Saturday, 12 July 2014 12:49

3 የጀርመንና 2 የአርጀንቲና የዓለም ዋንጫ ድሎች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    ጀርመንና አርጀንቲና በዓለም ዋንጫ 5 የሻምፕዮናነት ክብሮች  አግኝተዋል፡፡ ነገ በዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ የሚገናኙት በታሪክ ለሶስተኛ ጊዜ ይሆናል፡፡  በሁለቱ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች በ1986 እኤአ ላይ አርንጀቲና ስታሽንፍ በ1990 እኤአ ደግሞ ጀርመን አሸንፋለች፡፡ ከ20ኛው የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ፍልሚያ በፊት የአውሮፓዋ ጀርመን ለ3 ጊዜያት (በ1954፤ በ1974 እና በ1990 እኤአ) እንዲሁም አርጀንቲና ለ2 ጊዜያት (በ1978 እና በ1986 እኤአ) የዓለም ሻምፒዮን ሆነዋል፡፡ የእነዚህ የዓለም ዋንጫ ድሎች ታሪክ ከዚህ በታች የቀረበው ነው፡፡
በፊፋ የወርቅ ኢዮቤልዩ የደመቀው የጀርመን የመጀመርያ ድል
በ1954 እ.ኤ.አ 5ኛው ዓለም ዋንጫ  በአውሮፓዊቷ አገር ስዊዘርላንድ የተካሄደ ነበር፡፡   ሁለተኛው ዓለም ጦርነት ትኩሳት ከረገበ ከ8 ዓመታት በኋላ ነው፡፡ ይህ ዓለም ዋንጫ ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ጋር መያያዙ ልዩ ያደርገዋል፡፡ የዓለም ዋንጫ የቴሌቨዥን ስርጭት በጥቁርና ነጭ ለመጀመርያ ጊዜ የተከናወነበትም ነበር፡፡ በሌላ በኩል  በአጠቃላይ 140 ጐሎች ከመረብ ማረፋቸውና ባንድ ጨዋታ በአማካይ 5.38 ጐሎች መመዝገቡ እስካሁን በሪከርድነት ቆይቷል፡፡ በ5ኛው የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ የተገናኙት ምዕራብ ጀርመንና ሃንጋሪ ነበሩ፡፡ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በካፒታሊዝም ስርዓት ይተዳደር በነበረው የአገሪቱ ክፍል ተወካይነት ምእራብ ጀርመን ተብሎ የተሳተፈ ነበር፡፡   በ1950ዎቹ ምርጥ ከሚባሉ  ቡድኖች አንዱ የነበረውና እነ ፈረንስ ፑሽካሽ፣ ቦዝስክ ኮሲስኮና ሀይ ድግኡቲ የሚገኙበት የሃንጋሪ ብሄራዊ ቡድን ደግሞ የውድድሩ አስደናቂ አቋም ያሳየ ነበር፡፡ የፍፃሜው ፍልሚያ በስዊዘርላንዷ በርን ከተማ በሚገኘው የዋንክድሮፍ ስታድዮም ሲካሄድ ከ60ሺ በላይ ተመልካች ነበረው፡፡ የሃንጋሪ  ቡድን 2ለ0 ሲመራ ቢቆይም ከኋላ ተነስቶ 3 ጐሎችን በማስቆጠር 3ለ2 በሆነ ውጤት የምዕራብ ጀርመን  ብሄራዊ ቡድን አሸነፈ፡፡ ስለሆነም የመጀመሪያው የሻምፒዮንነት ክብር በማግኘት  የጁሌዬስ ሪሜት ዋንጫን ተቀዳጅቷል፡፡ የምእራብ ጀርመን ደጋፊዎች ብሄራዊ ቡድናቸው የጁሌዬስ ሪሜት ዋንጫን ሲረከብ በስታድዬሙ ምእራብና ምስራቅ ጀርመንን የሚያዋህደውን መዝሙር እንዳሰሙ ታሪክ ያስታውሳል፡፡
የአሁኗ ዓለም ዋንጫ ለሽልማት ቀርባ ለአስተናጋጇ ጀርመን  ሁለተኛ ድል
10ኛውን የዓለም ዋንጫ  በ1974 እ.ኤ.አ  ላይ የተካሄደው በምዕራብ ጀርመን ነበር፡፡  በ9 ዓለም ዋንጫዎች ለሻምፒዮኑ አገር ስትሸለም የቆየችው የጁሌስ ሪሜት ዋንጫ በአዲስ ተቀይራ የቀረበችበት ዓለም ዋንጫ ነበር፡፡ የጁሊዬስ ሪሜት ዋንጫን  ብራዚል ለሶስተኛ ጊዜ ወስዳ በማስቀረቷ  አዲሷ የፊፋ ዓለም ዋንጫ መሰራቷ አስፈላጊ ሆኗል፡፡ አዲስ የዋንጫ  ሽልማት ከ7 የተለያዩ አገሮች ቀራፂዎች የሰሯቸው 53 የተለያዩ ዲዛይኖች ለውድድር ቀረቡ፡፡ በጣሊያናዊው ቀራፂ ሲልቪዮ ጋዚንጋ  የቀረበችው ዋንጫ ተመረጠች፡፡ 10ኛው ዓለም ዋንጫ ከቀዳሚዎቹ 9 ዓለም ዋንጫዎች ልዩ ካደረጉት ሁኔታዎች አንዱ በባለቀለም ቴሌቪዥን ስርጭት ማግኘቱ ነበር፡፡ በሌላ በኩል የሆላንዳዊያን የ‹ቶታል ፉትቦል› የአጨዋወት ፍልስፍና የሚወሳ ታሪክ ነበር፡፡ በዋንጫው ጨዋታ የምዕራብ ጀርመን ብሔራዊ ቡድን እና በቶታል ፉትቦል የተደነቀው የሆላንድ ብሄራዊ ቡድን ተገናኙ፡፡ ምዕራብ ጀርመን  በብሄራዊ ቡድኑ አምበል  ፍራንዝ ቤከንባወር  እና  በዋና አሰልጣኝ ሄልሙት ሾን  የተመራ ነበር፡፡ ሆላንድ ደግሞ በአሰልጣኝ ሩኒስ ሚሸልስና በታዋቂው ተጨዋች ዮሃን ክሮይፍ አስደናቂ አቋም በማሳየት ለዋንጫው የታጨ ነበር፡፡  የምዕራብ ጀርመን ብሔራዊ ቡድን 2ለ1 በማሸነፍ አዲሷን የዓለም ዋንጫ ለመጀመርያ ጊዜ እንዲሁም በውድድሩ ታሪክ ሁለተኛው የዓለም ሻምፒዮናነት ክብር አስመዘገበ፡፡ ለምዕራብ ጀርመን የማሸነፊያዋን ግብ ያስቆጠረው ዘ ቦምበር በሚል ቅል ስሙ የሚታወቀው ገርድ ሙለር ነበር፡፡ ጀርመናዊያን ቄሳሩ እያሉ በሚያሞግሱት ፍራንዝ ቤከንባወር የተመራው ብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ሚዬርና በርቲ ቮጎትስ የተባሉ ምርጥ ተጨዋቾች ይታወሳሉ፡፡
የአርጀንቲና የመጀመርያ ድል
በ1978 እ.ኤ.አ 11ኛውን  የዓለም ዋንጫ የማስተናገድ እድል ያገኘችው አርጀንቲና ናት፡፡ በ1ኛው ዓለም ዋንጫ ለፍፃሜ ተጫውታ ዋንጫውን በኡራጋይ ከተነጠቀች ከ48 ዓመታት በኋላ ወደ እግር ኳስ ሃያልነቷ ለመመለስ የበቃችበት ነበር፡፡  በዓለም ዋንጫው ዋዜማ አርጀንቲናን ያስተዳድር የነበረው መንግስት በመፈንቅለ መንግስት  ተገልብጦ አምባገነኑ መሪ ጄኔራል ቪዴላ ስልጣን መያዛቸው ነበር፡፡ ስለሆነም የዓለም ዋንጫው መሰናዶ በጄኔራል ቪዴላ መንግስት በሰብአዊ መብት ጥሰትና በአምባገነናዊ ስርአቱ ከበርካታ አገራት ተቃውሞ የተሰነዘርበት ነበር፡፡ የሻምፒዮናነት ክብሩን ለመጀመርያ ጊዜ ለማግኘት ተስፋ በማድረግ በ11ኛው የዓለም ዋንጫ ለፍፃሜ ጨዋታ የቀረቡት አስተናጋጇ አርጀንቲና እና ሆላንድ  ነበሩ፡፡ የፈረንሳዩ ለኢክዊፔ ጋዜጣ እና ሌሎች አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃናት አስቀድመው ከተደረጉት 10 የዓለም ዋንጫዎች ምርጡ የፍፃሜ ፍልሚያ ተብሎ ነበር፡፡ አርጀንቲና 3ለ1 በሆነ ውጤት ሆላንድን በማሸነፍ  በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ድል አግኝታለች፡፡ በወቅቱ የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት የመሩት ሴዛር ሜኖቲ ከቡድናቸው የ17 ዓመቱን ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና መቀነሳቸው ቢያስተቻቸውም ቡድናቸው የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን ተከትሎት በነበረው ውበትን የተላበሰ አጨዋወት  አድናቆት አትርፈውበታል፡፡ ከተጨዋቾች አምበል የነበረው ዳንኤል ፓሳሬላ እና ማርዮ ኬምፐስ የተባለው አጥቂ ከፍተኛ አድናቆት ያተረፉ  ነበሩ፡፡ የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የጨረሰው ማርዮ ኬምፕስ በአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ከነበሩ  ተጨዋቾች መካከል  በፕሮፌሽናልነት በስፔን ላሊጋ ለሚወዳደረው ሻሌንሺያ ክለብ በመጫወት ብቸኛው ነበር፡፡
በማራዶና ጀብድ የአርጀንቲና ሁለተኛ ድል
13ኛው የዓለም ዋንጫ በ1986 እ.ኤ.አ ላይ በሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ ዞን የምትገኘው ሜክሲኮ ጊዜ ያስተናገደችው ነበር፡፡  ይህ ዓለም ዋንጫ በመስተንግዶ ማራኪነት፤ በስታድዬሞች በታየው ሜክሲኳውያን ማዕበል የተባለው ድጋፍ አሰጣጥና በአርጀንቲናዊው ኮከብ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ባሳየው የላቀ ችሎታ የማይረሳ  ነው፡፡  በዚህ ዓለም ዋንጫ ላይ በፍፃሜ ጨዋታ የተገናኙት አርጀንቲና ከምእራብ ጀርመን ጋር ነበር፡፡ ከ115ሺ በላይ ተመልካች ባስተናገደው ታላቁ አዝቴካ ስታድዬም የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ 2ለ2 በሆነ ውጤት እስከ 83ኛው ደቂቃ ቆየ፡፡  ማራዶና ለቡድን አጋሩ ጆርጌ ቡርቻጋ አመቻችቶ ያቀበለው ምርጥ ኳስ አማካኝነት  የማሸነፊያ ጎል ተመዘገበችና በአርጀንቲና 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ከ30 ሚሊዮን በላይ አርጀንቲናውያንም በድሉ ፌሽታ መላው አገራቸውን በደስታ አጠልቅልቀው ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡ አርጀንቲናን በአምበልነት እየመራ ለታላቁ የዓለም ዋንጫ ድል የበቃው ማራዶና  በአንድ ተጨዋች ጀብደኛነት ውድድረን ማሸነፍ እንደሚቻል ያሳየበት ነበር፡፡ አርጀንቲና እስከዋንጫው ባደረገችው ግስጋሴ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና አምስት ጎሎችን ከማግባቱም በላይ ለሌሎች  አምስት ግቦች መመዝገብ ምክንያትም ሆኗል፡፡ ማራዶና በምርጥ ችሎታው ዓለምን ማንበርከክ ቢችልም በተለይ በእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ላይ በእጁ ያስቆጠራት ግብ ግን የብዙዎችን አድናቆት ወደ ቁጣ ቀይራዋለች፡፡ በወቅቱ ለንባብ የበቃው የፈረንሳዩ ጋዜጣ ሌኢክዌፔ ማራዶናን ‹‹ግማሽ መልዓክ ግማሽ ሰይጣን››  ብሎታል፡፡
የዓለም ዋንጫ ድል ሃትሪክ በጀርመን  
14ኛው ዓለም ዋንጫ በ1990 እኤአ ላይ በጣሊያን አዘጋጅነት የተደረገ ነው፡፡ በውድድሩ ታሪክ  ዝቅተኛ የግብ ብዛት የተመዘገበበት ወቅት ነበር፡፡ አዘጋጇ ጣሊያን በግማሽ ፍፃሜው ከጨዋታ ውጪ የሆነችው በአርጀንቲና ተሸንፋ ነበር፡፡ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና በአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ስለነበር ግን በክለብ ደረጃ የሚጫወትበት ናፖሊ ክለብ ደጋፊዎች ግራ ተጋብተው ነበር፡፡ ጣልያን ትተው እሱን እንደግፍ በሚል ተወዛግበዋል፡፡
በዚህ ዓለም ዋንጫ በፍፃሜ ጨዋታ የተገናኙት  በታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ አርጀንቲና እና ምዕራብ ጀርመን ነበሩ፡፡ በሮም ኦሎምፒክ ስታድዬም በተደረገው ጨዋታ የምእራብ ጀርመን ብሔራዊ ቡድን  አርጀንቲናን 1ለ0 ረታ፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በፍፃሜ ጨዋታ በታላቁ አዝቴካ ስታድዬም በማራዶና በተመራችው አርጀንቲና የደረሰበትን ሽንፈት በመበቀል ለ3ኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን መሆን ችሏል፡፡ በወቅቱ የቡድኑ አሰልጣኝ የነበረው ፍራንዝ ቤከን ባወር ደግሞ የዓለም ዋንጫን በተጨዋችነት በ1974 እኤአ ላይ ካሸነፈ ከ16 ዓመታት በኋላ በአሰልጣኝነት በማሸነፍ በውድድሩ ታሪክ አስደናቂ ክብረወሰን አስመዝግቧል፡፡

Read 3246 times