Print this page
Tuesday, 29 July 2014 14:22

የሴቶች ወሳኝ ሚና በጀርመን ስኬት ተረጋግጧል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

           ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ በስተጀርባ ሴት ትኖራለች የሚለው አመለካከት ከዓለም ዋንጫው ጋር በተያያዘ ሲያነጋግር ሰንብቷል፡፡ የታዋቂ እግር ኳስ ተጨዋቾች ሚስቶች፤ እጮኛዎችና የፍቅር ጓደኞች የእንግሊዝ ሚዲያዎች ‹‹ዋግስ› የሚል ስም አውጥተውላቸዋል፡፡ ከዝነኛ ስፖርተኞች ጋር ግንኙነት ያላቸው ሴቶች እንደማለት ነው፡፡ በዓለም ዋንጫው ሰሞን ሴቶቹ ከየብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች ጋር በነበራቸው ግንኙነት ዙርያ አሰልጣኞች ያወጧቸው አንዳንድ የስነምግባር ደንቦች አወዛግበዋል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃናት የዝናቸው መጠን፤ ቁንጅናቸው፤ ለእግር ኳስ ባላቸው ፍቅር፤ ስለውድድሩ በሚሰጧቸው አስተያየቶች እየተነፃፀሩ ደረጃ ሲሰጣቸውም ነበር፡፡ ባሎቻቸውን ፤ እጮኛዎቻቸው እና ፍቅረኛዎቻቸውን ተጨዋቾችን ለማበረታት በየስታድዬሙ ማልያዎችን በመልበስ እና ባንዲራዎችን በማውለብለብ ድጋፍ በመስጠት ታውቀዋል። እነዚህ በዓለም ዋንጫው የደመቁ ሴቶች ልዩ ልዩ ሙያዎች ያላቸው ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ሞዴሎች ናቸው። ተዋናዮች፣ ሙዚቀኞች፣ ጋዜጠኞችና የቤት እመቤቶችም ከመካከላቸው ይገኙበታል፡፡

ከጀርመን ጀርባ የነበረው ምስጥራዊ ግብረኃይል የጀርመን ብሄራዊ ቡድን 20ኛውን ዓለም ዋንጫ አሸንፎ በተሸለመበት የመዝጊያ ስነስርዓት የተጨዋቾች ሚስቶች፤ ፍቅረኛዎች፤ ጓደኞች እና ቤተሰቦች በጋራ ደስታቸውን ሲገልፁ መላው ዓለም በትዝብት የተከታተለው ነበር፡፡ በጀርመን ቡድን ዙርያ የተሰባሰቡት እነዚህ ሴቶች በዓለም ዋንጫው ተሳታፊ ቡድኖች ከታዩ ድጋፎች እንደተሳካላቸው የተለያዩ ዘገባዎች አውስተዋል፡፡ ዴይሊ ሜል ባቀረበው ዘገባ እንዳብራራው ለዓለም ዋንጫ ስኬት የቡድን አንድነት እና የላቀ ብቃት እንዲሁም የአሰልጣኞች የታክቲክ ፍልስፍና ከፍተኛ አስተዋፅኦ ቢኖራቸውም ፆታዊ ፍቅር የማይናቅ ሚና እንደነበረው የጀርመን ድል አረጋግጧል፡፡ የጀርመን ተጨዋቾች ሴቶቻቸውን ቁጥር አንድ ደጋፊዎቻን እያሉ ሲጠሯቸው ነበር፡፡ የተጨዋቾች ሚስቶች፤ ፍቅረኞች እና ቤተሰቦች የሻምፒዮናነት ሜዳልያውን በማጥለቅና ከሻምፒዮኖቹ ጋር ፎቶ በመነሳት እድለኞች ነበሩ። አንዳንዶቹ እንደውም ዋንጫዋን በመንካት እና በማቀፍ የማይገኝ ታሪክ ሰርተዋል፡፡ ከጀርመን የዓለም ዋንጫ ድል በኋላ በነበረው ፓርቲ ከፍተኛ ትኩረት አግኝተው ከነበሩ ዝነኛ ሴቶች ግንባር ቀደሟ በዋንጫው ጨዋታ ለጀርመን ድጋፍ የሰጠችው በርባዶሳዊቷ ሙዚቀኛ ሪሃና ነበረች፡፡

ሪሃና ከጀርመን ተጨዋቾች ጋር ባላት የቀረበ ግንኙት ከሻምፒዮናዎች ጋር አብራ መዝናናቷን ያወሳው ዴይሊ ሜል ጋዜጣ፤ ዓለም ዋንጫዋን በመንካት የፊፋ ስነምግባር እስከመተላለፍ መድረሷን በመጥቀስ ትችት አቅርቦባታል፡፡ ፊፋ ዓለም ዋንጫን ከመንግስታት መሪዎች ከአሸናፊ ብሄራዊ ቡድን አባላት በስተቀር ማንም እንዳይነካ የሚከለክል የስነምግባር ደንብ ነበረው፡፡ ሪሃና ግን ወደ ጀርመን ብሄራዊ ቡድን ሰርጋ በመግባት እንደፈለገች ፎቶዎች ተነስታ በሶሽያል ሚዲያ አሰራጭታለች፡፡ ሚሮስላቭ ክሎሰ፤ ሽዋንስታይገር እና ፖዶሎስኪ ዋና ምክንያቶች ነበሩ፡፡ ሜሲቲ ኦዚል ማልያውን አውልቆ ለሪሃና እንደሸለማትም ዴይሊ ሜል አትቷል፡፡ ጀርመን ዓለም ዋንጫውን ያሸነፈችበትን ግብ ያስቆጠረው ማርዮ ጎትዜ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ፍቅረኛውን አን ካተሪን ብሮሜል ፍቅሩን እየገለፀ በተደጋጋሚ ሲያመሰግናት ታይቷል፡፡ ‹‹በዚህ ታሪካዊ ድል የቤተሰቤ እና የፍቅረኛዬ አና ድጋፍ ልዩ ነበር፡፡ ሁሉም በእኔ ውጤታማነት ሙሉ እምነት ነበራቸው›› በማለት ማርዮ ጎትዜ የሴቶቹን ሚና ገልፆታል። ጎትዜ የጎሏን ያገባው መታሰቢያነት ለዚህችው የ25 ዓመት እጮኛው አድርጓታል፡፡

አና ካተሪን ብሮሜል በጀርመን የተሳካላት ሞዴል ስትሆን በፒያኖ ተጫዋችነትም እየታወቀች ነው፡፡ ዓለም ዋንጫውን ያደመቁት ሌሎች ሴቶች ጀርመንን የደገፉ ሴቶች በድል አድራጊነት ቢንበሻበሹም በዓለም ዋንጫው በርካታ ሴቶች በየሚደግፏቸው ብሄራዊ ቡድኖች ድምቀት ፈጥረዋል፡፡ የጣሊያኑ አጥቂ ማርዮ ባላቶሊ ዓለም ዋንጫው ሳይጀመር በዋዜማው ሰሞን እጮኛውን በማግኘቱ ቀዳሚውን ትኩረት መሳብ ችሎ ነበር፡፡ 100ሺ ፓውንድ በሚያወጣ ቀለበት ፋኒ ኔጉሻ ከተባለች ፍቅረኛው ጋር የተተጫጨው በብራዚል የባህር ዳርቻ ላይ ነው፡፡ ፋኒ የራሷ ስም የተፃፈበትን የጣሊያን ማልያ በመልበስ ሁሉንም የምድብ ጨዋታዎች ከሌሎች የጣሊያን ተጨዋቾች ሚስቶች እና ፍቅረኛሞች ጋር በየስታድዬሙ በመገኘት ተከታትላለች። ከሮናልዶ ጋር የፍቅር ጓደኝነት ከጀመረች 4 ዓመታት ያስቆጠረችው የ28 ዓመቷ ሩስያዊት ሱፕር ሞዴል ኤሪና ሻይክ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በተሰጣት ሽፋን በቁንጅናዋ፤ በገቢዋ ከፍተኛነት የሚወዳደራት አልነበረም፡፡ የስፔን ብሄራዊ ቡድን ተከላካይ የሆነው ጄራርድ ፒኬ ጋር በፍቅር ጓደኝነት ከተሳሰረች 11 ዓመት ያለፋት ሻኪራ ደግሞ ዓለም ዋንጫ በሙዚቃዋ የገነነችበት ሆኗል፡፡ በ2010 እኤአ ለዓለም ዋንጫ ዜማ የነበረውን ዋካ ዋካ የሰራችው ሻኪም ለእግር ኳሱ ዓለም በመቅረብ የሚፎካከራት የለም፡፡ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ የመዝጊያው ስነስርዓት ላይ ደግሞ የሙዚቃ ኮንሰርቱ ዋና ሙዚቀኛ ኮሎምቢያዊቷ ስትሆን፤ በ2006፣ በ2010 እና በ2014 እ.ኤ.አ ላይ በተከናወኑት የዓለም ዋንጫ የመዝጊያ ስነስርዓቶች ሙዚቃ በማቅረብ የመጀመርያ ሆናለች፡፡ ኮሎምቢያዊቷ በ2010 እ.ኤ.አ የሠራችው “ዋካ ዋካ” የተሰኘው የዓለም ዋንጫ መሪ ዜማ ከዓለም ዋንጫ ዘፈኖች ከፍተኛውን ሽያጭ ያገኘ ነው፡፡ ሻኪራ በመላው ዓለም የአልበሞቿን 70 ሚሊዮን ቅጂዎች በመሸጥ የተሳካላት የላቲን ሙዚቃ ንግስት ናት፡፡

የሊዮኔል ሜሲን የበኩር ልጅ ቲያጐን የወለደችው አንቶኔላ ሬኩዞ በዓለም ዋንጫው ከታዩ እናቶች ተወዳጅነት ያተረፈችው ናት፡፡ ሜሲ 27ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ከኢራን ጋር በተደረገ ጨዋታ ላይ አንድ ጎል አስቆጥሮ ሲያከብር አንቶኔላ ከልጃቸው ጋር በስታድዬም ተገኝታ ደስታዋን ገልፃለች፡፡ እስከፍጫሜው ድረስም አንድም የአርጀንቲና ጨዋታ አላመለጣትም፡፡ የዋይኔ ሩኒ የትዳር አጋር የሆነችው ኮሊን ሩኒ ሌላዋ አነጋጋሪ ሴት ናት፡፡ ኮሊን በራሷ ወጭ በዓለም ዋንጫው ሰሞን ካይ እና ክሌይ የተባሉ ሁለት ልጆቿን ይዛ ብራዚል በመገኘት ድጋፍ የሰጠች ነበረች፡፡ የ28 ዓመቷ ኮሊን ከእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ሚስቶች ወጭዋን ሸፍና ብራዚል በመጓዝ እና በአሳፋሪ ውጤት በጊዜ በመመለስ የምትጠቀስ ሆናለች፡፡ አብረዋት የ4 ዓመት ልጃቸው ካይ እና ገና 1 ዓመት የደፈነው ሌላ ወንድሙን ይዛ እንግሊዝ በመጨረሻው የዓለም ዋንጫው የምድብ ጨዋታ ከውድድር ውጭ ስትሆን ታድመዋል፡፡ ታዳጊ ሞዴል የሆነችው የኔይማር ጓደኛ ብሩና ማርኪውዚን፤ የዌስሊ ሽናይደር ሚስትና በሙያዋ ተዋናይት የሆነችው ዮላንቴ ሽናይደር ካቡ፤ እንዲሁም ታዋቂ ጋዜጠኛ የሆነችው የኤከር ካስያስ ሚስት ሱዛን ካርቦኔ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ስማቸው ከተነሱ ሴቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ሚስቶች እና ፍቅረኞች ቡድናቸው ስታድዬም ገብተው በመደገፍ ተደንቀዋል፡፡

የባካሪ ሳኛ እና የፓትሪስ ኤቭራ ሴቶች በአስጨፋሪነታቸው አልተቻሉም ነበር፡፡በኡራጋይና ጣሊያን ብሄራዊ ቡድኖች የሚገኙ ተጨዋቾች ግንኙነት ያላቸው ሴቶች ያረፉባቸው በየአቅራቢያቸው የሚገኙ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ናቸው። የሆላንዱ አሰልጣኝ ሊውስ ቫንጋል በአንዳንድ ግጥሚያዎች ዋዜማ ለተጨዋቾቻቸው ከቤተሰባቸው ጋር የሚገናኙበትን እረፍት በመፍቀድ ልዩ ውሳኔ አድርገዋል፡፡ የፍቅር ግንኙነት ይጠቅማል፤ ይጎዳል? ከዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ ስለ ሴቶቹ መዘገብ የተጀመረው ውድድሩ ከመጀመሩ ሁለት እና ሶስት ወራት ቀድሞ ነበር፡፡ ከ32 ብሄራዊ ቡድኖች መካከል አብዛኛዎቹ የተጨዋቾች ሚስቶች፤ እጮኛዎችና ጓደኞች በዓለም ዋንጫው ስለሚኖራቸው ሚና የተለያዩ መመርያዎች አውጥተዋል፡፡ አንዳንድ አሰልጣኞች ከቡድናቸው አቅራቢያ ሴቶች፤ ልጆችና ሌሎች የቤተሰብ አባላት መኖራቸው ተጨዋቾች የልምምድ ሰዓቶችን እንዳያከብሩ፤ በተለያዩ ሁኔታዎች ሃሳብ እንዲገባቸው እና ትኩረታቸውን እንዲያጡ ያደርጋል የሚሉ ምክንያቶችን በመደርደር ጥብቅ ደንቦችን ለማውጣት ተገደዋል፡፡ ተጨዋቾች ከሚስቶቻቸው፤ ከፍቅረኞች እና ከሴት ጓደኞቻቸው ጋር በየጨዋታው ዋዜማ የወሲብ ግንኙነት የሚገድቡ ደንቦች አወዛግበዋል፡፡ አንዳንድ አሰልጣኞች ተጨዋቾች ማናቸውንም የፍቅር ግንኙነት ማድረጋቸው ውጤት ያበላሻል የሚል አቋም ነበራቸው፡፡ የራሽያ፣ ቦስኒያ፣ ቺሊና ሜክሲኮ አሰልጣኞች ምሳሌ ናቸው፡፡

ሌሎች ደግሞ ተጨዋቾች በነፃነት የፈለጉትን እንዲያደርጉ ፈቅደዋል፡፡ ጀርመን፣ ስፔን፣ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ጣሊያን፣ ሆላንድ፣ ስዊዘርላንድና ኡራጋይ ናቸው፡፡ የቦስኒያ እና ሜክሲኮ አሰልጣኞች ከጨዋታ በፊት የሚፈፀም የወሲብ ግንኙነት የአካል ብቃት ያጓድላል በሚል ሲከለክሉ የትኛውም ፕሮፌሽናል ተጨዋች ያለ ወሲብ አንድ ወር ቢያሳልፍ ምንም ችግር አይፈጠርበትም በሚል መከራከርያ ነው፡፡ የብራዚል አሰልጣኝ የነበሩት ሊውስ ፍሊፕ ስኮላሬ በበኩላቸው ክልከላውን ቢደግፉም መመርያቸውን ለዘብ በማድረግ ተጨዋቾች ወሲብ ከፈፀሙ ከልክ ባለፈ ሁኔታ እንዳይሆን በማሳሰብ ነበር፡፡ የስፔን አሰልጣኝ ቪሴንቴ ዴልቦስኬ ማናቸውም ግንኙነት ግጥሚያ በሌለባቸው የእረፍት ቀናት ብቻ እንዲሆን ሲፈቅዱ የአውስትራሊያ፤ የፈረንሳይ እና የአሜሪካ አሰልጣኞች በበኩላቸው በተለያየ ደረጃ ቁጥብ ግንኙነት እንዲኖር አሳስበዋል፡፡

የናይጄርያው አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ በበኩላቸው ትዳር የመሰረቱ ተጨዋቾች ከሚስቶቻቸው እና ቤተሰባቸው ጋር ግንኙነት እንዲኖራቸው ቢፈቅዱም ከማንኛውም የሴት ጓደኛ ወይም ፍቅረኛ ለሚደረግ ግንኙነት ግን ፈቃድ አልሰጥም ብለዋል፡፡ የቺሊ አሰልጣኝ ደግሞ ተጨዋቾቻቸው ቡድናቸውን ለጥሎ ማለፍ ምእራፍ ካበቁ በኋላ ለማናቸውም ግንኙነት ነፃነት ሰጥተዋል፡፡ የሆላንዱ አሰልጣኝ ሊውስ ቫንጋል ደግሞ ቡድናቸው ያለፈው ዓለም ዋንጫ ሻምፒዮኗን ስፔን 5ለ1 ካሸነፈበት ጨዋታ በፊት ተጨዋቾቹ ባረፉበት ሆቴል ሚስቶቻቸው፤ ፍቅረኞቻቸው እና ጓደኞቻቸው የጉብኝት ሰዓት እንዲፈቀድላቸው በመወሰናቸው ተሳክቶላቸዋል፡፡ ብዙ የእግር ኳስ አሰልጣኞች ከጨዋታ በፊት ተጨዋቾች ወሲብ ማድረግ የለባቸውም የሚል አመለካከትን ይቀበሉታል፡፡ ከጨዋታ በፊት ወሲብ መፈፀም የተጨዋችን ጉልበት ያባክናል፣ ኃይል ያሳጣል እንዲሁም የስነልቦና ዝግጅትን ያቃውሳል በሚልም ያስረዳሉ፡፡ አንዳንዶች ግን የሴቶቹ በዓለም ዋንጫ አካባቢ መገኘት ተጨዋቾች በሞራል እንዲነቃቁ ያደርጋል በሚል እምነት ሰርተዋል፡፡ ስታድዬም ገብተው ድጋፍ የሚሰጡበትን እድል እንደሚፈጥር እና ዝነኛ ሴቶች ከሆኑ ደግሞ የብሄራዊ ቡድኖችን ማልያ በማስተዋወቅ፤ የሚዲያ ሽፋን በማግኘት ብዙ መልካም ገፅታዎችን በመፍጠር ያላቸው አስተዋፅኦ መናቅ እንደሌለብትም የሚያስረዱ አሉ፡፡

Read 3187 times
Administrator

Latest from Administrator