Print this page
Saturday, 19 July 2014 13:07

የክብር ዶክትሬት ዲግሪዎች ይገባሉ፤ ወደፊትም ይደጋገማሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

     በኢትዮጵያ ስፖርት የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ለመሸለም የበቁት ለአገሪቱ ከፍተኛ ዝና እና ክብር ያስገኙት አትሌቶች ናቸው፡፡ ባለፉት ዓመታት በአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ዩኒቨርስቲዎች የክብር ዶክትሬት ተሸላሚዎች የነበሩት ፈር ቀዳጆቹ አትሌቶች ኃይሌ ገ/ስላሴ እና ደራርቱ ቱሉ ናቸው። ባለፈው ሰሞን ደግሞ  ሁለት የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች ለአትሌት መሠረት ደፋርና ጥሩነሽ ዲባባ የክብር ዶክትሬት ዲግሪዎችን ሸልመዋል፡፡ ለሁሉም የክብር ዶክትሬት ዲግሪው ይገባቸዋል፡፡ ዘንድሮ ባለመሸለሙ የሚያስቆጨውና በቅርቡ መሸለሙ የማይቀረው የኢትዮጵያ ታላቅ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡
በመላው ዓለም የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሌጆችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በማህበረሰብ ተሟጋችነታቸው፤ በበጐ አድራጊነታቸው፤ በጀግንነት ተግባራቸው፤ በስፖርት፣ የሙዚቃ ለኪነጥበብ በሰሯቸው ፈር ቀዳጅ ታሪኮችና ስኬቶቻቸው ለተመረጡ ግለሰቦች የክብር ዶክትሬት ዲግሪዎችን ይሸልማሉ፡፡ በክብር ዶክትሬት ዲግሪዎች ተሸላሚነት ከሚጠቀሱ የሙያ መስኮች ደግሞ ስፖርተኞች ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ የክብር ዶክትሬት ዲግሪዎች የሚሰጡት ለከፍተኛ ስኬት እውቅና ለመስጠት እና ለማክበር ተብሎ ነው፡፡ ዩኒቨርሲዎቹ ለታላላቅ ስፖርተኞች የክብር ዶክትሬት ዲግሪዎችን በመሸለም ለስኬታቸው ዕውቅና ይሰጣሉ፡፡ ተሸላሚዎቹ የክብር ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለው ንግግር ማድረጋቸውንም ይፈልጉታል፡፡ ከስኬታማ ስፖርተኞች ጋር ስማቸው እንዲነሳ በመፈለግም የክብር ዶክትሬት ዲግሪዎችን ይሰጣሉ፡፡
የፈር ቀዳጆቹ ኃይሌ እና ደራርቱ የክብር ዲክትሬት ዲግሪዎች
ታላቁ ሯጭ ኃይሌ ገ/ስላሴ በዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከተሸለመው ልዩ “የኦሎምፒክ ኦርደር” ሽልማት ባሻገር አራት የክብር ዶክትሬት ዲግሪዎችን ሁለት ከአገር ውስጥ እንዲሁም ሁለት ከውጭ አገር ዩኒቨርስቲዎች ተቀብሏል፡፡ የመጀመሪያውን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የተቀበለው በ2005 እ.ኤ.አ ላይ ከ‹‹ናሽናል ዩኒቨርሲቲ ኦፍ አየርላንድ›› ነበር፡፡ አትሌት ኃይሌ ይህን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ለመሸለም የበቃው በስፖርቱ መስክ ካስመዘገባቸው ታላላቅ ስኬቶች ባሻገር በአገሩ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረጉና በተለይ ለትምህርት ዘርፍ በተጫወተው ሚና እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ኃይሌ ከ‹‹ናሽናል ዩኒቨርሲቲ ኦፍ አየርላንድ›› የክብር ዶክትሬት ዲግሪውን ሲቀበል ባቀረበው ንግግር ሽልማቱ ወደፊትም ብዙ ለመስራት እንደሚያነሳሳው የተናገረ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው የተገነባውን የስፖርት መሠረተ ልማት መርቆ የከፈተ የክብር እንግዳ ነበር፡፡ የኃይሌ ሁለተኛው የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሽልማት ደግሞ በ2008 እ.ኤ.አ ከ‹‹ሊድስ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲ›› የተበረከተለት ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ይህን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ለኃይሌ የሸለሙት  16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአዲስ አበባ ለተከናወነበት ወቅት በአዲስ አበባ ስታድዬም በተደረገ ስነስርዓት ነው። የሊድስ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ዳይሬክተር በወቅቱ ስለ ኃይሌ መሸለም ንግግር ሲያረጉ “ኃይሌ አትሌት ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ አምባሳደር” ነው ብለዋል፡፡ ኃይሌ ሌሎቹን ሁለት የክብር ዶክትሬት ዲግሪዎች የተሸለማቸው  በ2010 እ.ኤ.አ ላይ ከአዲስ አበባና ከጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች 2 የክብር ዶክትሬት ዲግሪዎች መቀበል የቻለችው ደራርቱ ቱሉ ናቸው፡፡ አንድ ከአገር ውስጥ እንዲሁም ሌላ ከውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች የተቀበለቻቸው ናቸው፡፡  አትሌት ደራርቱ ቱሉ ከ4 ዓመት በፊት የመጀመሪያ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የተሸለመችው በጅማ ዩኒቨርሲቲ ነበር። በ2012 እ.ኤ.አ ላይ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካው “ዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ” ተሸልማለች፡፡ የዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ ለአትሌት ደራርቱ ቱሉ የክብር ዶክትሬቱን የሰጠው በአፍሪካ ሴቶች የኦሎምፒክ ተሳትፎ በወርቅ ሜዳልያ ስኬት ፈር ቀዳጅ ታሪክ ለመስራቷ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል፡፡
መሲና ጥሩ የዘንድሮ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሸላሚዎች
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ድንቅ ታሪክ በመስራት ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ዝና ያገኙት ሁለት አትሌቶች የክብር ዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። አትሌት መሠረት ደፋርና አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ናቸው። የመጀመሪያዋ ተሸላሚ አትሌት መሠረት ደፋር የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የተቀበለችው ከጐንደር ዩኒቨርሲቲ ነው። መሰረት ለዚህ ሽልማት የበቃችው በአትሌቲክስ ስፖርት የላቀ ውጤት በማስመዝገቧ ነው ተብሏል፡፡ ለመሠረት ደፋር ይሄው የክብር ሽልማት የመጀመሪያ ልጇን በወለደችበት ወር ውስጥ ነው፡፡ የ30 ዓመቷ አትሌት መሠረት ደፋር በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች 11 ወርቅ፣ 7 የብር እና 4 የነሐስ ሜዳልያዎች ሰብስባለች፡፡ ከሳምንት በፊት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ  ለ28 ዓመቷ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ሸልሟታል፡፡ በ63ኛው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምረቃ ስነስርዓት ላይ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ለክብር ዶክትሬት  የበቃችው በአትሌቲክስ ስፖርት በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቧ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ከፍተኛው ስኬት ያስመዘገበችው ሴት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ  ናት፡፡ በሩጫ ዘመኗ በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ውድድሮች 15 የወርቅ፣ 5 የብርና 2 ነሐስ ሜዳልያዎች የሰበሰበች ሲሆን የ5ሺ ሜትር የዓለም ሪኮርድ ከያዘች 8 ዓመት ሆኗታል፡፡
እነማን መሸለም ይገባቸዋል
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ከላይ የተጠቀሱት የኢትዮጵያ ምርጥ አትሌቶች ከክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሽልማት ባሻገር የአገሪቱን የክብር ኒሻን መሸለማቸው ትልቁ ክብር ነው፡፡ አትሌት ቀነኒሣ በቀለ በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበ አትሌት መሆኑ ደግሞ ለክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሸላሚነት ዋናው ዕጩ ያደርገዋል፡፡
የ32 ዓመቱ አትሌት ቀነኒሣ በቀለ በረዥም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች በ10ሺና በ5ሺ ሜትር የዓለም ሪኮርዶችን ከያዘ ከ12 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ በኦሎምፒክ 3 ወርቅ 1 የብር፤ በዓለም ሻምፒዮና 5 ወርቅና 1 ነሐስ፤ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮን 11 ወርቅ 1 የብር ሜዳልያዎች በመሰብሰብ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን የውጤት ክብረወሰን ያስመዘገበ ነው፡፡ በ2004 እና በ2005 እ.ኤ.አ በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የዓለም ኮከብ አትሌት ሆኖ አሸንፏል፡፡
በ1986 እ.ኤ.አ በሞስኮ ኦሎምፒክ ሁለት ድርብ የወርቅ ሜዳልያ ድሎችን ያስመዘገበው እና የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ እንዲቀጥል  በተምሳሌትነት የሚጠቀሰው አንጋፋው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር ሌላው የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ክብር የሚገባው ነው፡፡ ለረዥም ዘመናት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ለዋና አሰልጣኝነት የመሩት ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬም ያስፈልጋቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ፈርቀዳጅ ኦሎምፒያን የሚባለው እና በብስክሌት ስፖርት ግንባር ቀደም ታሪክ ያለው ገረመው ደንቦባም የሚጠቆም ነው፡፡ አንጋፋው አትሌት ምሩጽ ይፍጠር፤ ዋና አሰልጣኝ ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ እና ገረመው ደንቦባ ለክብር የዶክትሬት ዲግሪ ተሸላሚነት ዋና እጩ ሆነው የሚጠቆሙት በህይወት ያሉ የኢትዮጵያ የስፖርት ጀግኖች በመሆናቸው ነው፡፡  ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት በኋላ ከአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ እንድትበቃ ያስቻሉት፤ በቻን ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ እንድትሳተፍ ያደረጉት እና በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከፍተኛውን ውጤት እንድታስመዘግብ የሰሩት የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውም ለዚሁ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ክብር ቢበቁ የሚመሰገን ነው፡፡
የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሸላሚዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ
በመላው ዓለም የሚገኙ ትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎች ለዓለማችን ታላላቅ ስፖርተኞች የክብር ዶክትሬት ዲግሪዎችን በተለያዩ ጊዜያት ሸልመዋል፡፡ የዓለማችን የምንጊዜም ታላቅ የእግር ኳስ ተጨዋች የሆነው ኤድሰን አራንተስ ዶናሺሜንቶ ፔሌ ከ2 ዓመት በፊት በአውሮፓ የመጀመሪያውን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የተቀበለው ከዓለም 20 ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ከሆነው ኤደንብራ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ፔሌ ከአውሮፓ ውጭ በርካታ የክብር ዶክትሬት ዲግሪዎችን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎችም ተቀብሏል፡፡  የኤድንብራ ዩኒቨርሲቲ ለፔሌ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሸለመው በእግር ኳስ ስፖርት ካስመዘገበው ዘመን የማይሽረው ስኬት ባሻገር በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት እና በአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴዎች የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል በሚል ነው፡፡ታላቁ የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በስራ ዘመናቸው 9 የክብር ዲግሪዎችን ከመላው የብሪታኒያ ዩኒቨርስቲዎች ተቀብለዋል፡፡ ፈርጊ ያገኙት የክብር ዲግሪዎች ብዛት በኤፍ ኤካፕ እና የሻምፒንስ ሊግ ውድድሮች ከሰበሰቧቸው ዋንጫዎች ብዛት ይበልጣል፡፡ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በማንችስተር ዩናይትድ በቆዩባቸው የስራ ዘመናት 12 የፕሪሚዬር ሊግ፤ ሁለት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፤ 5 የኤፍ ኤካፕ እና 10 የሊግ ካፕ ድሎችን አስመዝግበዋል፡፡ ከፈርጊ የክብር ዲግሪዎች መካከል በ2011 እኤአ ላይ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ማንችስተር የተሰጣቸው በማንችስተር ዩናይትድ 25 አመታት ግልጋሎት እውቅና የተሰጠበት ሲሆን በወቅቱ ስለተሰጣቸው ክብር ባሰሙት ንግግር ‹‹ መደነቅ እና መመስገን ሁሌም ያስደስታል፡፡ በታታሪነት እና ጠንክሮ በመስራት ለሚገኝ ስኬት እውቅና ማግኘት ክብር ነው፡፡›› ብለው ነበር፡፡ የፈርጉሰን ሌላኛው የክብር ዲግሪ በ2012 እኤአ  በዩኒቨርስቲ ኦፍ ኡሊስተር የተሰጣቸው ሲሆን ዶክተር ኦፍ ሳይንስ በሚል የተሰጣቸው የክብር ዶክትሬት በእግር ኳስ ስፖርት ለፈፀሙት ግልጋሎት የተበረከተ ነበር፡፡
ታዋቂው ቦክሰኛ ማይክ ታይሰንም በስፖርቱ ካገኘው ስኬት ባሻገር በመጥፎ በሀገር ውስጥ በወንጀሎቹ ቢወቀስም በ1986 እ.ኤ.አ ላይ በኦሃዮ የሚገኘው ሴንትራል ስቴት ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሸልሟል፡፡

Read 3698 times