Saturday, 19 July 2014 12:55

የሮማ ካቶሊክ መሪ የማፍያ ቡድንን አወገዙ

Written by  አላዛር ኬ.
Rate this item
(3 votes)

    የደቡብ ጣሊያን ክልል የሆነችው ሲሲሊ ከድሮ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ዋነኛ መታወቂያዋ ታሪካዊ ቦታዎቿ አልያም በዋና ከተማዋ በናፖሊ ስም የተሰየመው በአንድ ወቅትም የእግር ኳሱ ጣኦት ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ይጫወትበት የነበረው የእግር ኳስ ክለብ ሳይሆን በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ማፍያ ነው፡፡
ጣሊያናውያን በካቶሊክ ክርስትና እምነታቸው ዋዛ ፈዛዛ አያውቁም እየተባለ ሲነገርላቸው ቆይቷል። ለሲሲሊው ማፍያ ግን ሃይማኖት እንደ አስፈላጊነቱ የሚታይ ተራ ጉዳይ ነው፡፡ በርካታ ጣሊያናዊ ቄሶች ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ቀኖና ውጪ ከሲሲሊ ማፍያ ጋር መነካካት ብቻ ሳይሆን በአባልነትም ጭምር ይንቀሳቀሳሉ እየተባሉ በሰፊው ይታማሉ፡፡ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም ይህንን ሀሜት እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ በይፋ አስተባብላም ሆነ የሲሲሊን ማፍያ አውግዛ አታውቅም፡፡
በ1993 ዓ.ም ግን ሊቀ ጳጳስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፤ የሲሲሊ ማፍያ በሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የተነሳ የእግዚአብሔር ፍርድ ከመቀበል መቸም ቢሆን እንደማያመልጥ ማስጠንቀቂያቸውን ሰጡ፡፡
ይህን የሰማው የሲሲሊ ማፍያ የሰራው ሀጢያት ይሰረይለት ዘንድ ንስሀ ለመግባትና “ይፍቱኝ አባ!” ለማለት ወደ ቫቲካን አላቀናም፡፡ ይልቁንም ታዛዥና ከተፎ አንጋቾችን ፈንጂ አስታጥቆ ወደ ሮም ከተማ ላካቸው፡፡ በሮም ከተማ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያኖችን በማጋየትም ለሊቀ ጳጳስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ማስጠንቀቂያ ምላሹን ሰጠ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አንድም የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስም ሆነ ሌላ ከፍ ያለ ደረጃና ስልጣን ያለው የቤተክርቲያኗ ቄስ የሲሲሊን ማፍያ ሲያወግዝ ድምፁ ተሰምቶ አያውቅም፡፡
ባለፈው ሳምንት ግን ከወደ ቫቲካን አንድ ፀረ -ማፍያ ድምጽ ተደምጧል፡፡ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መሪ የሆኑት አርጀንቲናዊው ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ከሲሲሊ የማፍያ ቡድኖች እጅግ አስፈሪ የሆነው የንድራንጊታ ማፍያ ቤተሰብ ዋነኛ መናኸርያ ወደሆነችው የካላብሪያ ከተማ ለስራ ጉዳይ ብቅ ብለው ነበር፡፡ በዚች ከተማ ውስጥ ከጥቂት አመታት በፊት ኒኮላ ካምፓሎንጎ የተባለ የሶስት አመት ሕፃን ከነአያቱና አንድ ሌላ ዘመዱ በንድራንጊታ ማፍያ ቤተሰብ በጥይት ተደብድበው የተገደሉበት ቦታ ላይ ሲደርሱ ቆም አሉና እንዲህ አሉ፤ “የሲሲሊ ማፍያ ከመልካም ነገር ይልቅ ክፉ መስራት የሚያረካው ቡድን ነው፡፡ ይህ የማፍያ ቡድንና ከዚህ የማፍያ ቡድን ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት የሚያደርግ ማናቸውም ሰው ሁሉ ውግዝ ከመአርዮስ!”
በርካታ ጣሊያናውያን የሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስን ግዝት የተቀበሉት በደስታ ነው፡፡ በግዝቱ በፍርሀት ተውጣ እየተንቀጠቀጠች ያለችው ግን በሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የምትመራው ራሷ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ናት፡፡ የሲሲሊ ማፍያ የሚሰጠው ተግባራዊ ምላሽ  ጠንቅቃ ስለምታውቀው ነው፡፡

Read 4166 times