Saturday, 19 July 2014 11:18

ኢትዮጵያዊው ገበሬ የእንግሊዝን መንግስት ከሰሱ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

       በጋምቤላ ክልል ለሰፈራ ፕሮግራም ከቀያቸው ከተፈናቀሉት በርካታ ሺህ ዜጐች አንዱ እንደሆኑና ወደ ኬንያ እንደተሰደዱ የገለፁ ገበሬ፤ የእንግሊዝ መንግስት ለሰፈራ ፕሮግራሙ የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት በደል ፈጽሞብኛል በማለት ሰሞኑን በለንደን ፍ/ቤት ክስ መሰረቱ፡፡  ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የገንዘብ እርዳታ በመስጠት በአለም ቀዳሚ ስፍራ የያዘው የእንግሊዝ መንግስት በበኩሉ፤ ለሰፈራ ፕሮግራም የሚውል ገንዘብ አልሰጠሁም በማለት ምላሽ መስጠቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከአስር አመት ወዲህ በየክልሉ የሰፈራ ዘመቻዎች መካሄዳቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት “ከፊል አርብቶ አደር” ተብለው በሚታወቁ እንደ ጋምቤላና ሶማሌ በመሳሰሉ ክልሎች፤ ነዋሪዎችን በመንደር የማሰባሰብና የማስፈር ፕሮግራሞች ተካሂደዋል፡፡ በርካታ ነዋሪዎች ያለፈቃዳቸው በግዳጅ እየተፈናቀሉ ለችግር ተዳርገዋል የሚል ተደጋጋሚ ትችት የሚሰነዘርባቸው እነዚህ የሰፈራ ፕሮግራሞች ላይ ሂዩማን ራይትስ ዎች የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም እና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የተለያዩ የምርመራ ሪፖርቶች አቅርበዋል፡፡
የማህበረሰብ ልማት ፕሮግራም በሚል ስያሜ የዛሬ ሦስት ዓመት በጋምቤላ በተካሄደ የሰፈራ ፕሮግራም ከመኖሪያ መሬታቸው እንደተፈናቀሉ የገለፁት ገበሬው፤ ከመኖሪያዬ ልፈናቀል አይገባም በማለት ይዞታዬን ለመከላከል ስለጣርኩ አስከፊ ስቃይና እንግልት ደርሶብኛል ሲሉ ለለንደን ፍ/ቤት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ የአራት ልጆች አባት እንደሆኑ የገለፁት እኚሁ ገበሬ፤ ቤተሰቦቼን ችግር ላይ ጥዬ ወደ ኬንያ ለመሰደድና በመጠለያ ጣቢያ ለመኖር  ተገድጃለሁ ብለዋል፡፡ የእንግሊዝ መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለተፈፀመበት የሰፈራ ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ በመስጠቱ ተጠያቂ  መሆን ይኖርበታል፤ ላደረሰብኝ በደልም ካሳ መክፈል አለበት ሲሉ ፍ/ቤቱን ጠይቀዋል - ኢትዮጵያዊው ገበሬ፡፡ የእንግሊዝ መንግስት ባለፉት አራት አመታት ከ1.3 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ (አሁን ባለው የምንዛሬ መጠን ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ) እርዳታ መስጠቱ የሚታወቅ ሲሆን፤ ዘንድሮም አለማቀፍ የልማት ድርጅት በተሰኘው መስሪያ ቤት አማካኝነት 10 ቢሊዮን ብር ገደማ እርዳታ እንደሚሰጥ ከሳምንት በፊት ገልጿል፡፡
እርዳታው ለሌላ ጉዳይ ሳይሆን፤ የጤና፣ የትምህርት፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ለመሳሰሉት የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ስራዎች የሚውል እንደሆነ የተናገሩት የእንግሊዝ መንግስት አለማቀፍ ልማት ድርጅት ቃል አቀባይ፤ ለሰፈራ ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ አልሰጠንም ብለዋል፡፡
ከሰፈራ ፕሮግራሙ ጋር የእንግሊዝ መንግስት ግንኙነት እንደሌለው በመግለጽም፤ በኢትዮጵያዊው ገበሬ የቀረበው ክስ ውድቅ ሊደረግ ይገባል ብለዋል - የእንግሊዝ መንግስት ባለስልጣናት፡፡ የለንደኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት ግን የቀረበለትን ክስ ውድቅ አላደረገም፡፡ ከሳሹ ገበሬ፣ “የእንግሊዝ መንግስት ለሰፈራ ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል” ብለው የማመን መብት እንዳላቸው ፍ/ቤቱ ገልፆ፤ የክሱ ፍሬ ነገር በአግባቡ መመርመር አለበት በማለት ክሱን ለማየት ወስኗል፡፡  የሰፈራ ፕሮግራሙ ድህነትን ለመቀነስ ታስቦ በኢትዮጵያ መንግስት ተግባራዊ መደረጉን የገለጸው ቢቢሲ፤ ሂዩማን ራይትስ ዎች ከሁለት አመታት በፊት ባወጣው ሪፖርት፣ በጋምቤላ ክልል 70 ሺህ ያህል ዜጎች ያለፈቃዳቸው ከይዞታቸው ተነስተው በቂ ምግብ፣ የእርሻ ቦታና የመሰረተ ልማት አውታር ወደሌሉባቸው መንደሮች ተዛውረዋል ማለቱን አስታውሷል፡፡
የከሳሹ ገበሬ ስም ያልተጠቀሰው “የቤተሰቦቼ ደህንነት ያሰጋኛል” በማለታቸው እንደሆነ የገለፀው ዴይሊ ሜይል በበኩሉ፣ ገበሬው በጠበቆች አማካኝነት ክስ ለማቅረብና ለመከራከር በአስር ሺዎች ፓውንድ የሚገመት ገንዘብ እንደሚያስፈልጋቸውና ወጪው የሚሸፈነው በእንግሊዝ መንግስት እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ አገራት በየአመቱ በሚመደበው እርዳታ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚባክንና ሸክሙ በእንግሊዛዊያን ግብር ከፋዮች ትከሻ ላይ እንደሚያርፍ በመዘገብ የሚታወቀው ዴይሊ ሜይል፤ ኬንያ ውስጥ የሚኖር የሌላ አገር ዜጋ ክስ የሚመሰርተውና ካሳ የሚከፈለው በእንግሊዝ ግብር ከፋይ ዜጐች ኪሳራ ነው የሚል ተቃውሞ እንደተፈጠረ ገልጿል፡፡ ክስ አቅራቢው ገበሬ በበኩላቸው፤ በፍ/ቤቱ ውሳኔ ካሳ ከተከፈላቸው ገንዘቡን ለበጐ አድራጐት እንደሚያውሉት ተናግረዋል፡፡

Read 5047 times