት በኋላም ሌላ አሳዛኝ ክስተት ተፈጠረ፡፡

በበረራ ቁጥር ጂ ኢ 222 በረራ ላይ እያለ ባጋጠመው አስቸጋሪ የአየር ጠባይ ሳቢያ፣ በታይዋኗ የፔንጉ ደሴት ለማረፍ በመሞከር ላይ የነበረውና ንብረትነቱ የትራንስ ኤዥያ አየር መንገድ የሆነው አውሮፕላን ታይዋን አካባቢ ተከሰከሰ፡፡ 47 ሰዎችም ለህልፈተ ህይወት ተዳረጉ፡፡ የአቪየሽን ዘርፉ መርዶ አላበቃም፡፡ ባለፈው ረቡዕ ደግሞ ሌላ አሳዛኝ የአቪየሽን ኢንዱስትሪ መርዶ ተሰማ፡፡ 116 ተሳፋሪዎችን ይዞ በበረራ ቁጥር ኤኤች 5017 ከቡርኪናፋሶ በመነሳት ወደ አልጀርስ በመጓዝ ላይ የነበረ ንብረትነቱ የኤር አልጀሪያ አየር መንገድ የሆነ አውሮፕላን በአሰቃቂ ሁኔታ ተከሰከሰ፡፡ ቀጠለናም የታይዋን አየርመንገድ አውሮፕላን ተከስክሶ ከ50 በላይ ሰዎች ለህልፈተ ህይወት ተዳረጉ፡፡ እነዚህ ሰሞንኛ አሰቃቂ አደጋዎች፣ ብዙዎች የአቪየሽን ኢንዱስትሪውን እንዲጠራጠሩት አድርጓል ይላል ዩ ኤስ ቱዴይ፡፡ አደጋዎቹ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መከሰታቸውን በጥርጣሬ ያዩት እንዳሉ የጠቆመው ጋዜጣው፣ የኢንዱስትሪው ኤክስፐርቶች ግን ነገሩ ከሁኔታዎች መገጣጠም የዘለለ ትርጉም የለውም ስለማለታቸው ዘግቧል፡፡ “የማሌዢያው ተመትቶ፣ የትራንስ ኤዢያው ደግሞ በአየር ጠባይ ሳቢያ ነው አደጋ የደረሰባቸው። የሁለቱ አደጋዎች በተቀራራቢ ጊዜ መከሰት አጠቃላዩን ኢንዱስትሪ ስጋት ላይ የሚጥልም ሆነ፣ ተሳፋሪዎች የአውሮፕላን ጉዞ አደገኛ ነው ብለው እንዲደመድሙ የሚያስችላቸው አይደለም” ብለዋል በፍራንሲስኮ አትሞስፌር ምርምር ተቋም የጉዞ ተንታኝ የሆኑት ሄነሪ ሃርቲልት፡፡

ጆን ቤቲ የተባሉት የበረራ ደህንነት ፋውንዴሽን ፕሬዚደንትም ቢሆኑ፣ የአቪየሽን ኢንዱስትሪው እንደተባለው ደህንነት የጎደለውና መንገደኞችን ስጋት ላይ የሚጥል፣ ሌላ አማራጭ እንዲወስዱ የሚያነሳሳበት ደረጃ ላይ አይደለም ባይ ናቸው፡፡ “ባለፉት አስርት አመታት የአለማቀፉ የንግድ አቪየሽን ደህንነት እጅግ የሚገርም ደረጃ ላይ ደርሷል። አልፎ አልፎ መሰል አደጋዎች ሊፈጠሩ ቢችሉም፣ ክስተቶቹ የኢንዱስትሪውን አስተማማኝነት ጥያቄ ውስጥ አያስገቡትም። አደጋዎቹ አሳዛኝ ናቸው፤ የንግድ አቪየሽንም አሁንም ድረስ መቢገርም ሁኔታ ደህንነቱ የተረጋገጠ ነው!” ብለዋል ቤቲ፡፡ አመቱ ለአየር መንገዶች የመከራ ነበር የሚሉ ተበራክተዋል፡፡ የስታር ዶት ኮሙ ዘጋቢ ቫኔሳ ሉ ግን፣ ይህ አመት የአለማችን የንግድ አቪየሽን ከቀደምት አመታት የተሻለ ከአደጋ ነጻ የነበረበት ነው፡፡ የአለማቀፉ የአቪየሽን ደህንነት ኔትዎርክ ፕሬዚደንት ጠቅሶ ዘጋቢው እንዳለው፣ በዚህ አመት የተከሰቱ አደጋዎች ቁጥር ባለፉት አስር አመታት ከተከሰቱት አደጋዎች አማካይ ቁጥር በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡ እርግጥ በአንድ አደጋ ለሞት የሚዳረጉ የአውሮፕላን ተሳፋሪዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡

በቅርቡ በተከሰከሱት ሁለቱ የማሌዢያ አውሮፕላኖች ብቻ 537 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል፡፡ ዘስታር ዶት ኮም እንደዘገበው፣ በዚህ አመት ብቻ በአለማችን 11 አሰቃቂ የአውሮፕላን አደጋዎች ተከስተዋል፡፡ የአለማቀፉን የአየር ትራንስፖርት ማህበር መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ባለፈው አመት በተከሰቱ መሰል 11 አደጋዎች የሞቱ ሰዎች ቁጥር 210 ነበር፡፡ ባለፈው አመት በአለማቀፍ ደረጃ ከ36 ሚሊዮን በላይ በረራዎች ተደርገው፣ ከ3 ቢሊዮን በላይ መንገደኞች ያለምንም አደጋ ካሰቡበት መድረሳቸቸውንም መረጃው ያስታውሳል። በመሆኑም የኢንዱስትሪው ደህንነት አደጋ ላይ ነው ብሎ ለመደምደም የሚያበቃ ምንም ነገር የለም፡፡ በቅርብ የተከሰተውን የማሌዢያው አየር መንገድ አደጋ ተከትሎ ስጋት ውስጥ የገቡት መንገደኞችና አየርመንገዶች ብቻም አይደሉም፡፡ የአውሮፕላን ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጭምርም እንጂ፡፡

ኒውዮርክ ታይምስ ከሰሞኑ እንደዘገበው፣ ለአየር መንገዶች የአደጋ ዋስትና የሚሰጡ ታላላቅ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በተደጋጋሚ በሚከሰቱ አደጋዎች ሳቢያ የሚያወጡት ወጪ እየናረ በመምጣቱ ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በጦርነት ቀጠናዎች አካባቢ ለሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖች ዋስትና የሚሰጡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፡፡ የጦርነት አደጋ ዋስትና ደንበኞቻቸው ከሆኑ አየር መንገዶች በአመት በድምሩ 65 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ የሚሰበስቡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ በአውሮፕላኖች ላይ ለተከሰቱ አደጋዎች 600 ሚሊዮን ዶላር የካሳ ክፍያ መክፈላቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ኩባንያዎቹ ምን ያህል ለከፍተኛ ወጪ እንደተዳረጉና የኪሳራ ሰለባ እየሆኑ እንደሚገኙ ገልጧል፡፡ ተደጋግመው የሚሰሙት የአውሮፕላን አደጋዎች መንገደኞችን ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል። ዘጋርዲያን ከትናንት በስቲያ ባስነበበው ጽሁፉ እንዳለው፣ ተደጋግመው የተከሰቱት የአውሮፕላን አደጋዎች አንዳንዶች ይህን የትራንስፖርት ዘርፍ በጥርጣሬና በስጋት እንዲያዩት አድርገዋቸዋል፡፡ በአውሮፕላን መጓዝ ለመሞት ፈቅዶ ትኬት መቁረጥ ነው ብለው ማሰብ የጀመሩ አልታጡም። ዘጋርዲያን ግን፣ ይህ ጅልነት ነው ይላል፡፡

የአለማቀፉን የሲቪል አቪየሽን ድርጅት መረጃ ጠቅሶ ዘጋርዲያን እንደጻፈው፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት በአለማቀፍ ደረጃ በተደረጉ በረራዎች የተከሰቱ አደጋዎች ሲሰሉ፣ ከ300 ሺህ በአንዱ ላይ ብቻ ነው አደጋ የተከሰተው፡፡ ይህም በአውሮፕላን አደጋ እሞት ይሆን የሚለው ስጋት ከንቱ መሆኑን ያሳያል ይላል ዘገባው፡፡ እንዲህ ያለ ስጋት የገባችሁ መንገደኞች፣ ከአደጋው ይልቅ ስጋቱ ይገላችኋል ያለው ዘጋርዲያን፣ ለዚህም የአሜሪካውን የመንትያ ህንጻዎች አደጋ በዋቢነት ይጠቅሳል፡፡ አደጋው በተከሰተ በቀጣዩ አመት በርካታ አሜሪካውያን አውሮፕላን ትተው መኪና ወደመጠቀም ዞሩ። የአውሮፕላን ተጠቃሚዎች ቁጥር እስከ 20 በመቶ ቀነሰ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ መኪና ተጠቃሚው በመብዛቱ መንገዶች ተጣበቡ፡፡ ረጅም ርቀት ማሽከርከር ታዲያ፣ ከአውሮፕላን የባሰ ለአደጋ የሚያጋልጥ አስጊ ነገር ወደመሆን ተሸጋገረ፡፡ በአቪየሽን መስክ ጥናት በማድረግ የሚታወቁትን ጀርመናዊ ፕሮፌሰር ገርድ ጊገንዘርን ጥናት ጠቅሶ ዘገባው እንደጠቆመው፣ በዚያው አመት በአገሪቱ በመኪና አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር በ1 ሺህ 595 ጭማሪ አሳየ፡፡ ቀስበቀስም አርም አውሮፕላን ብለው የነበሩ መንገደኞች ምርጫ በማጣት ፊታቸውን ወደ አውሮፕላን መልሰው አዞሩ፡፡

============

ባለፉት ሰባት ወራት በአለማችን የተከሰቱ የአቪየሽን አደጋዎች

ሃምሌ 24 የታይዋን አየር መንገድ አውሮፕላን ሃምሌ 23 የአልጀሪያ አየር መንገድ አውሮፕላን

ሃምሌ 23 የትራንስ ኤዥያ አየር መንገድ አውሮፕላን ሃምሌ 17 የማሌዢያ አየር መንገድ አውሮፕላን

ሃምሌ 7 የቬትናም አየር ሃይል አውሮፕላን

ሃምሌ 5 በፖላንድ የግል አየር መንገድ አውሮፕላን

ሃምሌ 2 የስካይዋርድ ኢንተርናሽናል አቪየሽን አውሮፕላን ሰኔ 14 የዩክሬን አየር ሃይል አውሮፕላን

ግንቦት 31 የማሳቹሴትስ የግል ቻርተርድ አውሮፕላን ግንቦት 17 የላኦስ አየር ሃይል አውሮፕላን ግንቦት 8 የአሊሳና ኮሎምቢያ አየር መንገድ አውሮፕላን ሚያዝያ 20 የሱሜን ኡርሂሊዩሊሜሊጃት አየር መንገድ አውሮፕላን ሚያዝያ 19 የሊኒያስ ኤሪያስ ኮመርሺያሌስ አየርመንገድ አውሮፕላን

ሚያዝያ 8 የሃጊላንድ አቪየሽን ሰርቪስስ አውሮፕላን

መጋቢት 28 የህንድ አየር ሃይል አውሮፕላን መጋቢት 22 የስካይዳይቭ ካቦልቸር አየርመንገድ አውሮፕላን

መጋቢት 18 የሄሊኮፕተርስ ኢንክ ኮሞ ቲቪ ሄሊኮፕተር

መጋቢት 8 የማሌዢያ አየርመንገድ አውሮፕላን

የካቲት 26 የማኦይ አየርመንገድ አውሮፕላን

የካቲት 21 የሊቢያ ኤር ካርጎ አውሮፕላን

የካቲት 16 የኔፓል አየር መንገድ አውሮፕላን

ጥር 20 የስኳላ ሱፐርየራ ዲ አቪየቴ ሲልቫ አውሮፕላን

ጥር 18 የትራንስ ጉያና አየር መንገድ አውሮፕላን

Read 3827 times
Administrator

Latest from Administrator