Saturday, 19 July 2014 12:06

ጋሽ መስፍን ሃብተማርያም በፀሃፍት አንደበት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(6 votes)

“መስፍን ቅንና
ግልፅ ሰው መሆኑን አውቃለሁ”
(ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል)
መስፍን ሀብተማርያም በሁለት በኩል አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ አንደኛው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በወግ ስነ-ፅሁፍ ዘውግና በሌላውም ዘርፍ ከ10 ዓመት በላይ አስተምሯል፡፡ መስፍን ራሱ ከሚፅፈው ውጭ የሚፅፉ የፈጠራ ሰዎችን በመፍጠር ከፍተኛ ድርሻ ነበረው፡፡ ውጭ አገር በወግ አፃፃፍ፣ በአጫጭር ልቦለድና በሌሎች ስነፅሁፎች ላይ ትምህርቱን ተከታትሎ ከመጣ በኋላ፣ የተማረውን ወደ ተማሪዎች በማስተላለፍ ብዙ ፀሐፍትን አፍርቷል፡፡ ይሄ የመጀመሪያውና ትልቁ አገራዊ አስተዋፅኦ ነው፡፡
ሁለተኛው ከዩኒቨርሲቲ ከወጣ በኋላ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ውስጥ በሰራበት ወቅት ያበረከተው አስተዋፅኦ ነው፡፡ በዚያን ወቅት ቦርዱ ያሳለፋቸውን መፅሀፍት (የቦርድ አባል ይሁን አይሁን አላስታውስም) ይህን አሟላ፣ “ይህን ቀንስ፣ ይህን አዳብር” እያለ መፅሀፍት ለአንባቢው እንዲመጥኑ ሆነው እንዲወጡ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ አርታኢ፣ ገምጋሚና ሀያሲ ሆኖ ሰርቷል፡፡ ፅሁፎቹም የአገር ሀብትና አስተማሪ ናቸው፡፡
ስብዕናውን በተመለከተ በቅርበት ባላውቀውም ግልፅና ቅን ሰው መሆኑን በተለያዩ የስራ አጋጣሚዎች በተገናኘን ጊዜ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ በመፅሀፍት ምረቃ፣ በስነ ፅሁፍ ውይይቶች እና መሰል ዝግጅቶች ላይ ተጋብዞ ሲመጣ፤ ለግማሽ ቀን፣ ለሙሉ ቀን አሊያም ለሁለት እና ሶስት ሰዓታት ስንገናኝ ቅንነቱ ጎልቶ ይታያል። የሚጠየቀውንም ጥያቄ አቅሙ እስከፈቀደ ድረስ ለመመለስ ጥረት ሲያደርግ እመለከታለሁ። በተለያዩ መፅሄቶች በርካታ ፅሁፎቹን ሳነብ በጣም ያዝናናኝ ነበር፡፡ ይህን መሰል ትልቅ ሰው ማጣት ጉዳት ነው። አንድ መፅሄት ላይ የመስፍን ፅሁፍ ካለ፣ መፅሄቱን ገዝቼ መጀመሪያ የማነበው የእሱን ጽሁፍ ነው፡፡ ለምን? ሳያስጨንቅሽ ነው ህይወትን በፅሁፍ የሚያሳይሽ፡፡ ሌላው በ1970ዎቹ ከጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህና ከነመዓዛ ብሩ ጋር የእሁድ ፕሮግራም ሬዲዮ ዝግጅት ላይ ሲካፈል በነበረበት ጊዜ፣ በጣም በጣም ተወዳጅ ነበር፡፡ መስፍንን ይህን ያህል ነው የማውቀው፡፡
“በህዝቡ ውስጥ ኖሮ ያለፈ
ሰው ነው”
(ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ)
በኢትዮጵያ ስነ-ፅሁፍ የመጀመሪያውን የወግ አፃፃፍ መንገድ ከዘረጉት ውስጥ የሚመደብ ነው። እንደሚታወቀው ደበበ ሰይፉ ለመስፍን “የቡና ቤት ስዕሎች” ላይ ግሩም የሆነ መግቢያ ፅፎለታል፡፡ የዝቅተኛውን ማህበረሰብ ህይወትም እንድናስተውል ያደረገን ጋሽ መስፍን ነው፡፡ ይህንን ስትመለከቺ ድንቅ ጸሐፊ ነው ከማለት ውጭ ምን ትያለሽ፡፡ ስብዕናውን ስትመለከቺ “Simple person” የምትይው አይነት ሰው ነው፤ ጋሽ መስፍን፡፡ የማይከብድ፣ ከቀረብሽው ሰዓት ጀምሮ እንደራስሽ አካል የምታይውና የሚገርም ሰው ነው፡፡ አቅሙ በፈቀደው መጠንም ሰዎችን ለመርዳት ሙከራዎችን ሲያደርግ ማየቴን አስታውሳለሁ፡፡ ወጣት ደራሲያንን በመፍጠር በኩል ያደረገው አስተዋፅኦ በቃላት የሚገለፅ አይደለም፡፡ እኔና ጋሽ መስፍን የዛሬ 26 ዓመት አስመራ ከተማ መሀል አራዳ ላይ ተገናኝነተን ነበር፡፡ በወቅቱ እኔ መርከበኛ ስለነበርኩኝ ዳህካክ ቀይ ባህር ላይ ነበር የምሰራው፡፡ ለአጭር ኮርስ አስመራ ወጥቼ ነው ያገኘሁት፡፡ እኔ አውቀው ስለነበር ሰላምታ ሰጥቼ ራሴን አስተዋወቅሁት፡፡ ከዚያም “ስነ-ፅሁፍ እንድታስተምረኝ እፈልጋለሁ” አልኩት፡፡ “አንተ ደግሞ ስለባህር ታስተምረኛለህ” አለኝ፡፡ እኔ ግን ደነገጥኩ፤ ምክንያቱም ደራሲ ሀያሲ ሲባል ሁሉንም የሚያውቅ ነበር የሚመስለኝ፡፡ “እንዴት እንደዚህ ትለኛለህ?” ጋሽ መስፍን?” አልኩት፡፡ “እኔ የስነ-ፅሁፍ ኤክስፐርት ነኝ አስተምርሃለሁ፤ አንተ ስለ ባህር ታውቃለህ ታስተምረኛለህ” አለኝ ደጋግሞ፡፡ ቀጠለናም “በአለም ላይ ስንት የባህር ስነ-ፍጥረታት አሉ?” ሲል ጠየቀኝ። “ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ በባህርና በውቅያኖስ የሚኖሩ ስነ ፍጥረታት አሉ” አልኩት፡፡ “ዘነበ፤ ይሄ በቁጥር ስታገኘው ቀላል ሊመስልህ ይችላል፤ ግን አንተ ስትፅፍ ምርጥ ምርጡ ላይ አተኩር” አለኝ፡፡ የዚያን ጊዜ አንጎሌ ውስጥ ያለውን ሼል እንክት አድርጎ ሰበረው፡፡ የሰው ልጅ እድሜ አጭር ነው፤ ሊያውቅ የሚችለውም ውስን ነገር ነው፤ ጎበዞቹና የተቀቡት ግን ቶሎ ቶሎ ሰርተው አልፈዋል፡፡ ለምሳሌ ሼክስፒርን ውሰጂ፤ እዚህ ምድር ላይ የቆየው 52 ዓመት ብቻ ነው፤ ስራዎቹ ግን እስካሁን አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ጋሽ መስፍን እኔን የመራኝ ወደዚህ ነው፤ ምርጥ ምርጦቹ ላይ አተኩር በማለት፡፡ ሁሌም አንድ ነገር ሳስብ ይህቺ አባባሉ የእኔ መነፅር ናት። ስለ 30 ሺህ ስነ-ፍጥረታት ባለፉት 26 ዓመታት ባነብ እንኳን አልጨርስም፤ በምርጥ ምርጡ ላይ አተኩሬ ግን “ህይወት በባህር ውስጥ” የምትል አንድ መፅሀፍ ለመፃፍ በቅቻለሁ፡፡ መፅሀፉን ያዘጋጀሁት ትንሹን የእጅሽን ጣት ከምታክለው አሳ እስከ አሳ ነባሪ ድረስ ያለውን የአሳ ዝርያ አጥንቼ ነው፡፡ በማዘግምበትና በማስብበት ጊዜ ሁሉ “ከምርጥ ምርጡ ላይ አተኩር”  የሚለው የጋሽ መስፍን ምክር አብሮኝ አለ፡፡ ጋሽ መስፍን መደበኛ ባልሆነ መልኩ አስተምሮኛል ማለት እችላለሁ፡፡ በህይወቱም ቀለል ብሎ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅሎ ነበር የሚኖረው፡፡ የደራሲ ህይወት ደግሞ ይሄ ነው፡፡
በአንድ ወቅት ጋሽ ስብሀትን “አንዲት ቮልስ ስዋገን ብትኖርህ ኖሮ መጭ ትላትና የፈለግህበት ታደርስህ ነበር” አልኩት፡፡ “ኖ! ማሽን ከህዝብ ይነጥልሀል፡፡ በህዝብ ውስጥ የምትኖር ከሆነ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና ማሽኖችን መጠቀም የለብህም” ብሎኛል፡፡ ጋሽ መስፍንም ቢሆን በህዝብ ውስጥ እየኖረ ያለፈ ሰው ነው፡፡
“የአማርኛ ወግ የተጀመረውም ፈር የያዘውም በጋሽ መስፍን ነው”
(ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ)
ጋሽ መስፍን ሃብተማርያም በኢትዮጵያ ስነ-ፅሁፍ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ሰው ነው፡፡ የአማርኛ ወግም የተጀመረው በእሱ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የተጀመረው ብቻ ሳይሆን ፈር የያዘውም በመስፍን ሃብተማርያም ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሲፅፋቸው የነበሩት ወጎች፣ በአንድ ላይ ተሰብስበው ለኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ሲሰጡ ምን ተብሎ መሰየም እንዳለበት ግራ መጋባት ፈጥሮ ነበር፡፡ ምክንያቱም ያን ጊዜ ወግ በአማርኛ ስነ-ፅሁፍ ውስጥ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ጋሽ አስፋው ዳምጤና ደበበ ሰይፉን በማስጠራት “እስኪ ምን ብለን እንሰይመው? ምከሩን” የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡ ከዚያም እነሱ ተነጋግረው “ድርሰት” ብለውት ነበር፡፡ በኋላ ግን ደበበ ሰይፉ ወግ ቢባል ይሻላል አለ፡፡ ወግ የሚባለው የስነ-ፅሁፍ ዘውግ የደረሰን በጋሽ መስፍን ነው፡፡ እሱ የሳይንሳዊ እውቀቱም አለው፤ ተሰጥኦውም አለው፡፡ ይሄንንም ከ250 በላይ ወጎችን በመፃፍ አሳይቷል፡፡ ጋሽ መስፍን ወግ መጀመር ብቻ ሳይሆን ተስፋፍቶ በወጣት ደራስያን እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ጭምር ወጎቹን በመተረክ ህብረተሰቡ ለወግ ቅርበት እንዲኖረው ማድረግ ችሏል፡፡ በእነ በዕውቀቱ ስዩም፣ በእነ በሃይሉ ገ/እግዚአብሔር፣ በእነ ኤፍሬም ስዩም.. የታየው ወግ፣ ያኔ በጋሽ መስፍን ተፅዕኖ የመጣ ነው። በእንግሊዝ እነ ፍራንሲስ ቤከን የወግ ጀማሪ የሆኑትን ያህል በአማርኛም የወግ ጀማሪው ጋሽ መስፍን ነው። እነፍራንሲስ ቤከን በአገራቸው እንደጀማሪነታቸው ያገኙትን ክብር ጋሽ መስፍንም ሊያገኝ ይገባል ባይ ነኝ፡፡ እንግዲህ በአማርኛ ስነ-ፅሁፍ ውስጥ ያለው ቅሬታ አንጋፋ ደራሲዎች ወጣቶቹን ለማቅረብ ሰፊ ሆድ የላቸውም የሚል ነው፡፡ እንደውም ደራሲ አዳም ረታ “እንደ ጠርሙስ ልሙጥ ናቸው፤ ወጣቱን ለመሸከም የሚችል ትከሻ የላቸውም” ይላል፡፡ ይህ አባባል በጣም ትክክል ነው፡፡ ጋሽ መስፍን ሃ/ማርያም፣ አስፋው ዳምጤ፣ ስብሃት ገ/እግዚያብሔርና አብደላ እዝራ ጋር ስትሄጂ ግን ትከሻ ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡
እኔ ጋሽ መስፍንን በሁለት የህይወቴ ጫፍ ሁለት ጊዜ አግኝቼዋለሁ፡፡ በመጀመሪያ ስነ-ፅሁፍ ምን ማለት እንደሆነ እንኳን በወጉ ሳይገባኝ፣ ምንም በነበርኩበት ጊዜ አግኝቼው ያናገረኝ በከፍተኛ ትህትናና ፍቅር ነው። ስለ ስነ-ፅሁፉም ቢሆን ሲያበረታታኝ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የእኔን ፅሁፎች አንብቦ ሂስ ከሰራ በኋላ ሰያገኘኝም የመጀመሪያው ዓይነት አክብሮትና ትህትና ነው ያሳየኝ። ምንም ነገር ሳትይዥና የሆነ ነገር ይዘሽ ስትቀርቢ አቀራረቡ መለያየት ነበረበት፡፡ ለማንም ቢሆን ጥሩ ወዳጅ ነበር፡፡ ጋሽ መስፍን ለወጣቶቹ እንደመሸሸጊያ ጥላ ነበር፡፡ በሥነ-ፅሁፍ ሰፊና መሸሸጊያ የሆነን ሰው ማጣት ለስነ-ፅሁፉም የራሱ የሆነ ትልቅ ጉዳት አለው፡፡ ይህ ጉዳት በተተኪዎቹ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ነው የሚታየው፡፡ ዞሮ ዞሮ የጋሽ መስፍን መልካም ባህሪ ስነ-ፅሁፉን አግዞታል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡
“በወግ ፀሀፊያን ዘንድ የመስፍን አሻራ ጎልቶ ይታያል”
(ደራሲና ጋዜጠኛ በሃይሉ ገ/እግዚአብሔር)
ስለአጠቃላይ የወግ ፅሁፍ ሲነሳ፣ በጉልህ የሚነሳው መስፍን ሃብተማርያም ነው፡፡ አሁን ወግ በሚፅፉ ፀሃፊያን ላይ የመስፍን አሻራ ጎልቶ ይታያል፡፡ ለምን ቢባል በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እያለን የተማርነው በመስፍን ሃ/ማርያም መፅሀፎች ነው፡፡ በኮሌጅ ደረጃም ስነ-ፅሁፍን ስንማር የእሱ ስራዎች ናቸው ተጠቃሾቹ፡፡ እስከዛሬ ድረስ በወግ አፃፃፍ ዘውግ ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው መስፍን ሃብተማርያም ነው፡፡ እነ “አውድአመት”፣ “የቡና ቤት ስዕሎች” የመሳሰሉት ስራዎቹ የሚዘነጉ አይደሉም፡፡
እነዚህ ስራዎች ከእሱ በኋላ ለመጡትም ሆነ አሁን ላሉት የወግ ፀሐፊዎች ፈር ቀዳጅ ናቸው። አሁን የወግ መፅሀፍ ፅፈው ለሚያሳትሙትም ሆነ በየጋዜጣው ላይ በአምደኝነት ለሚፅፉት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የመስፍን እጅ አለበት፡፡ የወግ ጸሀፊያን እየበዙ መምጣታቸው በራሱ፣ ጋሽ መስፍን በስነ-ፅሁፉ ውስጥ ያለውን ጉልህ ድርሻ የሚያሳይ ነው፡፡ እኔ በጣም ቀርቤው ባላውቅም በሌሎች ወጣት ደራሲያን በኩል ስሰማ፣ በጣም አጋዥና በተቻለው አቅም ሁሉ ገንቢ አስተያየቶችን የሚሰጥ መሆኑን ነው የምረዳው። እኔ እንደውም ሃያሲ ሲባል ጋሽ መስፍን ወጣቶችን ለማበረታታት የሚሰጣቸው አስተያየቶች ናቸው የሚታሰቡኝ፡፡ ስብዕናውን በተመለከተ የጠለቀ ቅርርብ ስለሌለን ብዙ ማለት አልችልም፡፡ ከስራዎቹ ጋር ነው የበለጠ ትውውቅ ያለኝ፡፡ ለረጅም ጊዜ በመጽሔቶች ላይ በሚፅፋቸው ፅሁፎችና ባሳተማቸው መፅሃፍቱ በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ ህልፈቱ ለስነ-ፅሁፍ በጣም ጉዳት ነው፡፡
“መስፍን አንጀት አርስ ደራሲ ነው”
(ጋዜጠኛ እሸቴ በቀለ)
እርግጥ መስፍን ሃ/ማርያም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ እኔን በቀጥታ አላስተማረኝም፡፡ እኔ ወደ ዩኒቨርሲቲ ስገባ እሱ ወጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ከጋሽ መስፍን ጋር በስነ-ፅሁፍ ስራ እንገናኝ ነበር፡፡ አንድ መስሪያ ቤትም ሰርተናል። በአጠቃላይ ግን መስፍን አንጀት አርስ ደራሲ ነው እላለሁ፡፡ ጋሽ መስፍን የሚፅፋቸውን ወጎች ስታነቢ ስዕል ከስቶ ነው የሚያመጣልሽ፡፡ “ወግ እንደዚህ ይፃፋል ወይ?” እንድትይ ያደርግሻል፡፡ እኔ ወግ ፀሀፊ ጥራ ብትይኝ አንድና አንድ መስፍን ሃብተማርያም ነው፡፡ በተለይ “የቡና ቤት ስእሎች”ን ያነበብኩ ጊዜ ወግ እንዲህም አለ ወይ ነው ያስባለኝ፡፡ ስለ አጭር ልብወለድ ስናወራ ብዙ የተፃፈ ነገር አለ፡፡ “Essay” የሚለውን ነገር በተመለከተ ግን እንዲህ ንጥር ባለ መልኩ ሊፃፍ እንደሚችል ያሳየ ብርቱ ሰው ጋሽ መስፍን ነው፡፡
ከዚያ በኋላም ብዙ ፅሁፎችን በየመፅሄቱ ፅፏል፡፡ በስብእና ደረጃም ቢሆን ጋሽ መስፍን በምንም መልኩ ሰውን የሚያስቀይም አልነበረም፡፡ ጋሽ መስፍን አጠገብሽ ከተቀመጠ አንቺ ያለብሽ መሳቅ ብቻ ነው፡፡ ድንጋይን የማሳቅ ሁሉ ኃይል ያለው ይመስለኛል፡፡ ሲያስቅሽ ደግሞ ተራ የወረደና ትንንሽ ጆክ አይደለም የሚያወራሽ፡፡ ከትምህርቱ፣ ከእውቀቱ ጋር የሚመጣጠን ቁም ነገር አዘል ቀልድ ነው የሚናገረው፡፡ ለምሳሌ አብረሽው ሆነሽ አንድን ነገር አንቺ ልብ ሳትይው፣ እሱ አይቶ እንዴት ወደ ጨዋ ቀይሮ እንደሚያስቅ ስመለከት በጣም ይደንቀኝ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከስራ በኋላ ጊዜ ሲኖር ስንሰበሰብ ወጣቱን፣ ጎልማሳውን፣ አዛውንቱን እኩል የማሳቅ፣ የማጫወትና የማዝናናት ክህሎት ነበረው፡፡ እንደው የሚያውቁትን ሁሉ በአካል አግኝተሽ ስለሱ ብትጠይቂያቸው ብዙ የምትሰሚያቸው አስገራሚ ነገሮች ይኖራሉ፡፡     

Read 6941 times