Saturday, 12 July 2014 12:36

የተሰረቀው ጥንታዊ የኢትዮጵያ ስዕል በፓሪስ ሊሸጥ ሲል ተገኘ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

         በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተሳለ የተነገረለትና ፓሪስ ውስጥ ከሚገኘው ‘ሚዩዜ ዲ ኢሆሜ’ ሙዚየም እኤአ በ1989 የተሰረቀው የቅዱስ ዮሃንስን ምስል የሚያሳይ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ስዕል፣ ከሰሞኑ ዱሮውት በተባለ አጫራች ድርጅት አማካይነት ማይሰን ፒያሳ ውስጥ በተዘጋጀ ጨረታ ለሽያጭ ቀርቦ መገኘቱን ዘ ፊጋሮ የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ ባለፈው ሰኞ ዘግቧል፡፡
እኤአ በ1932 ማርሴል ግሪአውሌ የተባሉ የኢትኖግራፊ ባለሙያ ከዳካር እስከ ጅቡቲ ባደረጉት የጥናት ጉዞ በእጃቸው እንዳስገቡትና አባ አንጦንዮስ በተባለ ደብር ውስጥ እንደነበረ የተነገረለት ይህ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ስዕል፣ ወደ ሙዚየሙ ከመግባቱ በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ለተመልካች የቀረበው ፈረንሳይ ውስጥ በሚገኝ ቤተክርስቲያን ነበር ተብሏል፡፡
ባለሙያው ቤተክርስቲያኑ መሰል ጥንታዊና ውድ ስዕሎችን ለማሰቀመጥ ምቹ አለመሆኑን በመግለጽ ስዕሎቹን በዘይት ቀለም አስመስለው በማሰራት ለመተካትና ዋናውን ቅጂ ለማውጣት እንዲችሉ ያቀረቡት ጥያቄ በአካባቢው የቤተክህነት አስተዳዳሪዎች ፈቃድ ማግኘቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የስዕሉን ከቤተክርስቲያኑ መውጣት ቢቃወሙም የስልጣን ላይ የነበሩት የፈረንሳይ ንጉስ ግን ድጋፋቸውን ለባለሙያው መስጠታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
በግለሰቡ እጅ ላይ ለተወሰነ ጊዜ ቆይቶ፣ ፓሪስ ውስጥ ወደሚገኘው ‘ሚዩዜ ዲ ኢሆሜ’ ሙዚየም እንዲገባ የተደረገው  ይህ ስዕል፣ እኤአ በ1989 ከሙዚየሙ የስዕል ስብስቦች መካከል ድንገት እንደተሰወረና ማን እንደሰረቀው ሳይታወቅ ደብዛው ጠፍቶ እንደኖረ ተነግሯል፡፡
ከ25 አመታት በኋላ ታዲያ፣ ጃክ ሜርሲየር የተባሉ በኢትዮጵያ ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን በመስራት የሚታወቁ ምሁር ናቸው፣ ደብዛው ጠፍቶ የኖረውን ይህን ጥንታዊ ስዕል በጨረታ ሊሸጥ ቀርቦ ባለበት ሁኔታ ሰሞኑን ድንገት ያገኙት፡፡ የእኒህን ምሁር ጥቆማ የተቀበለው ሙዚየሙ አጫራቹን ድርጅት በማግኘት ስለጉዳዩ ያነጋገረ ሲሆን፣ ስዕሉን ለጨረታ ያቀረበችው ነዋሪነቱ በፈረንሳይ የሆነው የታዋቂው ኩባዊ ሰዓሊ ጃኪን ፌረር ባለቤት መሆኗ ታውቋል፡፡
 ሴትዮዋ ስዕሉ ከሙዚየሙ ከጠፋ ከጥቂት አመታት በኋላ ከአንድ ገበያ እንደገዛችው ተናግራለች፡፡ በወቅቱ ስዕሉን ከሙዚየሙ ማን እንደሰረቀውም ሆነ ለእሷ እንደሸጠላት አሁንም ድረስ የተጨበጠ ነገር አልተገኘም፡፡
ስዕሉ ግን ሙዚየሙ ከሴትዮዋ ጋር ባደረገው ስምምነት ሊሸጥ ከቀረበበት ጨረታ እንዲወጣ የተደረገ ሲሆን፣ በቀጣይም ኳይ ብራንሊ ውስጥ በሚገኘው የስዕል ማዕከል ውስጥ ከሚገኙት የሌሎች 11 ቅዱሳን ስዕሎች ጋር እንዲቀላቀል የሚደረግ መሆኑ ተገልጧል፡፡



Read 5095 times