Saturday, 12 July 2014 12:35

ላሊበላ መታየት ካለባቸው 50 የአለማችን ከተሞች አንዷ ናት ተባለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የጣሊያኗ ቬነስ በአንደኛ ደረጃ ተቀምጣለች


ዩኔስኮ በአለም ቅርስነት ከመዘገባቸው የኢትዮጵያ ቅርሶችና የቱሪስት መስህቦች መካከል የሚጠቀሱት ጥንታዊ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙባት የላሊበላ ከተማ፣ ‘አንድ ሰው በህይወት ዘመኑ ሊያያቸው የሚገባቸው 50 ምርጥ የአለማችን ከተሞች’ በማለት ታዋቂው ሃፊንግተን ፖስት ጋዜጣ ከጠቀሳቸው ከተሞች ተርታ ተመደበች፡፡
ጋዜጣው በቅርቡ ሚኑቢ ዶት ኔት በተባለ ድረገጽ አማካይነት የአለማችን ጎብኝዎች የሚያደንቋቸውን ታላላቅ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲጠቁሙ በማድረግ ባሰባሰበው መረጃ፣ በጎብኝዎቹ ከተመረጡ 50 የአለማችን ከተሞች ዝርዝር ውስጥ ላሊበላ 17ኛ ቦታ ላይ መቀመጧን ታዲያስ መጽሄት በሳምንቱ መጀመሪያ ዘግቧል፡፡
ላሊበላ ከኢትዮጵያ ታላላቅ ቅዱስ ከተሞች አንዷ ናት ያለው ሃፊንግተን ፖስት፣ በውስጧ የያዘቻቸው ጥንታዊ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትም በመላው አለም የሚታወቁ ድንቅ መስህቦች መሆናቸውን ገልጧል፡፡
ከጥንታዊ የአገራት ርዕሰ መዲናዎች፣ እስከ እስያ ዘመናዊ ከተሞች በመላው አለም የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ከተሞችን ባካተተው በዚህ ዝርዝር ውስጥ ቀዳሚነትን ያገኘችው የጣሊያኗ ቬነስ ናት፡፡ የሚያማምሩ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ ገራሚ አብያተ ክርስቲያናት፣ ማራኪ ቤቶች፣ ምቾት የሚለግሱ መጠጥ ቤቶች ብዙ ብዙ ማራኪ ነገሮች የሞሉባት ቬነስ፣ ከአለም ከተሞች አምሳያ የሌላት ምርጥ ከተማ ናት ብሏታል ጋዜጣው፡፡
የስፔን ነገስታት መናገሻ ውብ ከተማ፣ ጎብኝዎች በብርቱካናማ አበቦች የተዋቡ ጠባብ መንገዶቿን ተከትለው በመጓዝ ማራኪ ጥንታዊ ህንጻዎችን አሻግረው እየቃኙ መንፈሳቸውን የሚያድሱባት አይነግቡና ቀልብ አማላይ ከተማ በማለት ሁለተኛ ደረጃ የሰጣት ደግሞ የስፔኗን ሲቪሊ ነው፡፡
 ኒዮርክ ሲቱን ሶስተኛዋ መታየት ያለባት የአለማችን ቀልብ ገዢ ከተማ ያላት ሃፊንግተን ፖስት፤ የትም ዙሩ የትም፣ እንደ ኒዮርክ ሲቲ መንፈስን ገዝቶ በአድናቆት የሚያፈዝ የኪነጥበብ፣ የባህል፣ የምግብ አሰራርና የንግድ እንቅስቃሴ በአንድ ላይ ተዋህደው የሚገኙባት ከተማ በየትኛውም የአለም ጥግ አታገኙም ብሏል፡፡
የህንዷን ላህሳ በመንፈሳዊ ማዕከልነቷና በማራኪ የተፈጥሮ ገጽታዋ፣ የብራዚሏን ሪዮ ዲ ጄኔሮ በውበቷ፣ የእንግሊዟን ለንደን በምርጥ ሙዚየሞቿና በጎብኝዎች ተመራጭ ከሆኑ የአለማችን ቀዳሚ ከተሞች አንዷ በመሆኗ በተከታታይ እስከ ስድስተኛ ያለውን ቦታ ሰጥቷቸዋል፡፡ የሞሮኮዋ ማራኬች፣ የዮርዳኖሷ ፔትራ፣ የጣሊያኗ ሮምና የህንዷ ቫራናሲም አንድ ሰው በህይወት ዘመኑ ሳለ ሳያያቸው ማለፍ የሌለባቸው ከተሞች ናቸው ተብለዋል፡፡

Read 2185 times