Print this page
Saturday, 19 July 2014 11:52

“ምን አደረግኋችሁ!…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ኳሱም አለቀ አይደል! የተናቁት ‘እንትን ያሉበት…’ ኳስ፡፡ እና ‘የተናቀ እንትን ማለቱ…’ በኳስ ብቻ ሳይሆን በሌላም እንዳለ ልብ ይባልልንማ!
የኳስ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው የእግር ኳስ ዳኛ ነው፡፡ እናላችሁ… በየዓመቱ የልደቱ ቀን በደረሰ ቁጥር ከተለያዩ ቡድኖች ደጋፊዎች በርካታ ‘የልደት’ ካርዶች ይደርሱታል፡፡ ታዲያላችሁ እሱ እንደሚለው፤ የሚደርሱት ካርዶች በሙሉ ሊባል በሚችልበት ሁኔታ አንድ አይነት ምኞት ነበር የሚያስተላልፉት፡፡ “የዘንድሮው የልደት በዓልህ የመጨረሻህ እንዲሆን እመኛለሁ!” አሪፍ አይደል! ልክ ነዋ…‘የሰለጠነ ምኞት’ ማለት ይሄ ነው፡፡
ይሄኔ በሆዳችን ለስንትና ስንት እነ እንትናዎች “….የመጨረሻህ እንዲሆን እመኛለሁ!” ብለን እንደምንመኝ አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ክፍት ቦታው ላይ የሚሞላው የግድ ‘ልደት’ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ ልክ ነዋ…‘ንግግርህ’፣ ‘ዲስኩርህ’፣  ‘ቃለ መጠይቅህ’  ምናምን የሚባሉ በርካታ አማራጮች እንዳሉ ልብ ይባል ብለን ነው፡፡
እግረ መንገዴን… የሆነ ታዋቂ የሆሊዉድ ሰው ነው አሉ፡፡ ታዲያ በብዙ ሰዎች ሥራ ይበሳጫል። እናማ ምን ይላል መሰላችሁ…“አንዳንድ ሰዎች በህይወት የሚቆዩት ሰው መግደል ወንጀል ስለሆነ ብቻ ነው!”
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሰውየው ንብረቱን ተሸክሞ ሲጓዝ ወንበዴዎች ይገጥሙታል፡፡ እናላችሁ…እስከ ለበሳት ድረስ ሁሉንም ነገር ወስደው መለ መላውን ያስቀሩታል። ከዛላችሁ…ትተውኝ ሄዱ ሲል ጭራሽ በዱላ ያራውጡታል፡፡ ቢቸግረው ምን አለ መሰላችሁ…“ምን አደረግኋችሁ! ንብረቴን ሁሉ ወስዳችሁ፣ አሁን የምትደበድቡኝ አርፍዶ መጣ ብላችሁ ነው!”
አሀ…ምን ያድርግ፡፡ ያለን ሁሉ ተወስዶብን ‘ቆሎ ብንደፋ’ እንኳን ዕዳ መሸፈኛ የሚሆን ‘ሰባራ ሶልዲ’ ሳይኖረንም “ምን አደረግኋችሁ!…” የሚያሰኙ ነገሮች መአት ናቸው፡፡ እኔ የምለው…ሁሌ የምለውን ልድገመውና “ምነው እንዲህ ተከፋፋን!” የምር እኮ ‘የዱር እንትኖች’ እነ አንበሳና አያ ጀቦ መሆናቸው ቀርቶ እኛ ራሳችን የሆንን ሊመስል ምንም አይቀረው፡፡
“በቃ ወድቋል…” ብሎ ትቶ መሄድ የለም። እንደማይነሳም ቢታወቅም እንደገና ‘መሬት እንድትውጠው’ አይነት ይፈለጋል፡፡ ስሙኝማ…በትዳር አካባቢ በተፈጠሩ አለመግባባቶች አንደኛው ወገን ሌላኛውን ለመበቀል የሚሄድበትን ርቀት ስትሰሙ ግርም ይላችኋል፡፡ እናላችሁ፣ ንብረቱን ምኑን ምናምኑን “የእኔ ድርሻ…” “የአንቺ ድርሻ…” ምናምን ተባብለው ከተከፋፈሉ በኋላ የመጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል ይቀጥላል፡፡
“እኔን ፈንግላ እሷ ከሌላ ሰው ጋር በሰላም ልትኖር! ሞቻታለኋ!”
“ምን አለች በሉኝ፣ የተወለደበትን ቀን ባላስረግመው!”
ስሙኝማ…የትዳር ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…አንዱ ግራ የገባው ያለውን ስሙኝማ…“ምርጡ ትዳር ማለት የአዳምና የሔዋን ነው፡፡ ምክንያቱም አዳምም ‘ሌሎች ባሎች ለሚስቶቻቻው እንዴት እንደሚንሰፈሰፉላቸው ባየህ፡፡ እኔ እዚህ ዘላለሜን…!’ አይነት ንዝንዝ የለበትም፡፡ እሷም ‘እማዬ እንዴት አይነት ባለሙያ እንደሆነች ባየሻት፡፡ አሁን እንቁላል እንዲህ ነው የሚጠበሰው!...’ አይነት ጭቅጭቅ የለባትም፡፡”
ስሙኝማ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እውቅ ተዋናይት ናት አሉ፡፡ እናማ…አንድ ግብዣ ላይ የሆነ ይከጅላት የነበረ ሰውን ከብዙ ጊዜ በኋላ ታገኘዋለች፡፡ ታዲያላችሁ ሰውየው አጠገቧ እንደደረሰ አንዳንድ ምክንያታዊ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ‘አካላዊ ለውጦች’ ይታያሉ፡፡ ይሄኔ እሷ ‘ፎቶ ገጭ’ አይነት አስተያየት ታየውና ምን ብትለው ጥሩ ነው… “ኪስህ ውስጥ ሽጉጥ ይዘሀል ወይስ እኔን በማየትህ ደስ ብሎህ ነው…፡፡” እንዴት ሸጋ አባባል ነች!
የምር ግን እኔም እኮ እንትናዬዎች በርከት በሚሉበት አካባቢ…አለ አይደል… “ወንዱ ሁሉ ይሄን ለአተር ማስጫ የሚበቃ  ሞባይል በኪሱ ይዞ የሚዞረው ለምንድነው?” እል ነበር፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ኑሮን ወደኋላ መለስ ብሎ ላየው አለ ብዙ ነገር ካሁን የሚለየው፣ ድሮማ ቢመለስ እየገሰገሰ ትዝታዉ ተሸሮ ፍቅሩ በነገሰ፡፡
የምትል አሪፍ ስንኝ አለች፡፡ እናማ…የትናንቱ መልካም ነገሮች ሁሉ ትዝታ መሆናቸው ቀርቶ እውን ቢሆኑ የምንል ቁጥራችን እየጨመረ ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሰዎች አለን የሚሏትን ‘ትዝታ’ መለስ ብለው ቢያዩ የሚገርም አይደለም፡፡ ሰዎች የአሁኑ ራስና ጭራው አልያዝ ሲላቸው፣ የወደፊቱ ድቅድቅ ጨለማ ሲሆንባቸው… አለ አይደል… ‘ቀዌ’ ከመሆን የሚያድናቸው ከትናንት የተራረፈችው መልካም ትዝታ ነች፡፡ ለተወሰነ ደቂቃ “የሰው ክብር የሚታወቅበት፣ አንድ ዳቦ ለአራት ተካፍሎ የሚበላበት፣ ሰው ሲያደናቅፈው “ይድፋህ፣ ሸፋፋ!” ሳይሆን “እኔን ድፍት ያድርገኝ!” ይባልበት የነበረ ዘመን እንደነበረ ማስታወሱ…
ድሮማ ቢመለስ እየገሰገሰ ትዝታዉ ተሽሮ ፍቅሩ በነገሰ ቢያሰኝ አይገርምም፡፡
እናማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…“ምን አደረግኋችሁ!…” የሚያሰኙ ነገሮች በዝተዋል። በየመሥሪያ ቤቱ ጥርስ የነከሰ አለቃ ምስኪኑን ከሥራ ማስወገድ ወይም ደሞዙን መቆንደድ ብቻ ሳይሆን ሌላም ቦታ ሠርቶ እንዳይበላ ሊያደርገው ነው የሚፈልገው፡፡ የሚጻፍለት ደብዳቤ አንድ ተቀጥሮ ለበርካታ ዓመታት የሠራ ሰው ሳይሆን… አለ አይደል… ጠፍቶ አርጀንቲና ውስጥ ተደብቆ የኖረ የሂትለር የኦሽዊዝ ዘብ ሊያስመስለው ምንም አይቀረው፡
እኔ የምለው…የሆነ ‘ቦስ’ ሰውየውን በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ከሥራ ካስወጣው በኋላ ሌላ ቦታ ሠርቶ የቤተሰቡን ሆድ እንዳያሸንፍ ማድረግ ምን አይነት ጭካኔ ነው! (እግረ መንገዴን…ይሄን አይነት “አይደለም ተዝናንቶ ምሳ እራት ሊበላ፣ ቆሎ እንዳማረው ድብን ይበላት!” አይነት “ምን አደረግኋችሁ!…” የሚያሰኙ ነገሮች ‘ቦተሊከኞቻችን’ አካባቢ በሽ ነው ይባላል፡፡)
በኪነጥበቡ አካባቢም እንዲህ አይነት ነገሮች ይታያሉ የሚል ወሬ ቢጤ ነገር አለ፡፡ አለ አይደል… የዓይኑ ቀለም ያልተወደደለት፣ ወይም በፈራንካም ሆነ በውሽሜ ‘ጥርስ የገባ’ ምስኪን ጨርቁን ጥሎ እስኪሄድ መከራውን ያያል ይባላል፡፡ በነገራችን ላይ ማበጠሪያ መዋዋስ፣ አንዱ በነካው ብርጭቆ ሌላው መጠጣት ምናምን አይነት ነገሮች እዛ አካባቢ ‘የተለመዱ’ አይደሉም ይባላል፡፡ “ምን አደረግኋችሁ!…” የሚያስብሉ ነገሮች ያስከትላሉ የሚባል ፍርሀት አለ አሉ፡፡
ታዲያ አንቺ ኢትዮዽያ፣ እኛስ ልጆችሽ ምንድነን
አመንኩሽ ማለት የማንችል፣ ፍቅራችን የሚያስነውረን
ዕዳችን የሚያስፎክረን
ግፋችን የሚያስከብረን
ቅንነት የሚያሳፍረን፣ ቂማችን የሚያስደስተን
ኧረ ምንድነን?  ምንድነን?
ብሏል፤ ሎሬት ጸጋዬ በ1957 ዓ.ም.፡፡
እናላችሁ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላም እነኚህ ቃላት ሀያው ናቸው፡፡ ልክ ነዋ…አሁንም በዕዳችን የምንፎክር ነን፡ ከአገር እስከ ግለሰብ ባለዕዳ መሆንን አንገት የሚያስደፋ ሳይሆን የሚያስፎክር ነው፡፡
ግፋችን የሚያስከብረን ሆነናል፡፡ ዘንድሮ የሚከበረው ባለ እውቀቱ ሳይሆን ባለጡንቻው ሆኗል፡፡ በጡንቻ የሚታስብበት ዘመን ውስጥ ነን፡፡ ግፍም የጡንቻ የመጨረሻ ውጤት ነው፡፡ የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማንልበት፣ ዓለም የአዋቂዎች ሳይሆን የጉልበተኞች የሆነችበት ዘመን ነው፡፡ እንዲህ ሲሆንም ጊዜ ሚሊዮኖች “ምን አደረግኋችሁ!…” ይላሉ፡፡ ሰሚ የለም እንጂ!
ቅንታችን የሚያሳፍረን ሆነናል፡፡ ቅንነት የሞኝነት መለያ ሆኗል፡፡ ቅንነት ከጊዜ ጋር አብሮ መሄድ አለመቻል ሆኗል፡፡ ቅንነት የጨዋታውን ህግ አለማወቅ ሆኗል፡፡ እንዲህ ሲሆንም ሚሊዮኖች “ምን አደረግኋችሁ!…” ይላሉ፡፡
በቂማችን የምንደሰት ነን፡፡ “የት አባቱ፣ ልክ አገባሁት!” “እኔ ላይ እንዳልዘነጥችብኝ አሁን ብታያት አይደለም ገዥ፣ ሻጭ እንኳን የተጠየፋት ዶሮ አስመስያታለሁ!” አይነት ነገሮች በየዕለት ንግግሮቻችን ውስጥ እየበዙ የሄዱበት ዘመን ነው፡፡ እንዲህ ሲሆንም ሚሊዮኖች “ምን አደረግኋችሁ!…” ይላሉ፡፡ ሰሚ የለም እንጂ!
እናማ…ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የተጠየቀውን ጥያቄ ደግመን እንጠይቃለን፡፡
ኸረ ምንድነን?  ምንድነን?
“ምን አደረግኋችሁ!…” ከሚያስብሉ ነገሮች ይሰውረንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2167 times