Saturday, 19 July 2014 11:30

ትናንት በአንዋር መስጊድ ተቃውሞና ግርግር ተፈጠረ

Written by 
Rate this item
(61 votes)

“የታሰሩት የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ይፈቱ” የሚል ተቃውሞ ትናንት ከቀትር በኋላ በተካሄደበት የታላቁ አንዋር መስጊድ አካባቢ በርካታ ፖሊሶች ተሰማርተው የዋሉ  ሲሆን፤ ለሰዓታት በዘለቀው ግርግርና ረብሻ የተኩስ ድምጽ የተሰማ ቢሆንም የደረሰው ጉዳት እስካሁን በዝርዝር አልታወቀም፡፡ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች በፖሊስ ተይዘው ሲወሰዱ ታይቷል፡፡
ተቃውሞና ግርግር የተፈጠረው የጁምዓ ስግደት ከመጠናቀቁ በፊት እንደሆነ የተናገሩ የአይን እማኞች፤ ቆመጥ የያዙ ፖሊሶች ተሰማርተው እንደነበርና በርካቶች ድብደባ እንደደረሰባቸው ገልፀዋል፡፡
በተክለሃይማኖት አደባባይ እና ከፒያሳ ወደ መርካቶ የሚወስዱ መንገዶች ለእግረኞችና ለተሽከርካሪ ተዘግተው የነበረ ሲሆን፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለእግረኞች መከፈቱን የተናገሩ የአካባቢው ሰዎች፤ ግርግሩ ግን ወዲያው አልቆመም ብለዋል፡፡
“የታሰሩት የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ይፈቱ” ከሚለው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ “ድምፃችን ይሰማ” በተሰኘው ድረገፅ የተቃውሞ ጥሪ ሲተላለፍ እንደሰነበተ ምንጮች ገልፀዋል። አምናም በተመሳሳይ የረመዳን የጾም ወቅት፣ በሦስት የአዲስ አበባ መስጊዶች ሦስት ሰፋፊ ተቃውሞዎች መካሄዳቸው ይታወሳል፡፡

Read 12307 times