Saturday, 19 July 2014 12:30

“ቱሪዝም ማለት ለእኔ ፍቅር ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

“ባለሀገሩ አስጐብኚ ድርጅት” አባት አርበኞችን ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ወስዶ ለማስጐብኘት እየተንቀሳቀሰ ነው
“ግድቡን ጠዋት ጐብኝቼ ማታ ብሞት ገነት እንደምገባ እርግጠኛ ነኝ” - አባት አርበኛ
ትክክለኛ ስሙ ተሾመ አየለ ቢሆንም ብዙዎች “ባለሀገሩ” በሚል ስያሜው የበለጠ ያውቁታል፡፡ ዘወትር በሚለብሰው ባህላዊ ልብስና በሚያጎፍረው ፀጉሩ ይታወቃል። በድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “ጥቁር ሰው” የሙዚቃ ቪዲዮ ላይ የባልቻ አባነፍሶን ገፀ-ባህሪ ወክሎ በመጫወት ብዙዎችን አስደምሟል። “ባላገሩ” የተሰኘ የአገር ውስጥ አስጐብኚ  ድርጅት ከፍቶ በመስራት ላይም ይገኛል። በቅርቡ በቶቶት ሆቴል በተዘጋጀ የባህል ልብሶች የመልበስ ውድድር ከተሸላሚዎቹ አንዱ ሆኗል - ወጣት ተሾመ አየለ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ 50 ለሚሆኑ አርበኞች የታላቁን ህዳሴ ግድብ ለማስጎብኘት ማቀዱን ተናግሯል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በቱሪዝም፣ በሥራ ተመክሮውና በህይወቱ ዙርያ አነጋግራዋለች፡፡

ባላገር ነኝ፤ ንግግር አልችልም ስትል ሰምቼ ነበር፡፡ ትውልድና እድገትህ የት ነው?
ትውልድና እድገቴ በሰሜን ሸዋ አካባቢ፣ ደብረ ብርሃን ዙሪያ፣ ወረዳ በዞ የሚባል ቀበሌ ውስጥ ነው።
እንዴት ወደ አዲስ አበባ መጣህ? የትምህርትህስ ሁኔታ ምን ይመስላል?
ትምህርቴን የተማርኩት እስከ 10ኛ ክፍል ነው። ነገር ግን አሁን በምሰራበት የቱሪዝም ሙያ ዙሪያ የተለያዩ የቱሪዝም ስልጠናዎችን ወስጃለሁ፡፡ አዲስ አበባ ከገባሁ ወደ 12 ዓመት ሆኖኛል፡፡ አዲስ አበባ መጥቼ ስራ የጀመርኩት በጣም አነስተኛ በሚባል ደሞዝ ነበር፡፡
አነስተኛ ስትል ስንት ብር ነው? ስራውስ ምን ነበር?
ደሞዙ በወር 35 ብር ሲሆን ስራው ዘበኝነት ነበር። ማታ ዘበኝነት እሰራለሁ፤ ቀን ቀን ደግሞ የጉልበት ስራ፣ ሸክም እየተሸከምኩ  መንጃ ፍቃድ ለማውጣት ገንዘብ እቆጥብ ነበር፡፡ ቁርስ በልቼ ከሆነ ምሳ ወይም እራት በመዝለል ነበር ገንዘብ የምቆጥበው፡፡ ያንን ካላደረግሁ ትልቅ ቦታ እንደማልደርስ አውቅ ነበር። ህይወት እንደጠበቅኩት ባለመሆኑ እንጂ አዲስ አበባ የመጣሁት ለመስራት ሳይሆን ለመማር ነበር፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ግን መማር አልቻልኩም፡፡
መንጃ ፍቃዱን አወጣህ?
የእግዚአብሄር ፈቃድ ተጨምሮበት እኔም ታግዬ መንጃ ፈቃዴን አወጣሁ፡፡ በቢጂአይ ኢትዮጵያ በቢራ ጫኝ እና አውራጅነት ተቀጥሬ እሰራ ነበር። በኋላ ላይ መንጃ ፈቃድ ስለነበረኝ  በሹፍርና ተቀጠርኩ፡፡ ከዚያ የሽያጭ ባለሙያ ሆንኩኝ፡፡
ለምንድነው ብዙ ሰዎች “ባላገሩ” እያሉ የሚጠሩህ?
ስራዬን በአግባቡ ስለምሰራ አለቆቼ ይወዱኝ ነበር፡፡ ታዲያ አብረውኝ የሚሰሩት ባልደረቦቼ “ይሄ ቆምጬ ባላገር እኮ እኛን አሳጣን” ይላሉ፡፡ በዚያው ባላገር እያሉ መጣራት ጀመሩ፡፡ እኔም አልከፋኝም። እውነትም ባላገር ነኝ፡፡ ባላገር ማለት አገር ያለው ማለት ነው፡፡ “ትናንትና ከእረኝነት መጥቶ ዛሬ እኛን በለጠን፤ ይሄ ባላገር ዶሮ ጠባቂ” ይሉኝ ነበር።  ባላገር ማለት ወግ ማእረግን አክብሮ የሚኖር፤ የሚታረስ ቦታ፣ የሚኖርበት ስፍራ፣ የሚከበርበት ባህልና ትውፊት ያለው ማለት ስለሆነ፣ ባላገርነቴን ተቀብዬው ኮርቼበት እኖራለሁ፡፡ በአጠቃላይ ባላገር ማለት በእርሻ አገሩን አልምቶ፣ አገሩን የሚመግብ የአገር ዋልታ ማለት ነው፡፡
እንዴት ነው ወደ ቱሪዝም ዘርፍ ልትገባ የቻልከው? “ባላገሩ አስጎብኚ” ድርጅትን እንዴትና መቼ አቋቋምክ?
ወደ ቱሪዝም ሥራ ለመግባት አጋጣሚው የተፈጠረልኝ በ1997 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት የዘመዴን መኪና የሊቢያ ኤምባሲ ተከራይቶት ሰለነበር እሱ ላይ እሰራ ነበር፡፡ በወቅቱ እኔ የማውቃቸው የእንግሊዝኛ ቃላት ቢቆጠሩ 15 አይሞሉም ነበር፡፡
እስከ 10ኛ ክፍል ተምረህ የለም እንዴ? እንዴት 15 አይሞሉም፤ ቢያንስ 150 እንኳን መሆን ነበረባቸው …
(ሳ….ቅ) ያው ትምህርት አቋርጠሽ ለረጅም ጊዜ ሌላ ስራ ስትሰሪም ይረሳል እኮ! የሆኖ ሆኖ እዚያ ስሰራ የቱር ባለቤቶች ሸራተን አገኙኝ፡፡ መኪናውንም ወደዱት፤ መከራየት ጀመሩ፡፡ ያለኝን የስራ ፍቅር፣ ትህትናዬን ያዩ የኤፍኬ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት አቶ ፍቅረሥላሴ፤ “ለቱሪዝም የሚመጥን ባህሪ ስላለህ ከዚህ ሥራ ባትወጣ ጥሩ ነው” የሚል ምክር ሰጡኝ። ከዚያም በራሳቸው ድርጅት ስልጠና ሰጥተውኝ፣ ባዶ መኪና ይዤ፣ ቱሪስቶች ተከትዬ እየሄድኩ ልምድ እንዳዳብር ካደረጉኝ በኋላ፣ ብቃቴን አረጋግጠው ከእሳቸው ጋር ለረጅም ጊዜ ሰራሁ፡፡ ከዚያም ለውጥ ስለሚያስፈልግ በሌላ ድርጅት ውስጥ ተቀጠርኩ። ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ “ባላገሩ አስጎብኚ” በሚል የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የራሴን ድርጅት ለመክፈት በቃሁ፡፡
በምን ያህል በጀት ነው ድርጅትህን የከፈትከው?
ምንም ገንዘብ አልነበረኝም!! በሶስትና አራት ድርጅቶች ተቀጥሬ የቱር ስራ ስሰራ የቆጠብኩት ገንዘብ አልነበረኝም፡፡ በነገራችን ላይ ቱሪዝም ማለት ለእኔ ፍቅር ነው፤ ህይወትሽን ሰጥተሸ ልትሰሪው የሚገባ ስራ ነው፡፡ ገጠር ውስጥ እንግዳ ሲመጣ ጎንበስ ቀና ብለሽ፣ እግር አጥበሽ፣ ቤት ያፈራውን አቅርበሽ፣ ፊትሽን በፈገግታ አድምቀሽ ነው የምትቀበይው፡፡ ይሄ ቱሪዝም የሚፈልገው ትክክለኛ ባህሪ ነው፡፡ ይህ ባህሪ ደግሞ በትምህርት ሳይሆን በአስተዳደግና ካደግሽበት ማህበረሰብ የምትወርሺው ነው፡፡ በዲግሪ በማስተርስ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ የሆነ ሆኖ ብር ያላጠራቀምኩበት ዋና ምክንያት፣ ልናስጎበኝ ስንሄድ የምወስዳቸው እንግዶች ቢታመሙ፣ አንድ ነገር ቢደርስባቸው በቅርብ ለመገኘት ስል እነሱ የሚያርፉበት ውድ ሆቴል  ስለማድርና አበሌን ለሆቴልና ለምግብ ከፍዬ ባዶ እጄን ወደ ቤቴ ስለምመለስ ነበር፡፡
ታዲያ አስጎብኚ ድርጅትን ያህል ትልቅ ተቋም በምን ካፒታል ከፈትክ?
በመጨረሻ ላይ የሰራሁበት ድርጅት አንድ መኪና ተበላሽቶብኝ ከስራ ስቀነስ፣ በባንክ ሂሳቤ የነበረኝ ገንዘብ 1842 ብር ብቻ ነበር፡፡ ይህን ብር ይዤ ነው “ባለሀገሩ አስጎብኚ” ድርጅትን የከፈትኩት፡፡ ከተቋቋመ ሁለት አመቱ ነው፤ ስራውን አውቀዋለሁ፤ ፍቅር የሆነ ስራ ነው፤ ስራውን ስትሰሪ ሆቴሎች ታውቂያለሽ፤ ብዙ ግንኙነት ትፈጥሪያለሽ፤ ስለዚህ በዱቤ መስራት ይቻላል። ብድርም ታገኚያለሽ፡፡ ለስራዬ ስኬት ባለቤቴ፣ እህቶቼና አጎቴ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገውልኛል፡፡ ገንዘብ አበድረውኛል፡፡ አዲ ብድርና ቁጠባም ወደ 300 ሺህ ብር ገደማ አበድሮኛል፡፡ አምስት ቋሚና 18 ገደማ የኮሚሽን ሰራተኞች አሉት፤ ድርጅቱ፡፡ ትኩረት ያደረግነው ሎካል ቱሪዝም (የአገር ውስጥ ጐብኚዎች) ላይ ነው፡፡ በአገራችን አገርን የመጎብኘት ባህላችን ደካማ በመሆኑ ሳዝን ኖሬያለሁ፡፡ አሁን ግን ትኩረት ያደረግነው ዜጎች ስለአገራቸው በደንብ እንዲያውቁና እንዲጎበኙ ማድረጉ ላይ ነው። ኢትዮጵያን ለነጭ ጎብኚዎች ትተን መቀመጥ የለብንም፡፡ እነሱም አጠራቅመው እንጂ ተርፏቸው አይደለም የሚጐበኙት፡፡
በአሁኑ ወቅት አንድ ሰው ሁለት ማኪያቶ የሚጠጣ ከሆነ አንድ እየጠጣ፣ የተወሰነ መንገድ በእግሩ በመሄድ የትራንስፖርት ወጪውን ቀንሶ፣ በቀን አስር ብር፣ በወር 300 ብር፣ በአመት 3600 ብር በመቆጠብ፣ በጋራ ሰብሰብ ብሎ አገርን የመጎብኘት ልምድ እንዲያዳብር ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየሰራን ነው፡፡
በሁለት አመት ውስጥ ምን ያህል የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን አስተናግዳችኋል?
ባለፈው አመት 1ሺህ ዘጠኝ መቶ ጐብኚዎችን አስተናግደናል፡፡ ዘንድሮም ተቀራራቢ ቁጥር ያላቸው የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ያስተናገድን ሲሆን አሁን የውጭ ጎብኚዎችንም ማስተናገድ ጀምረናል። ግንኙነቶችን እየፈጠርን ነው፡፡ ፍላጎት እያሳዩ ያሉ ጎብኚዎች አሉ፡፡ ሶስት ጥሩ ጥሩ የጉዞ መኪኖችም አሉን፡፡
ወደ አለባበስህ እንምጣ፡፡ 365 ቀናት የአገር ባህል ልብስ ነው የምትለብሰው፡፡ ፀጉርህን እንደ አርበኞች አጎፍረህ በማበጠርም ትታወቃለህ፡፡ መቼ ነው የጀመርከው?
ተወልጄ ያደግሁት ገጠር እንደመሆኑ፣ አዲስ አበባ እስክመጣ በባህል ልብስ ነው ያደግሁት፡፡ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ አጎቴና እህቶቼ የገዙልኝ ዘመናዊ የፈረንጅ ልብስ ከሰውነቴ ጋር ሊዋሀድ አልቻለም፡፡ ሱፍ ለብሼ አየሁት፤ አልተስማማኝም፣ ጂንስ ለበስኩኝ፤ መራመድ አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ ለእኔ የተፈጠረ አይደለም አልኩና ወደ አሳደገኝ ቁምጣዬ ተመለስኩኝ፡፡ ከተወለድኩ ጀምሮ እስካሁን በአገሬ ባህል ልብስ ነው የምዋበው፤ የፈረንጅ ልብስ ለብሼ አላውቅም፤ የመልበስ ፍላጎትም የለኝም፡፡
አርበኞችን ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ወስዶ የማስጎብኘት ሀሳብ የተጠነሰሰው እንዴት ነው?
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ብቸኛዋ ቅኝ ያልተገዛች አገር ናት፡፡ በዚህም እንኮራለን፡፡ ለዚህ ኩራታችን ዋነኛ ባለውለታዎች ደግሞ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ናቸው፡፡ ለዚህ ኩራት፣ ነፃነትና ክብር ህይወት አልፏል፤ ደም ፈስሷል፤ አጥንት ተከስክሷል፡፡ በአንድ አጋጣሚ አንድ አባት አርበኛ ያገኙኝና “አሁን 94 አመት ሆኖኛል፤ በተለያየ ጊዜ የነበሩ ትውልዶች የተለያየ ገድል ሰርተው አልፈዋል፤ ይሄኛው ትውልድ ደግሞ የዘላለም ቁጭቴ የነበረውን የአባይን ግድብ እየገነባ ነው፡፡ እኔ ግድቡን ጠዋት ጎብኝቼ ማታ ወይም
በነጋታው ብሞት ቀጥታ ገነት እንደምገባ እርግጠኛ ነኝ፤ እህ የእኔ ልጅ፤ ይህን ብታደርግ አንተንም መርቄህ አልፋለሁ” አሉኝ፡፡ ጉዳዩን ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ተመካክረንበት፡፡ ለምን በመኪና የምንችለውን ያህል ወስደን አናስጎበኛቸውም የሚል ሀሳብ ላይ ደረስን፡፡ ከዚያም ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ጋር ተነጋገርን፤ ሀሳቡ ጥሩ ነው በሚል ድጋፍ ሰጡን፡፡ መጀመሪያ በኛ ደርጅት የሚሳካ መስሎን ነበር፡፡ በትንሹና በህፃኑ ድርጅታችን የምንሰራው ከሆነ ግንጥል ይሆናል በሚል፣ ጉዳዩ አገራዊ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ ወሰንን፡፡
በመግለጫው ላይ እንደተባለው ወደ 77 ያህል ተጓዦች ይሳተፋሉ፤ በጀቱም ወደ አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ነው፡፡ በእርግጠኛነት የሚሳካ ዕቅድ ይመስልሃል?
እኛ እንዲሳካ የሚቻለውን ሁሉ እናደርጋለን። በሄሊኮፕተር ወስደን ብንመልሳቸው መልካም ነው። ይሄ እንግልትን ይቀንሳል፡፡ ምክንያቱም ትንሹ እድሜ የሚባለው 85 ዓመት ነው፡፡
ሁሉም ከዚያ በላይ እስከ 96 ዓመት እድሜ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ አባቶች ዶክተርና ነርሶች አብረዋቸው የሚጓዙ ቢሆንም እንግልቱን መቀነስ አለብን፡፡ በአንድ ቀን ግድቡን ጐብኝተው በዚያው ቀን ቢመለሱ ይሻላል፡፡ ለዚህም ሄሊኮፕተር የምንከራይበትን አሊያም በነፃ የምናገኝበትን መንገድ እየፈለግን ነው፡፡
እስካሁን ድጋፍ ለማድረግ ፈቃዳቸውን ያሳዩ ድርጅቶች አሉ?
ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለመከላከያ ሚኒስቴር ደብዳቤ ፅፈን ተስፋ ሰጪ ነገሮችን አይተናል፡፡ የትኛውም ኢትዮጵያዊ ካለው ላይ ቀንሶ በመስጠት፣ የአርበኞችን ምኞት እውን ያደርግልናል የሚል ተስፋ አለን፡፡ የአባቶች ወደ አባይ መሄድ፣ እዚያ በበረሀ ግድቡን በፅናት  የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያንን ሞራል ይገነባል፡፡ አባቶችም ምርቃት ይሰጣሉ። አባቶች ከጉብኝት በኋላ አዲስ አበባ ተመልሰው ምስክርነት ሲሰጡ ህዝቡ ለግድቡ ብር የማዋጣት ፍላጎቱ ይጨምራል፡፡ የአንዳንድ “አማርኛ ተናጋሪ ግብፃዊያንንም” አንገት ያስደፋል፡፡ እስከ መጪው መስከረም ሶስት ድረስ የጉብኝት ጉዞው በትክክል እንደሚሳካ እምነቴ ነው፡፡ እስካሁን በእጃችን የገባ ገንዘብ የለም፡፡ ግን ይሳካል፡፡
በመግለጫህ ላይ 77 ተጓዦች በጉብኝቱ እንደሚካተቱ ገልፀሃል፡፡ እነማን ናቸው?
50 አርበኞች፣ 16 የተለያዩ ሚዲያ ጋዜጠኞች፣ 6 ከአባቶች የአደራ ቃል የሚረከቡ የመንግስት ባለስልጣናት፣ አንድ ዶክተርና አንድ ነርስ፣ ሁለት አዝማሪዎች፣ ሁለት አስተባባሪዎች፣ በድምሩ 77 ተጓዦችን ያካትታል፡፡

Read 3125 times