Saturday, 19 July 2014 12:18

የጋሻው ስነ-ልቦናዊ ችግርና የቤተሰቡ ግራ መጋባት

Written by  ከወንድወስን ተሾመ የማህበራዊ ሳይንስና የስነልቦና ባለሙያ (ከአልታ ምርምር፣ሥልጠናና ካውንስሊንግ)
Rate this item
(6 votes)

ቤተሰቡ ስለ ጋሻው የተናገረው፡-
ጋሻው የ 26 ዓመት ወጣት ነው፡፡ በቅርቡ ለ 10 ዓመታት ከኖረበት ከ “እንግሊዝ “ አገር  መጥቶ “ደብረዘይት” ወላጆቹ ጋ ይገኛል። እናትና አባቱ ግራ የተጋቡበትን ነገር እንዲህ ሲሉ ለሥነ ልቡና ባለሙያው ገለጹለት፡- “ ልጃችን ብዙ ከቤት አይወጣም፣ ለስራም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ወዲያ ወዲህ ለማለት ምንም ፍላጎት የለውም፡፡ ቤተሰቡ ሳሎን ቤት ሲቀመጥ እሱ በጊዜ መኝታ ቤቱ ገብቶ ይተኛል፡፡ ለእራት ሲጠራ ለመብላት  አይፈልግም። እንዳንዴም የግድ ስንለው ምግቡን ቀመስ አድርጎ ወደ መኝታ ቤቱ ገብቶ ይተኛል፡፡ ጠዋትም አምስትና ስድስት ሰዓት ላይ በቅስቀሳ ነው የሚነሳው፡፡ በቃ መተኛት ነው፡፡ ዘመድ መጠየቅ አይፈልግም፤ ጓደኛ እንኳን የለውም፡፡ ስለ ወደፊት ኑሮውም ምንም ደንታ የለውም፡፡ የሚታየውም መልካም ነገር የለም፡፡ የሚገርምህ ተመልሶም ወደ እንግሊዝ አገር ለመሄድ አይፈልግም፡፡ እህቶቹም አልማርና አልሰራ ሲላቸው ነው ወደዚህ የላኩት፡፡ ይኸው ስድስት ወሩ ----ግራ ግብት ብሎናል፡፡”
ጋሻው እና የስነ ልቦና ባለሙያው ተገናኙ፡-
ጋሻው ከስነ ልቦና ባለሙያው ጋር ተገናኝቶ ለካውንስሊንግ ህክምና ፈቃደኛ መሆኑን ስለገለጠለት፣ የስነ ልቦና ባለሙያው በካውንስሊንግ ማዕከሉ “የቅበላ ቃለ መጠይቅ” አደረገለት፡፡ ጋሻው ፈቃደኛ ባይሆንና በቀጣይም ለሚደረገው የካውንስሊንግ አገልግሎት ተባባሪነቱን ባይገልፅ ኖሮ፣ የሥነ ልቦና ባለሙያው በወላጆቹ ፍላጎት ላይ ብቻ ተመስርቶ የሥነ ልቡና ህክምናውን ማድረግ አይችልም፡፡ እናም ጋሻውን እያዘነ ያሰናብተው ነበር። ግን ጋሻው ካውንስሊንግ በህይወቱ ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ በ ስነ ልቦና ባለሙያው የተሰጠውን ማብራሪያ ሰምቶ፣ በሂደቱ ውስጥ ለማለፍ ውስኗል-ትክክለኛ ውሳኔ!
ጋሻውን ምን ነክቶት ይሆን? ችግሩስ ምንድነው?
ከላይ ለመግቢያ ያህል የተጠቀምኩበትን መነሻ ሃሳብ በመያዝ  የጋሻውን ችግር ዝርዝሩን እንመልከት፡፡
ድብርት (Depression) ምንድነው?
ድብርት(Depression) ድብርት የተለያየ ደረጃና መጠን ቢኖረውም  በዚህ ፅሁፍ የምናየው ዋናውን ድብርት አምጪ ቀውስ (Major depressive disorder) የተባለውን ነው፡፡
ድብርትን ከመተርጎም መግለፅ ይሻላል፡፡ ድብርት የስሜትና የስነልቦና ችግር ሆኖ ድብርት ያለበት ሰው ስለወደፊት ህይወቱ የሚፈራ፣በአሉታዊ አስተሳሰቦችና እምነቶች የተሸነፈና “ የኔ ህይወት ከእንግዲህ አብቅቶለታል”(my life is over) የሚል እምነት በአብዛኛው የሚታይበት ነው፡፡
እንደ ሥነልቦና ባለሙያዎች ጥናት አንድ ሰው በተከታታይ ቢያንስ ለሁለት ሳምንታት ከደበተው ወይም በማንኛውም ተግባር(activity)ፍላጎትና ደስታ ማጣት ከተጠናወተው፣ ድብርት እንደያዘው ተረድቶ፣ ቶሎ  ወደ ስነ ልቦና ባለሙያ መሄድ ይገባዋል፡፡ በህፃናትና በታዳጊዎች ላይ ከመደበት ይልቅ ንጭንጭ ወይም ብስጭት ጎልቶ ሊታይ ይችላል፡፡
ድብርት የያዘው ሰው ሌሎች ተጨማሪ ምልክቶች ይታይበታል፡፡ እነዚህም ለውጦች የምግብ ፍላጎት መዛባት ወይም የክብደት  ለውጥ፣ የእንቅልፍ መዛባት፣ የስነ አዕምሮ ተግባር መዛባት(psychomotor changes)፣ ሃይል ማጣት፣ የዋጋቢስነት ስሜት ወይም ፀፀት፣ የማሰብ ችግር ወይም ትኩረት ማጣት ወይም ውሳኔ መስጠት ማቃት፣ ተከታታይ የሆነ ራስን የማጥፋት ሃሳብ፣ሙከራ ወይም ዕቅድ መኖር ናቸው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች በአንድ ቀን ውስጥ አብዛኛውን ጊዜና በየዕለቱ በመታየት ለሁለት ተከታታይ ሳምንታት ከዘለቁ ድብርት ውስጥ ተገብቷል ማለት ነው። ድብርት በአንዳንድ ሰዎች ላይ ማህበራዊ ግንኙነታቸውንና የሥራ ሁኔታቸውን ያደናቅፍባቸዋል፡፡ መጠኑ አነስተኛ ከሆነ ደግሞ  ችግሩ ከመከሰቱ በፊት  በቀላሉ የሚሰሩትን ሥራ በብዙ ጥረት ለመስራት ይገደዳሉ፡፡ በድብርት ውስጥ ያሉ ሰዎች ማዘንና ተስፋ መቁረጥ ጎልቶ ይጠናወታቸዋል።
ድብርት በአብዛኞቹ ላይ የምግብ ፍላጎት ማጣትና የክብደት መቀነስ ሲያመጣ፣ በአንዳንዶች ላይ ደግሞ የምግብ ፍላጎት መጨመርና ውፍረትን ያስከትላል፡፡ በልጆች ላይ ሲከሰት ደግሞ እድሜያቸው የሚመጥነውን ክብደት አለማግኘትን ያስከትላል፡፡
ድብርት በአብዛኛው እንቅልፍ ማጣትን የሚፈጥር ሲሆን አንዳንዶች ላይ ግን ከፍተኛና ያልተለመደ የእንቅልፍ ብዛትን ያመጣል ። ሌሊቱ አልበቃ ብሏቸው በቀንም ይተኛሉ፡፡ ጋሻው ከዚህኛው ወገን ይመደባል፡፡ እንቅልፍ ማጣቶች በሶስት ተከፍለው ሊታዩ ይችላሉ፡- ሌሊት እንቅልፍ ማጣት(middle insomnia) ይህ ማለት ሌሊት መንቃትና ተመልሶ መተኛት አለመቻል፣ በመጨረሻ ላይ እንቅልፍ ማጣት (terminal insomnia) ይህም በጣም ቶሎ መንቃትና ተመልሶ መተኛት አለመቻል፣ ከጅምሩ እንቅልፍ ለማግኘት መቸገር( initial insomnia) ተብለው ይመደባሉ።
ድብርት የአእምሮ ለውጦችም (psychomotor changes) ሊፈጥር ይችላል። ለምሳሌ አንድ ቦታ ቁጭ ማለት አለመቻል፣እጅን መጭመቅ፣ ቆዳን መጎተት ወይም ቆዳን፣ልብስን ወይም ሌላን ነገር ማሸት እንዲሁም ንግግር መቀነስ ወይም ድምፅን ዝቅ አድርጎ መናገር፣ ምላሽ ከመስጠት በፊት ለመናገር ጊዜ መውሰድ ሊፈጥር ይችላል።
ሃይል ማጣትና ከፍተኛ ድካምም በአብዛኛው የድብርት መገለጫዎቹ ናቸው፡፡
ጠቅለል አድርገን ስናየው ለድብርት (Major Depressive Episode) የሚከተሉት መለያ ምልክቶች እንደሚታዩ  የስነ ልቦና ምሁራን ይስማሙባቸዋል፡-
 በየዕለቱ አብዛኛውን የቀኑን ውሎ መደበት፣ ይህም ድብርት የያዘው ሰው ማዘኑንና ባዶነት እንደተሰማው በገፅታው ወይም በሌላ ሰው ግንዛቤ ለምሳሌ ሲያለቅስ በመመልከት መገንዘብ ይቻላል። በልጆችና በታዳጊዎች ላይ ብስጭት ይታያል።
በአብዛኛው ወይም በሁሉም ነገር የተጋነነ  ፍላጎት ወይም ደስታ ማጣት፡፡ ይህም አብዛኛውን የዕለት ኑሮና በአብዛኛው በየዕለቱ ሲሆን ይህም በሚገልፀው ወይም በምልከታ የሚረጋገጥ ነው።
የምግብ ፍላጎት ለሚያጣ የሚፈጠር ከፍተኛ ክብደት መቀነስ ወይም የምግብ ፍላጎቱ ለሚጨምር ከፍተኛ ክብደት መጨመር። በሁለቱም አቅጣጫ በየወሩ (ከአምስት በመቶ በላይ ለውጥ መገንዘብ። በህፃናት ዘንድ በእድሜያቸው ማግኘት የሚገባቸውን ክብደት አለማግኘት ጠቋሚ ነው።
በአብዛኛው በየዕለቱ እንቅፍ ማጣት ወይም እንቅልፍ መጨመር
በአብዛኛው በየዕለቱ የሚከሰት አዕምሯዊ ቸግር (psychomotor agitation or retardation):- በሌሎች እይታ ውስጥ የሚገባ መናወጥ
በአብዛኛው በየዕለቱ የሚገለፅ ድካምና ኃይል ማጣት
በአብዛኛው በየዕለቱ የሚሰማ የዋጋ ቢስነት ስሜት ወይም አግባብ ያልሆነ ራስን የመኮነን ስሜት(guilt)
በአብዛኛው በየዕለቱ የማሰብ አቅምን ወይም ትኩረት ማድረግን ማጣት፣መወሰን አለመቻል። ይህም ድብርት በያዘው ሰው ገለፃ ወይም በምልከታ ሊረጋገጥ ይችላል።
ተከታታይ የሆነ ራስን የማጥፋት ሃሳብ (የሞት ፍርሃትን አይመለከትም)፡፡ ይህም ራስን የማጥፋት እቅድ ሳይኖር የ ሃሳቡ በአዕምሮ ውስጥ መመላለስ ወይም ራስን የማጥፋት ሙከራ ማድረግ ወይም ራስን ለማጥፋት ዕቅድ አውጥቶ መመላለስ ሊሆን ይችላል።
ድብርት ከየት ይመጣል?
በሳይኮ አናሊቲክ ዘርፍ ያሉ ምሁራን፤ ልጆች  በለጋ እድሜ  ከፍተኛ ቅርርብ ከፈጠሩት ሰው (እናት፣አባት ወይም አሳዳጊ ሊሆን ይችላል) ድንገት መለየታቸው ከሚያመጣው ከባድ ስነ ልቦናዊ ችግር፣  በአዋቂነት ዘመናቸው ከሚወዱት ሰው መለየትና ጥቂት ፍቅር ማጣት ወይም መነፈግ  ተጋላጭ ሊያደርጋቸውና ለድብርት ሊዳርጋቸው ይችላል ብለው ትንታኔ ይሰጣሉ፡፡
“ራስን አለመርዳት ተሞክሮ” (learned helplessness) ማለትም ከዚህ በፊት የገጠመንና በድል ያልተሻገርነው እንቅፋት ሲኖር ወደፊትም አልሻገረውም የማለት አስተሳሰብና ተስፋ መቁረጥ በምክንያትነት የሚጠቀስበትም ሁኔታ አለ፡፡ አንድ ሳይኮሎጂስት( ከርት ሪቸር-Curt Ritchter ይባላል) በሁለት አይጦች ላይ አንድ ጥናት አካሄደ፡፡ አንዷን አይጥ በእጁ ያዘና ሞቅ ወዳለ  ውሃ የተሞላ ባልዲ ውስጥ ከተታት፡፡
አይጧ ለ 60 ሰዓታት ያህል ተስፋ ሳትቆርጥ  ተንፈራግጣ በመጨረሻ አቃታትና ሰመጠች፡፡ ሁለተኛዋን አይጥ ደግሞ እጁ ላይ ለረዥም ጊዜ እንድትፈራገጥ አደረገና ማምለጥ እንደማትችል ስታረጋግጥና እንቅስቃሴዋን ስታቆም፣ ወደ ባልዲው ከተታት፡፡ አይጧ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ውሃ ውስጥ ሰመጠች፡፡ የሳይኮሎጂስቱ ትንታኔ፤ የሁለተኛዋ  አይጥ በተወሰነ ደረጃ ውሃ ውስጥ ከገባች በኋላ መንፈራገጥ ነበረባት ነገር ግን የበፊቱ በእጅ ላይ በቆየችበት ተሞክሮዏ ማምለጥ እንደማትችል ተምራለች በዚህም ምክኒያት ለገጠማት ሁለተኛው እንቅፋት(challenge) ተስፋ ቆርጣለች፡፡ ከዚህ ተሞክሮ በኋላ  ሳይኮሎጂስቶች ጉዳዩን እየመረመሩት በመምጣት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ  “ ራስን አለመርዳት ተሞክሮ ሞትን፣ለውጥንና በህይወት የሚያጋጥም ጫናን ለመቋቋም ያለ ፍላጎትንና ችሎታን እንደሚያዳክም በመግለፅ የድብርት አንዱ ክፍል ለመሆን በቅቷል” ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል ቤክ (Beck) የተባለ ሳይኮሎጂስት፤ ዋናው የድብርት መገለጫ ባህሪ አሉታዊ የሆነ ግምት(expectaion) እና አስተሳሰብ መሆኑን በማብራራት፣ ይህም ድብርት የያዘው ሰው ዋና መገለጫ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ይህ ሰው ድብርትን ከአሉታዊ አስተሳሰብ ጋር ያቆራኘዋል፡፡ በዚህም መሰረት ሶስት ገፅታ ያላቸው ከአስተሳሰብ ጋር የተገናኙ አሉታዊ አስተሳሰቦች የድብርት መገለጫዎች ናቸው ይላል፡፡
የመጀመሪያው ገፅታ ስለ ራስ ያለ አሉታዊ ግምት ነው፡፡ ሁለተኛው ገፅታ፣ የራስ ተሞክሮን በአሉታዊ መልኩ ትንታኔ መስጠት ነው፡፡ ይህም ማለት የተሰሩ ስራዎችን፣የተሞከሩ ድርጊቶችና ግንኙነቶችን በአሉታዊ መልኩ ትንታኔ በመስጠት ራስን መኮነን ነው፡፡ ሶስተኛው ገፅታ፤ ስለ ወደፊት(future) አሉታዊ አስተሳሰብ ማሰብ ነው ይላል። በዚህ ምሁር አረዳድ፣ ድብርት ከላይ የተገለፁትን አስተሳሰቦች ከማምጣት አቅሙ በላይ  እነዚህ አስተሳሰቦች የሰውን ስሜት የመጫን ወይም ድብርትን የመፍጠር አቅማቸው ከፍተኛ ነው ብሎ ያምናል፡፡ በአብዛኛው የድብርት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ተገቢ አስተሳሰብ ባይሆንም በህይወታቸው ለገጠማቸው አሉታዊ ተሞክሮ ራሳቸውን ተጠያቂ በማድረግ፣ አሉታዊ ተሞክሮዎቹ ጥፋቶቻቸው እንደሆኑ አድርገው ይወስዳሉ፡፡
ሌሎች ደግሞ በአንጎል ውስጥ ያለ የኬሚካሎች መጠን መዛባት ለድብርት መነሻ ነው ብለው ይገምታሉ፡፡ ይህንንም ሲያስረዱ፤ ለ ድብርት የሚሰጡትን መድሃኒቶች ተፅእኖ በመመልከት ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ለምሳሌ ሜ ኤ ኦ አጨናጋፊ (MAO Inhibitors) የተባለው ለድብርት የሚሰጠው መድሃኒት ኖርኢፒንፍሪን (norepinephrine) የተባለውን በአንጎል ውስጥ የሚገኝ ንጥረ ነገር የማቆየት ሃይል እንዳለውና የዚህ ንጥረ ነገር  በአንጎል ውስጥ መቀነስ ከድብርት ጋር ይገናኛል የሚል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
በሌላ መልኩ ደግሞ ሌሎች ሳይኮሎጂስቶች የድብርት ጉዳይ ከሌሎች ጋር ባለ ግንኙነት ሊታይና ሊተነተን ይገባል ይላሉ፡፡ ኮይኔ(Coyne) የተባሉ ተመራማሪ፤ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋርና ከአካባቢያቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት እንደዋዛ የሚታለፍ አለመሆኑን ጠበቅ አድርገው ይናገራሉ፡፡ ከዚህም ጋር አያይዘው የድብርት ሰለባ የሆኑት ሰዎች ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚገደበው ጤናማዎቹ ሰዎች ከእነሱ ጊዜ ለማሳለፍ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ያመጣባቸው  ችግር ነው ባይ ናቸው፡፡
ጋሻውና መድሃኒቱ፡
ህክምናውን በሶስት ከፍለን ብናየው፡-
በራሱ በግለሰቡ የሚደረግ
በርታ ብሎ ትናንሽ ግቦችን በማስቀመጥ፣ በየዕለቱ አንድ ነገር ለመስራት መሞከር፡- ለምሳሌ  ብዙ ለሚተኙ የስምንት ሰዓት እንቅልፍ እንደ ግብ ማስቀመጥና ተፈፃሚ ለማድረግ መሞከር፤
ከሚወዱትና ከሚያምኑት ሰው ጋር ጊዜ ወስዶ ችግርን መግለፅና የሚፈልገውን እገዛ እንዲያደርጉለት መጠየቅ፤
ምንም እንኳን ፍላጎት ቢጠፋም ጨክኖ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ለመግባት መሞከርና ከሰዎች ጋር መቀላቀል፤ በተለይም መልካም ነገር ከሚናገሩና ተስፋ ካላቸው ሰዎች ጋር ማሳለፍ፤
አሉታዊ አስተሳሰቦችን መቋቋም -ለራስ ርህራሄን በመስጠት ራስን ተጠያቂ ማድረግንና መኮነንን ጋብ ማድረግ፤
የፍፁምነትን አስተሳሰብ መጨቆን- ብዙ ጊዜ ስህተትንና ደካማ ጎንን አለመቀበል፣ በድብርት ተጠቂዎች ዘንድ ስለሚታይ፣ ሰው ሁሉ ፍፁም እንዳልሆነ በመረዳት አስተሳሰቡን ለመጨቆን መሞከርና “ሁልጊዜ፤ በፍፁም፤ሁሉም፤” ወዘተ የሚሉ ቃላት ማስወገድ፡፡
በግል የተደረገው ጥረት መፍትሄ ካላመጣ የሚከተሉትን ሁለት አማራጮች መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡
በስነ ልቦና ባለሙያ(ካውንስለር) የሚደረግ ድጋፍ፡-
በስነልቦና ህክምና ድብርት የያዘው ሰው መድሃኒት ላለመጠቀም ነፃ የሚሆንበት ዕድል አለ፡፡ ካውንስለሩ ድብርት ከያዘው ሰው ጋር በሚያሳልፍበት ጊዜ የባህሪና የስሜት ህክምና ቴክኒኮችን በመጠቀም ከችግሩ ነፃ የሚሆንበት መንገድ ይከተላል፡፡ በሂደቱ ችግር የገጠመው ሰው የሚተገብራቸው በርካታ ተግባራት ከስነ ልቦና ባለሙያው ስለሚሰጡት  የግለሰቡ መሉ ፈቃደኝነት ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡
የሳይካትሪስት ድጋፍ፡-
የስነልቦና ባለሙያው ከጋሻው ጋር ባሳለፈው የተወሰኑ ጊዜያቶች የተረዳው ነገር ነበር፡፡ ጋሻው ከፍተኛ የሆነ ራስን የማጥፋት ሃሳብ ነበረው፡፡ በመሆኑም በስነልቦና ባለሙያው ውሳኔ ጋሻው ወደ ሳይካትሪስት ሄዶ “ማስታገሻ” መድሃኒት መውሰድ እንዳለበትና ለዘለቄታ መፍትሄው ግን በካውንስሊንግ የሚገኘውን ህክምና ጎን ለጎን ክትትል በማድረግ፣ ከድብርቱ እንዲወጣ ማሳሰብ ነበር፡፡ ጋሻውም ያደረገው ይህንኑ ነው፡፡
የስነ ልቦና ባለሙያው በስነልቦና ክትትል ብዙ ለውጥ ማምጣት የማይቻልበት ደረጃ መሆኑን ካረጋገጠ፣ የድብርት ተጠቂውን ሰው በሳይካትሪስት እንዲታይ ይልከውና መድሃኒት እንዲወስድ፣ ቀስ በቀስ ደግሞ መድሃኒቱን በመቀነስ በ ካውንስሊንግ አገልግሎት ጤናውን እንዲጎናፀፍ ያበረታታዋል፡፡
 አንዳንዴ ለመጠነኛ ድብርትና ጭንቀት ሆስፒታል ለሚሄዱ ሰዎች፣ ሳይካትሪስቶች ፈጥነው መድሃኒት ሊሰጧቸው አይገባም፡፡ ይልቁንም መደረግ ያለበት ወደ ስነ ልቦና ባለሙያ እንዲመሩና (Refer እንዲደረጉ)  የስነልቦና ህክምና ክትትል በማድረግ ጤናቸውን እንዲጎናፀፉ መጣር ነው፡፡
ውድ አንባቢያን፡- ከላይ የተጠቀሰውን ጋሻውን አታገኙትም-----የለምና!---- ለማስተማሪያ ታስቦ እዚሁ ወረቀት ላይ የተጀመረና ያለቀ ገጸባህሪ ነው፡፡
ቸር እንሰንብት
(ፀሐፊውን በተከታዩ ኢ-ሜይል፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ማግኘት ይችላል)

Read 5279 times