Saturday, 19 July 2014 13:02

በ20ኛው የዓለም ዋንጫ የጀርመን የበላይነት ታይቶበታል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

20ኛው ዓለም ዋንጫ የምንግዜም ምርጥ እንደነበር የተለያዩ ዘገባዎች፤ የስፖርት መሪዎች እና ባለሙያዎች ገልፀዋል፡፡ ጀርመን ለ4ኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን በመሆን አስደናቂ ስኬት ያስመዘገበችበት ነው፡፡ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ‹ፊፋ› ፕሬዝዳንት  ሴፕ ብላተር ዓለም ዋንጫው ከ10 ነጥብ 9.25 እንደተሰጠው ተናግረዋል። የነጥቡን ስሌት የሰራው የፊፋ ቴክኒካል ኮሚቴ ሲሆን ከ4 ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካ አስተናግዳ የነበረችው 19ኛው ዓለም ዋንጫ ያስመዘገበው 9 ነጥብ ነበር፡፡
በ20ኛው ዓለም ዋንጫ አዘጋጅነት ብራዚል በሜዳ ላይ ውጤት ባይቀናትም በመሰናዶዋ ግን ትርፋማ መሆኗን እየገለፀች ነው፡፡ የብራዚል መንግስት ይፋ ባደረገው መረጃ  መሰረት በዓለም ዋንጫው ሰሞን  እስከ 600ሺ የተጠበቀው የቱሪስት ብዛት 1 ሚሊዮን ማለፉንና ከ202 የተለያዩ አገራት መምጣታቸው ታውቋል፡፡ ከዓለም ዋንጫው ጋር ተያይዞ  ከ3 ሚሊዮን በላይ ብራዚላውያን በመላው የአገሪቱን ክፍሎች እንደተዘዋወሩ ተገልፆ፤ በተለያዩ የብራዚል ከተሞች በርካታ ህዝብ በሚመለከትባቸው አደባባዩች ዓለም ዋንጫው 5 ሚሊዮን ተከታታዮች እንደነበሩት ተነግሯል፡፡
64 ጨዋታዎችን በብራዚል 12 ስታድዬሞች ተገኝተው የታደሙት ብዛታቸው 3 ሚሊዮን 429 ሺ 873 ሲሆን በየጨዋታው በአማካይ 53ሺ 592 ተመልካች ስታድዬም ይገኝ ነበር፡፡
ለዚህ የስታድዬም ማራኪ ድባብ ብራዚላውያን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ ዓለም ዋንጫ በስታድዬም ገብቶ ለመከታተል ብራዚላውያን 1.5 ሚሊዮን ትኬቶችን በመግዛት አንደኛ ነበሩ፡፡ በ1994 እኤአ ላይ አሜሪካ ባዘጋጀችው 15ኛው ዓለም ዋንጫ በ24 ቡድኖች መካከል ቢደረግም የተመዘገበው 69ሺ የስታድዬም ተመልካች ክብረወሰኑ ነው፡፡ 20ኛው ዓለም ዋንጫ በስታድዬም ተመልካች ብዛት በውድድሩ ታሪክ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ሆኗል፡፡
በዓለም ዋንጫው ከመጀመርያው የምድብ ማጣርያ ጨዋታ እስከ ዋንጫው በተደረጉ 64 ግጥሚያዎች 171 ጎሎች መመዝገባቸው በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛው ሆኖ በክብረወሰን ተመዝግቧል፡፡171 ጎሎቹ የገቡት በ121 የተለያዩ ተጨዋቾች ነው፡፡ በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2.67 ጎሎች ተመዝግበዋል፡፡
በ6 ጎሎቹ የዓለም ዋንጫ ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን የጨረሰው የኮሎምቢያው ጀምስ ሮድሪጌዝ ሲሆን የወርቅ ጫማ ተሸልሟል፡፡ ቶማስ ሙለር በ5 ጎሎች የብራዚሉ ኔይማር በ4 ጎል የብር እና የነሐስ ጫማቸውን ተቀብለዋል፡፡ የወርቅ ጓንት የተሸለመው የጀርመኑ ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኑዌር ሲሆን የኮስታሪካው ኬዬሎር ናቫስ እና የአርጀንቲናው ሰርጂዮ ሮሜሮ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ አግኝተዋል፡፡ በኮከብ ተጨዋችነት ደግሞ የአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ ሲመረጥ ቶማስ ሙለር ከጀርመን እንዲሁም አርያን ሮበን ከሆላንድ የብር እና የነሐስ ኳሶችን ተሸልመዋል፡፡  የዓለም ዋንጫው ምርጥ ወጣት ተጨዋች የተባለው ደግሞ የፈረንሳዩ ፖል ፖግባ ሲሆን  ኮሎምቢያ የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማትን አሸንፋለች፡፡
ጀርመን የዓለም እግር ኳስ ተምሳሌት ሆናለች
 የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ምእራብ እና ምስራቅ ጀርመን ከተዋሃዱ የመጀመርያውን ዓለም ዋንጫ ድል ማስመዝገቡ ነው፡፡ በአጠቃላይ ለአራት ጊዜያት የዓለም ሻምፒዮን በመሆን ከጣሊያን ብሄራዊ ቡድን ጋር በከፍተኛ የዋንጫ ስብስብ የሁለተኛ ደረጃን ተጋርቷል፡፡ በሌላ በኩል የአውሮፓ ቡድን በደቡብ አሜሪካ የተዘጋጀን ዓለም ዋንጫን ሲያሸንፍ በታሪክ የመጀመርያው ሆኖ ሲመዘገብ የአውሮፓ አህጉር በዓለም ዋንጫ ያስመዘገበውን የሻምፒዮናነት ክብር ወደ 11 አሳድጎታል። የደቡብ አሜሪካ ቡድን የሻምፒዮናነት ክብር በ9 ድሎች ተወስኖ ቀርቷል፡፡
ለጀርመን 4ኛው የዓለም ዋንጫ ድል ከ24 ዓመት በኋላ የተመዘገበ ስኬት ነው፡፡ የአገሪቱ የእግር ኳስ ፌደሬሽን በዚህ ታሪካዊ ድል ከፊፋ 35 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ተበርክቶለታል።  የጀርመን ብሄራዊ ቡድን 23 ተጨዋቾች ቃል በተገባላቸው መሰረት በነፍስ ወከፍ 408ሺ ዶላር ይከፍላቸዋል። የጀርመን እግር ኳሷን እዚህ ደረጃ ለመድረስ ከ2000 እ.ኤ.አ በታዳጊ ፕሮጀክት ተስርቶበታል፡፡ በዚህ የለውጥ እንቅስቃሴ የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሽን እና በአገሪቱ ከፍተኛ የስፖርት ባለሙያዎች እና አሰልጣኞች ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ ከ20 ሺ በላይ የስፖርት መምህሮችና ባለሙያዎች በማሳተፍ የተሰራበት ተእድገት ስትራቴጂ የዓለም ሞዴል መሆን እንደሚገባው የተለያዩ ባለሙያዎች መክረዋል፡፡የጀርመን ክለቦች በታዳጊዎች ላይ የተመሰረተ መዋቅር መያዛቸውም የሊጉ ፉክክር ተመጣጣኝ እና እድገት የሚያሳይ አድርጎታል፡፡ በአውሮፓ ከሚካሄዱ አምስት ታላላቅ ሊጎች የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ባለፉት አምስት አመታት በከፍተኛ እድገት ላይ ነው፡፡ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ በስታድዬም ተመልካቾች ብዛት፣ በክለቦች ተመጣጣኝ የፉክክር ደረጃ፣ አስተማማኝ ገቢና ጤናማ የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንደተምሳሌት የሚታይ ሆኗል፡፡ ከዓለም ዋንጫው በኋላ ይፋ በሆነው ወርሃዊው የፊፋ እግር ኳስ ደረጃ ጀርመን በ1724 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ወስዳለች፡፡ ይህ የሚያመለክተው ጀርመን ለሚቀጥሉት አራት አመታት በዚሁ ደረጃ መሪነት ልትቆይ እንደምትችል ነው፡፡ አርጀንቲና በ1606 ነጥብ፤ ሆላንድ በ196 ነጥብ፤እንዲሁም ኮሎምቢያ በ1492 ነጥብ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ አግኝተዋል፡፡ በአዘጋጀችው ዓለም ዋንጫ 4ኛ የሆነችው ብራዚል በ4 ደረጃዎች በማሽቆልቆል 7ኛ ስትሆን ያለፈው ዓለም ዋንጫአሸናፊ ስፔን በ8 በ7 ደረጃዎች በመውረድ 8ኛ ሆናለች፡፡
 ከ20ኛው ዓለም ዋንጫ ድል በኋላ የጀርመን ማልያ 4 ኮከቦች የሚታተሙበት ይሆናል፡፡ ከ4 ዓመታት በኋላ ዓለም ዋንጫው ለመጀመርያ ጊዜ በምስራቃዊ የአውሮፓ ክፍል ሲካሄድ ጀርመን ካሸነፈች እንደ ብራዚል ባለ አምስት ኮከብ ማልያ ትለብሳለች ተብሎም ተገምቷል፡፡
ተሳታፊዎችን ከ32 ወደ 40 የማሳደግ ሃሳብ ፈጥሯል
20ኛው ዓለም ዋንጫ በተጋባደደ ማግስት የአውሮፓ እግር  ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ሚሸል ፕላቲኒ ከ4 ዓመት በኋላ ራሽያ በምታስተናግደው 21ኛው ዓለም ዋንጫ የተሳታፊዎችን ቁጥር ከ32 ወደ 40 ማሳደግ እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡  ተሳታፊዎችን የመጨመሩ አስፈላጊነቱ አንዳንድ አህጉራት በቂ ውክልና ባለማግኘታቸው ነው፡፡ የአፍሪካ እና የኤስያ አህጉራት በጋራ እስከ 100 ፌደሬሽኖችን ቢወክሉም በ9 አገራት የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ መያዛቸው ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ሚሸል ፕላቲኒ እንደማስረጃ ጠቅሰዋል፡፡ የአውሮፓ አህጉር ከ53 አባልዕ ፌደሬሽኖች የዓለም ዋንጫው ተሳትፎ በ13 ቡድኖች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የፊፋ ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር የአውሮፓ ቡድኖች በዓለም ዋንጫው ባሳዩት ደካማ ብቃት  ከ13 ቡድን ውክልናቸው ተቀንሶ ለተወሰኑ የአፍሪካ እና የኤስያ ቡድኖች ተጨማሪ እድል እንዲፈጠር ይደረግ የሚል ሃሳብ አስቀድመው አቅርበዋል፡፡ የፊፋ ዋና ፀሃፊ የሆኑት  ዤሮሜ ቫልካ በበኩላቸው የፕላቲኒ ምክር ሊሆን የማይችል ብለው ያጣጣሉት ሲሆን የ21ኛው ዓለም ዋንጫ አዘጋጅ አገር ተወካይ የሆኑት የራሽያ ስፖርት ሚኒስትር ቪታሊ ሙቱኮ ደግሞ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ላይ  8 ቡድኖችን ጭማሪ ማድረግ አጠያያቂ ነው ብለዋል፡፡ እኝህ የራሽያው ስፖርት ሚኒስትር የተሳታፊ ቡድኖች ብዛት ከ32 ወደ 40 ለማሳደግ መወሰን  በዝግጅታችን ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚፈጥር ይታሰብበት ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
ሚሸል  ፕላቲኒ ተሳታፊዎች ከ32 ወደ 40 ማደግ እንዳለባቸው  የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ስለሚያምን ለተግባራዊነቱ  ግፊት ማድረጋችን ይቀጥላል ብሏል፡፡ ሃሳቡ ተቀባይነት አግኝቶ በ21ኛው ዓለም ዋንጫ 40 ቡድኖች ከገቡ እያንዳንዱ ምድብ አምስት አገር ሊደለደልበት ይችላል፡፡ ሚሸል ፕላቲኒ ሃሳባቸውን ለእንግሊዙ ታይምስ ጋዜጣ ሲያብራሩ ለ8 ቡድኖች በሚጨመረው አዲስ የተሳትፎ ኮታ ላይ ከአፍሪካ 2፤ ከኤሽያ 2፤ ከሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ ሁለት ፤ ከኦሺኒያ 1 እንዲሁም ከአውሮፓ አህጉር 1 ቡድን ተጨማሪ ውክልና ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
ባየር ሙኒክና አውሮፓ በገቢ ከፍተኛ ድርሻ አግኝተዋል
በ20ኛው ዓለም ዋንጫ በስፖርት ውድድር ትልቁ ሽልማት ቀርቧል፡፡ በፊፋ የቀረበው 576 ሚሊዮን ዶላር በውድደሩ ታሪክ ሪኮርድ  ሆኖ የተመዘገበ ነው፡፡ ከምድብ ማጣርያ እስከ ዋንጫ በሚገኝ ውጤት መሰረት የገንዘብ ሽልማቱ የሚከፋፈል ሲሆን ለተሳታፊ 32 ቡድኖች ፌደሬሽኖች በቀጥታ የሚሰጥ ነው። ለዋንጫ  አሸናፊው 36.5 ሚሊዮን ዶላር፤ ለሁለተኛ ደረጃ  26.5 ሚሊዮን ዶላር፤ ለሶስተኛ ደረጃ  23.5 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለአራተኛ ደረጃ 21.5 ሚሊዮን ዶላር ተበርክቷል፡፡ ሩብ ፍፃሜ የደረሱ 4 ቡድኖች እያንዳንዳቸው 15.5 ሚሊዮን ዶላር፤ ጥሎ ማለፍ ለደረሱ 8 ቡድኖች እያንዳንዳቸው 10.5 ሚሊዮን ዶላርእንዲሁም በምድብ ማጣርያ ለተሳተፉ 16 ቡድኖች እያንዳንዳቸው 19.5 ሚሊዮን ዶላር ያገኛሉ፡፡ በሌሎች የፊፋ ክፍያዎች ተጨዋቾቻቸውን ለብሄራዊ ቡድን ላስመረጡ ክለቦች 70 ሚሊዮን ዶላር፤ ለአዘጋጇ ብራዚል የተሳካ መሰናዶ  20 ሚሊዮን ዶላር እና ለተጨዋቾች የጉዳት ካሳ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚሰጥ ይሆናል፡፡ፊፋ በዓለም ዋንጫ በየአገሩ ብሄራዊ ቡድን ለሚሰለፍ ለአንድ ተጨዋች በአንድ ቀን 2800 ዶላር ለክለቡ ከፍሏል፡፡ 14 ተጨዋቾች እስከ ዋንጫ ጨዋታ የደረሱለት የጀርመኑ ባየር ሙኒክ ክለብ ከፍተኛው ክፍያ እንደሚወስድ ተረጋግጧል፡፡ ተጨዋቾቻቸውን ለብሄራዊ ቡድን ላስመረጡ ክለቦች በፊፋ ከተዘጋጀው 70 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች 56% ድርሻ አላቸው፡፡ በዓለም ዋንጫ 290 ክለቦች በተጨዋቾቻው ሲሳተፉ 190ዎቹ የአውሮፓ ክለቦች ሲሆኑ ከዓለም ዋንጫው 736 ተጨዋቾች 563 በአውሮፓ ክለቦች የሚጫወቱ ናቸው፡፡

Read 1585 times