Saturday, 12 July 2014 12:27

ለስኬት የሚያበቁ ሰባት የቢዝነስ ግቦች መመሪያዎች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

ባለፈው ሳምንት “ስማርት” ስለተባሉት የቢዝነስ መመሪያዎች ስንነጋገር፣ በአሁኑ ወቅት ሕይወትም ሆነ ቢዝነስ ያለእቅድና ግብ አይመራም ብለን ነበር። በዚህ ሳምንት ቀጣዩን ክፍል ነው የማቀርበው፡፡
ለሕይወታችንና ለቢዝነስ የምንቀርፃቸው ግቦች በሁለት ይከፈላሉ፡፡ አንደኛው ግብ በአብዛኛው ከአሁን ቀደም የሰራነውና የምናውቀው ስለሆነ 95 በመቶ ይሳካል ብለን የምንቀ    ርፀው ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ቀደም ብለን በፍፁም ያልሞከርነውና የማናውቀው ስለሆነ ያለመሳካት ዕድሉ 95 በመቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ልንሰራውና ልንሞክረው እንፈልጋለን፡፡ ዝርዝር ውስጥ ባንገባም ሁለቱም የቢዝነስ ግቦች በራሳቸው መንገድ ጠቀሜታ አላቸው፡፡
የግብ ዕቅድ በማንኛውም መንገድ ሊዘጋጅና ሊፃፍ ይችላል፡፡ የዚህ ጽሑፍ መጠነኛ ትኩረት ግብ ቀረፃ ላይ ቢሆንም በአብዛኛው ግን፣ ግቡን በመፈፀም ሂደት ላይ የበለጠ ያተኩራል ይላሉ፤ ሚ/ር ስኮት ሃልፎርድ፣ በጁን በታተመው ኢንተርፐሪነር መጽሔት ላይ ባቀረቡት ዘገባ፡፡
ጸሐፊው በማከልም “የቀረፃችሁት ግብ በእርግጥ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሊሳካ የሚችልባቸውን አንዳንድ ሁነኛ የስኬት ምክንያቶች ብትመርጡ እመርጣለሁ፡፡ ምክንያቱም ለዓላማና ግባችሁ ጠንካራና ጎበዝ መሆናችሁን ታዩበታላችሁ። የሰው ልጅ አዕምሮ፣ እርግጠኛ ሆነው ይሳካል ብለው ያመኑበትን ግብ ለማሳካት የተቃኘ ነው” ብለዋል፡፡ ስለዚህ በንግድ ሥራ ለመመንደግ ወይም ቢዝነሱን ወደ አዲስ ከፍታ ለማምጠቅ ከፈለጉ፣ ጸሐፊው ለከፍተኛ ስኬት ያበቃሉ ያሏቸውን ሰባት ነጥቦች እነሆ!
የተነቃቃ ሕልም ለትልቅ ግብ - ቤት፣ መኪና፣ ትምህርት፣… ማለም ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን እርግጠኛ ሆነው ተግባራዊ የሚያደርጉት ከሆነ ለዚያ ሥራ የሚያተጋ (የሚነቃቃ) ነገር ያስፈልጋል፡፡ የመጀመሪያው ነገር፣ ሕልሙ ላይ ለመድረስ የሚያነሳሳ ምክንያትና ጥልቅ ፍላጎት ነው፡፡
ግብዎ ጋ የሚያደርሰው መንገድ አሰልቺ፣ ችግርና መሰናክሎች የተጋረጡበት ሊሆን ይችላል፡፡ ካሰቡበት ህልም እንዳይደርሱ የሚጋረጡ በርካታ አጋጣሚዎች (ችግሮች) ሊኖሩና ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሊረዳዎትና ሊያጠነክርዎት የሚችለው ግቡ ላይ ለመድረስ ያነሳሳዎትን ምክንያት ማሰብ ነው፡፡
የሚከወኑትን ነገር ለ24 ሰዓት ይከፍላሉ፡- ግብዎ ከክብደትዎ 10 ኪሎ መቀነስ ከሆነ አዕምሮዎ የሚያውቀው በ24 ሰዓት 10 ኪሎ መቀነስ ሳይሆን በወሰኑት ጊዜ ውስጥ 500 ግራም መቀነስዎን ነው፡፡ ስለዚህ፣ ግብዎን አዕምሮዎ እንዲረዳ አድርገው ይቅረፁ፡፡ ሕልምዎ ሀብታም መሆንና መኪና መግዛት ከሆነ፣ እንዴት አድርገውና በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሀብታም እንደሚሆኑ (በየወሩ እቁብ እየጣሉ፣ ንብረት ሸጠው፣ ውርስ ተካፍለው፣ ደሞዝ አጠራቅመውና ተጨማሪ ገቢ ፈጥረው፣… በአንድ፣ በሁለት፣ በአምስት ዓመት፣ …) ተብሎና ተዘርዝሮ መቀመጥ አለበት፡፡ በጊዜ የተከፋፈለችው ትንሿ ግብ፣ ምክንያታዊና ቀጣይነት ያላት መሆን አለባት፡፡
በየወሩ ከደሞዜ 1000 ብር እየቆጠብኩ በዓመት 12 ሺ ብር ይኖረኛል፡፡ በአምስት ዓመት ደግሞ 60 ሺ ይኖረኛል፡፡ ተጨማሪ ሥራ በመስራት በወር 10ሺ ብር፣ በዓመት 120 ሺ ብር፣ ከአምስት ዓመት በኋላ 600ሺ ብር፣… ተብሎ ግብ ከተበጀ፣ በምንም ዓይነት ምክንያት ከዕቅዱ መዛነፍ የለበትም ማለት ነው፡፡
 በየቀኑ የሆነ ነገር ይሥሩ፡- ካሰቡት ግብ ላይ ለመድረስ፣ በየቀኑ ከሚያደርጉት የሥራ ድግግሞሽና ፍጥነት የበለጠ ምንም ዓይነት ነገር ወደ ግብዎ አያቀርብዎትም፡፡ ይህ ሲባል ግን ታምመው ቢተኙ እንኳ ከዕለታዊ ሥራዎ መቅረት የለብዎትም ማለት አይደለም፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ሲያጋጥም ወይም ሲደብርዎት ሊያቋርጡት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ግብዎ ጋ ለመድረስ የመጀመሪያዎቹን 30 ቀናት በሚገባ ካልተጠቀሙና የአካሄድዎን ፍጥነት ካልለኩ 90 ከመቶ ግብዎን እንደማያሳኩ ማረጋገጫ ይሆናል፡፡ ስለዚህ፣ የመጀመሪያዎቹ 30 ቀናት ቁርጠኛ እንደሆኑ አዕምሮዎን ለማሳመን እጅግ ወሳኝ ናቸው፡፡
መቀየርና ማስተካከል (Adapt and Adjust)፡- ትልቁ ግብ ላይ ለመድረስ የሚችሉበትን ትንሿን የዕለት ተዕለት ግብ ሲተገብሩ፣ አመቺ ያልሆነ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥም፣ ሁኔታውን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ የየዕለቱ ትንሿ ግብም በጣም ቀላል ከሆነች ጥሩ አይደለም። አተገባበሩ በጣም ቀላል ከሆነ የበለጠ ከበድ ያድርጉት፡፡ በአጠቃላይ፣ ወዳሰቡት ግብ ለመድረስ የሚደረገው ትግልና ጥረት ከባድ ከሆነ ደግሞ ቀለል ያድርጉት፡፡
የሰው አስተያየትና ሽልማት (Feedback and Reward)፡- የሰው ልጅ አዕምሮ፣ አዲስ ነገር ለመማርና አዲስ ባህርይና እውቀት ለመቅሰም ሁለት ነገሮች ያስፈልጉታል፡፡ አንደኛው አስተያየት (Feedback) ሲሆን፣ ሌላኛው ሽልማት (Reward) ነው፡፡
ግብዎን ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ፣ የሌሎች አስተያየት ምን እንደሆነ ለመጠየቅ ድፍረት ይኑርዎት፡፡ “ይኼን ነገር እንዴት አየኸው? ምኑ መስተካከል አለበት ትላለህ/ትያለሽ?...” ብሎ መጠየቅ፣ ስህተትን አውቆ ለማስተካከል በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ የሰዎች አስተያየት ጥሩ ከሆነና ወደ ግብዎ ለመድረስ ትክክለኛ መስመር ላይ ከሆኑ ጥሩ ነው፣ በየዕለቱ ትንሿን ግብዎን ያለስህተት ስላከናወኑ፣ እውቅና እንዲሆንዎ ራስዎን ይሸልሙ፡፡
ውጤታማ ሥራ ባከናወኑበት ቀን፣ ትንሽ ወርቃማ የኮከብ ምልክት የሚያደርጉበት ቀን መቁጠሪያ ቢኖርዎ ለበለጠ ለትጋት የማነሳሳት አቅም እንዳለው በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ትክክለኛ ሥራ እያከናወኑ መሆኑን መገንዘብ ለአዕምሮ በቂ ሽልማቱ ነው፡፡         
በትኩረት ያልሰሩበትን ጊዜ ይለዩ (Schedule Slop Time):- ላቀዱት ግብ ትኩረት ያልሰጡበትን ወይም ራስዎን ያታለሉበትን ወይም ጭራሽ ያልሰሩበትን ጊዜ መዝግበው ይያዙ፡፡ ምክንያቱም፣ ያንን የባከነ ጊዜ ተመልሰው ስለሚሰሩ፣ ለጊዜው ተግባርዎን ያለመወጣትዎ ሊያሳዝንዎትና ሊያሸማቅቅዎት አይገባም፡፡ ግን ልማድ እንዳይሆን በጣም ይጠንቀቁ፡፡
መሰልቸት እንዳለ ይወቁ፡- አንድን ነገር በየቀኑ ትንሽ ትንሽ መሥራት ሊያሰለች ይችላል። ቢሆንም ግን አያቋርጡ፡፡ ምክንያቱም፣ ያቀዱት ግብ ላይ መድረስ፣ በየቀኑ የደስታ ሻምፓኝ የመክፈት ሥነ-ሥርዓት ያህል ቀላል አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ በየቀኑ ጥቃቅን ነገሮች ላይ አጣብቆ የሚያውል አሰልቺ ነገር መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ይህን ነገር ተገንዝቦ በየቀኑ ትንሽ ጠንከር አድርጎ ደጋግሞ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ግባቸውን የሚያሳኩ ሰዎች፣ ነገሮች ከባድና አሰልቺ ሲሆኑባቸው ብዙ ጊዜ የሚያደርጉት እንደዚያ ነውና፡፡  

Read 3895 times