Saturday, 12 July 2014 12:30

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪዎቹን የሚያሰባስብ ፅ/ቤት ሊከፍት ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

የቀድሞ ተማሪዎቹን የሚያሰባስብ ፅ/ቤት ሊከፍት ነው
ዩኒቨርሲቲው እስከዛሬ ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል
622 መምህራን መኖርያ ቤት ተገንብቶላቸዋል

ዩኒቨርሲቲው እስከዛሬ ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል
622 መምህራን መኖርያ ቤት ተገንብቶላቸዋል

የተመሰረተበትን 60ኛ ዓመት ያከበረው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤ ከ35ሺህ የቀድሞ ምሩቃኖቹ መካከል ከ500 በላይ የሚሆኑትን በድጋሚ ያስመረቀ ሲሆን የቀድሞ ተማሪዎችን የሚያሰባስብ ጽ/ቤትም ይከፈታል ተብሏል፡፡
ዩኒቨርሲቲው 60ኛ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው የሚገኙ 1ሺህ ያህል የቀድሞ ምሩቃኖቹን በልዩ ስነ-ስርአት በድጋሚ ለማስመረቅ ጠርቶ የነበረ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ተገኝተው የስነ-ስርአቱ ታዳሚ ሆነዋል፡፡ የቀድሞ ተማሪዎችን በድጋሚ ለማስመረቅ ያስፈለገበትን ምክንያት ያስረዱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕ/ር መንገሻ አድማሱ፤ “እውቀት የቀሰሙበት ዩኒቨርሲቲ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ እንዲያውቁትና ለዩኒቨርሲቲያቸው የተቻላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ ነው” ብለዋል፡፡ በቀጣይም ስለቀድሞ ተመራቂዎችና ከዩኒቨርሲቲው ተመርቀው በስራ ላይ ስላሉት ምሩቃኖች ሙሉ መረጃ አሠባስቦ በመያዝ፣ ተማሪዎቹ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሱ ክትትል የሚያደርግ ጽ/ቤት ለማቋቋም ዩኒቨርሲቲው ማቀዱን ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል፡፡
“ዩኒቨርሲቲውን ከአፍሪካ ቀዳሚዎች ተርታ ለማሰለፍ እየሰራን ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለውጭ ሃገር ዜጎች ባመቻቸው የትምህርት እድልም ከጅቡቲና ከሶማሊያ 25 የህክምና ተማሪዎችን ተቀብሎ 17 ያህሉን ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው የምረቃ ፕሮግራም ላይ አስመርቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም ከደቡብ ሱዳን ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሰልጠን እቅድ መያዙን ፕሬዚዳንቱ አክለው ገልፀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ጥራቱ በተለያዩ ጊዜያት በተሰጡት ደረጃዎች በኢትዮጵያ ካሉት በ2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ቢሆንም የመማር ማስተማር ሂደቱም ሆነ የትምህርት ጥራቱ ውጤታማ ነው ብለን እናምናለን ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ከሌላው ዩኒቨርሲቲ በተለየ የመምህራኖች በዩኒቨርሲቲው ተረጋግቶ መቆየት ሂደቱን ውጤታማ አድርጎታል ብለዋል፡፡ አስተዳደሩም የመምህራኑን ምቾት ለመጠበቅ ሲል በ220 ሚሊዮን ብር ገደማ እዚያው ጐንደር ከተማ አዘዞ አካባቢ ባለ 31 ብሎክ ህንፃዎችን አስገንብቶ ለ622 መምህራን የመኖሪያ ቤቶችን በቅርቡ እንደሚያስረክብ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው መምህራን ከዩኒቨርሲቲው ከሚያገኙት ደመወዝ ባሻገር እዚያው ጎንደር ከተማ ሃኪሞቹ የራሳቸውን ክሊኒክና የተለያዩ ስራዎችን በትርፍ ጊዜያቸው መስራታቸው ለመምህራኑ ገቢ ማደግ አስተዋፅኦ እንዳለው የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ዩኒቨርሲቲው መምህራኑ በተጓዳኝ ገቢ የሚያገኙበትን የስራ መስክ እንዲፈጥሩ ያበረታታል ብለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ግቢ ለመማር ማስተማሩ ሂደት የተመቻቸ እንዲሆን የተለያዩ የአካባቢ ጥበቃ እና የመናፈሻ ስራዎች ከመሰራታቸው ባሻገር በግቢው ላይ የዋይ ፋይ ኢንተርኔት አገልግሎት በማንኛውም ቦታ እንዲገኝ ተደርጓል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡
በዘንድሮው አመት በተለያዩ የትምህርት መስኮች የተመረቁትን 4135 ተማሪዎችን ጨምሮ ዩኒቨርሲቲው በ60 ዓመት ጉዞው ወደ 40 ሺህ ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን ከጤና ኮሌጅነት ተነስቶ በአሁን ሰዓት ዘጠኝ ፋኩልቲዎች፣ ኮሌጆች እና ት/ቤቶች አሉት ተብሏል፡፡ 60ኛ ዓመቱን ለማክበር 8 ሚሊዮን ብር ገደማ እንዳወጣ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ ወጪው የተጋነነ አይደለም፤ የዩኒቨርሲቲውን አርማ ከያዙ ቲ-ሸርቶች፣ እስክርቢቶና ከረቫት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውን የ60 ዓመት ጉዞ ከሚያስዳስሰው መፅሃፍ ሽያጭ ወጪውን እንመልሳለን ብለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ስር የሚተዳደረው የጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል የተመላላሽ ታካሚዎች ሆስፒታል በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተመረቀ ቢሆንም ሥራ ለመጀመር የሚያስችሉ የህክምና መሳሪያዎችና አልጋዎች እንዳልተሟሉለት ታውቋል፡፡ ለሆስፒታሉ የሚስፈልጉ ውድ የህክምና መሳሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለመለገስ ቃል እንደተገባ ለማወቅ ተችሏል፡፡
“ጐንደር ዩኒቨርስቲና የገበሬዎቹ ውለታ”
የዛሬው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለመመስረቱ ምክንያት የሆነው የወባ በሽታ ነው፡፡ ከ60 ዓመት በፊት ጎንደር ደንቢያ ላይ 20ሺህ ሰዎች በወባ መጠቃታቸውን ተከትሎ ዩኤስ ኤይድ፣ ዩኒሴፍ፣ የአለም ጤና ድርጅት እና የኢትዮጵያ መንግስት በጋራ በመሆን ለተጎጂዎች ህክምና የሚሰጥበትን ጤና ጣቢያ ቆላ ድባ በተባለ ቦታ ከፈቱ፡፡ በኋላም እዚያው የማህበረሰብ ጤና አጠባበቅ ኮሌጅ ተመሰረተ፡፡ ከዚያው ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ደረጃ አድጎ ከ10 ዓመት በፊት ሙሉ ለሙሉ ዩኒቨርሲቲ ሆነ፡፡ በኮሌጅ ደረጃ ሲመሰረት በዚያው በጎንደር ሆስፒታል ግቢ ውስጥ የነበረ ሲሆን ኋላም የማስፋፋት እቅድ ሲመጣ ማራኪ በሚባለው የከተማ አካባቢ ነዋሪ የነበሩ 59 ገበሬዎች “ልጆቻችን የትም ሳይሄዱ እዚሁ ትምህርት ማግኘት ከቻሉ፣ በነፃ ቦታውን እንሰጣለን” በማለት ቦታውን በ1963 ዓ.ም በነፃ ሰጡ፡፡ አፄ ኃይለሥላሴም የመሰረት ድንጋዩን ካኖሩ በኋላ ቦታውን ማራኪ ብለው ሰየሙት። እነዚያ ገበሬዎች በሰጡት ቦታ ላይ ዛሬ የማራኪ ካምፓስን ጨምሮ ቴዎድሮስና ፋሲል የተባሉ ሶስት ካምፓሶች ተገንብተውበት ለትምህርት አገልግሎት ውሏል። ዩኒቨርሲቲው ገበሬዎቹ አሊያም የገበሬዎቹን ቤተሰቦች አግኝቶ በሰፊው የመዘከር ሃሳብ እንደነበረው የጠቆሙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሙሉ ለሙሉ ባይሳካም በየጊዜው በሚወጡ መፅሄቶች እና የዩኒቨርሲቲውን ታሪክ በያዙ ፅሁፎች ላይ እንደሚያስታውሷቸው ገልፀዋል፡፡

Read 2239 times