Tuesday, 29 July 2014 14:23

ዋልያዎቹ አልጄርያን በሙሉ ብቃት መግጠም አለባቸው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

           በ2015 እኤአ ሞሮኮ ወደ የምታስተናግደው 30ኛው አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በምድብ ማጣርያ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅቱን በሃዋሳ እያደረገ ነው። ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከአልጄርያ ጋር በአዲስ አበባ ስታድዬም በሚያደርገው ጨዋታ የምድብ ማጣርያውን የሚጀምረው ብሄራዊ ቡድኑ በሙሉ ብቃት እና ዝግጅት ማድረጉ ወሳኝ ነው። ከዚሁ ጨዋታ በፊት ከግብፅ አቻው ጋር የወዳጅነት ግጥሚያ ማድረጉም አቋሙን ለመፈተሽ ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል። ዋልያዎቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በበጀት መልክ ቢያንስ እስከ 50 ሚሊዮን ብር የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በዚህ ጉዳይ እየተሰራባቸው ስላሉ የስፖንሰርሺፕ ድጋፎች እና የገቢ ምንጮች በይፋ የገለፀው ነገር የለም። በፌደሬሽኑ ፅህፈት ቤት አካባቢ እየተፈጠሩ ያሉ የአሰራር ዝርክርክነቶችም የብሄራዊ ቡድኑን ዝግጅት እና የማጣርያ ተሳትፎ አጓጉል እንዳየደርጉ ስጋት አለ፡፡ በሃዋሳ የሚዘጋጁት ዋልያዎች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የምድብ ማጣርያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከማድረጉ በፊት በዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ለ31 ተጨዋቾች ጥሪ ተደርጓል ፡፡

ከቅዱስ ጊዮርጊስ 12 ፤ከኢትዮጵያ ቡና 6፤ ከደደቢት 6 ፤ እንዲሁም ከአዋሳ ከዳሽን እና መከላከያ አንድ አንድ ተጫዋቾቹ ሲመረጡ ከሀገር ውጪ ደግሞ 5 ተጠርተዋል። አሉላ ግርማ ፤ቢያድግልኝ ኤልያስ፤ ሰላሀዲን ባርጊቾ ፤አበባው ቡጣቆ ፤አንዳርጋቸው ረታ ፤ምንተስኖት አዳነ ፤ምንያህል ተሾመ ፤በሀይሉ አሰፋ ፤አዳነ ግርማ፤ ኡመድ ኡኩሪ እና ፍፁም ገብረ ማርያም ናትናኤል ዘለቀ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተመረጡት ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ጀማል ጣሰው፤ ቶክ ጀምስ፤ ጋቶች ፓኖም ፤መስኡድ መሀመድ፤ ዳዊት እስቲፋኖስና አስቻለው ግርማ ሲመለመሉ ከደደቢት ክለብ ታደለ መንገሻ ፤አክሊሉ አየነው፤ ብርሃኑ ቦጋለ፤ ስዩም ተስፋዬ፤ ታሪክ ጌትነትና ሲሳይ ባንጫ ተመርጠዋል፡፡ ግርማ በቀለ ከአዋሳ ፤ሽመልስ ተገኝተው ከመከላከና አስራት መገርሳ ከዳሽን ቢራ ሌሎች ከአገር ውስጥ ክለቦች ለብሄራዊ ቡድኑ የተጠሩ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ ክለቦች የሚጫወቱት አምስቱ ተጨዋቾች ደግሞ ጌታነህ ከበደ ከደቡብ አፍሪካው ክለብ ቢድቪስት ዊትስ፤ ሰላሀዲን ሰኢድ ከግብፁ ክለብ አል አህሊ፤ ፍቅሩ ተፈራ በደቡብ አፍሪካ ክለቦች የተጫወተ እና አሁን ክለብ የሌለው ፤ከግብፁ አል ኢትሃድ ጋር ስሙ የተያያዘው ሽመልስ በቀለ እንዲሁም አዲስ ህንፃ ከሱዳኑ ክለብ አልአህሊ ሸንዲ ናቸው፡፡

ባሬቶ ምን ይጠበቅባቸዋል የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ከወራት በፊት ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ቅጥራቸውን ሲፈፅሙ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2015 እኤአ ለሚደረገው የሞሮኮው 30ኛው አፍሪካ ዋንጫ ማሳለፋቸው ይጠበቃል ከማለታቸውም በላይ በአፍሪካ ዋንጫው ገብቶ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን ከምድብ ፉክክር ባሻገር ለግማሽ ፍፃሜ በመድረስ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚጠበቅባቸው ማሳሰባቸው አይዘነጋም፡፡ ማርያኖ ባሬቶ ለምድብ ማጣርያው ዋና ዝግጅታቸውን በጀመሩበት ሰሞን በሰጡት መግለጫ ለ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ቃል እገባለሁ፤ ግን ፈታኝ ሂደትን በብቃት ለመወጣት መዘጋጀት አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የመጀመርያዋ ተጋጣሚ አልጄርያ የዓለም ዋንጫ ጀብዷ እና ክብደቷ የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን (ዋልያዎቹ) በ2015 እኤአ ሞሮኮ ለምታስተናግደው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው የምድብ ማጣርያ በምድብ 2 ከአልጄርያና ከማሊ የተገናኘ ሲሆን የምድቡ አራተኛ ቡድን በሁለተኛ ዙር ማጣርያ ከሚገኙት ቤኒና ማላዊ አንዱ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ የምድብ ማጣርያውን የምትጀምረው በሴፕቴምበር 5 እና 6 በሜዳዋ ከአልጄርያ ጋር በምታደርገው ጨዋታ ነው፡፡

ይህ ጨዋታ ለዋልያዎቹ እና ለአዲሱ አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ መልካም አጀማመር ወሳኝ ይሆናል፡፡ በዚሁ የምድብ 2 የማጣርያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባለው ሰፊ የዝግጅት ጊዜ በአካል ብቃት እና በአቋም መፈተሻ ግጥሚያዎች የተጠናከረ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አልጄርያ በብራዚል በሚደረገው 20ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ መሆኗ የግጥሚያውን ክብደት የሚያሳይ ነው፡፡ አልጄርያ በዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ምእራፍ በመድረስ አዲስ ታሪክ ከመስራቷም በላይ በአጨዋወት ደረጃዋ ከፍተኛ ብቃት ማሳየቷ ተቀናቃኝነቷን ያጎላዋል፡፡ አልጄርያውያን ተጨዋቾች በዓለምን ዋንጫ ተሳትፏቸው ከፊፋ ያገኙትን 9 ሚሊዪን ዶላር በጋዛ ለሚኖሩ ፍልስጤማውያን በመለገሳቸውም በአረቡ አለም አድናቆት አትርፈው ዝናቸው ገንኗል፡፡ ቦስናዊው የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ቫልሂዝድ ከዓለም ዋንጫው በኋላ ስራቸውን በክብር ለቅቀው የቱርኩን ክለብ ትራብዞንስፖር ተረክበዋል፡፡ የአልጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ምትካቸውን በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የቀጠረ ሲሆን የ59 ዓመቱ ፈረንሳዊ ክርስትያን ጉርኩፍ ናቸው፡፡ አልጄርያን ለ2015፤ እና ለ2017 የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያበቁ እና በ2018 ራሽያ ለምታስተናግደው 21ኛው ዓለም ዋንጫ እንዲያሳልፉ ኮንትራት ተሰጥቷቸዋል። ዮሃን ጉርኩፍ በፈረንሳይ ክለቦች እና እግር ኳስ የ25 አመት የአሰልጣኝነት ልምድ ያካበቱ ሲሆኑ በአልጄርያ አሰልጣኝነት የመጀመርያ ወሳኝ ጨዋታቸው አዲስ አበባ ላይ ከኢትዮጵያ ቡድን የሚገናኙበት ነው፡፡ በዓለም ዋንጫው የተሳተፉት 23 የአልጄርያ ተጨዋቾች መካከል 17 ያህሉ ትውልዳቸው በፈረንሳይ ሲሆን በከግማሽ በላይ የሚሆኑት በአውሮፓ ታላቅ ሊጎች የተጫወቱበት ሰፊ ልምድ አላቸው፡፡

በጀት፤ የወዳጅነት ጨዋታ እና ዝግጅት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአስተማማኝ ሁኔታ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፉን የሚያረጋግጠው በተሟላ ዝግጅት ለግጥሚያዎቹ ትኩረት መስጠት ከተቻለ ነው፡፡ ዋልያዎቹ በሜዳቸው የሚያደርጓቸውን ሶስቱንም ጨዋታዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማሸነፍ አለባቸው፡፡ ከሜዳ ውጭ ከሚደረጉት ሶስት ጨዋታዎች ደግሞ አንድ ድል እና አንድ አቻ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በ2018 እኤአ ራሽያ ለምታስተናግደው 21ኛው ዓለም ዋንጫ ለማለፍ በተለይ በአፍሪካ ዞን ከዚያ አስቀድመው በ2015 እኤአ ላይ በሞሮኮ እንዲሁም በ2017 እኤአ ላይ በሊቢያ የሚደረጉት 30ኛው እና 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ የሚገኝ ተሳትፎ የአህጉሩን ተወካዮች ይወስናሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2015 እኤአ ለሚደረገው አፍሪካ ዋንጫ ለመብቃት እንደደረጃው ቢያንስ ከ25 እስከ 50 ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚያስፈልገው ለመገመት ተችሏል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለብሄራዊ ቡድኑ ይህን በጀት ለሟሟላት ከቴሌቭዥን ስርጭት መብት፤ ከስታድዬም ትኬት ሽያጭ፤ ከተለያዩ የስፖርት ቁሳቁሶች ሽያጭ እና ከስፖንሰርሺፕ ድጋፎች ከሚያገኛቸው ገቢዎች ባሻገር በስፖንሰርሺፕ እንቅስቃሴዎች መስራት ቢጠበቅበትም ብዙም እንቅስቃሴ እያሳየ አይደለም፡፡

ብዙዎቹ የአህጉሪቱ ብሄራዊ ቡድኖች ወደ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በማጣርያው እስከ 5 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ያደርጋሉ፡፡ እሰከ 90 ሚሊዮን ብር ማለት ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ምሳሌ እንዲሆን በጎረቤት አገር ኬንያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የታዩ ርምጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። የኬንያ ቡድን ከ10 ዓመታት መራቅ በኋላ ወደ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎው ለመመለስ በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ ነው፡፡ የዓመት በጀቱ ከ300 ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ በላይ ነው፡፡ ይህን በጀት ከእግር ኳስ ፌደሬሽን፤ ከመንግስት እና ከስፖንሰሮች በሚያሰባስበው ገቢ ይሸፍናል፡፡ ሃራምቤስታርስ የሚባለው ብሄራዊ ቡድኑ በታዋቂው የአገሪቱ የቢራ ጠማቂ ኩባንያ ኬንያ ብሪዌሪስ ሊሚትድ አብይ ስፖንሰርነት እየተደገፈ ሲሆን ፍላይ540 የተባለ የአገሪቱ አየር መንገድ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ 1 ዓመት በሙሉ የትጥቅ ድጋፍ እና የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ስፖንሰር ሊያደርገው ከስምምነት ተደርሷል፡፡ የሁለቱ ኩባንያዎች የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ ለሃራምቤ ስታርስ እስከ 50 ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ ያስገኛል፡፡

Read 3496 times